ለ7ኛው ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ ከቀረቡት የፓርላማ ዕጩዎች መካከል ሴቶቹ ከሩብ በታች (23%) መሆናቸው ታወቀ

ለ7ኛው ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት (የፓርላማ) ተወዳዳሪ ለመሆን የዕጩነት የምስክር ወረቀት ከተሰጣቸው 2,080 ዕጩዎች መካከል የሴቶቹ ድርሻ ከሩብ በታች መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መረጃ አመላከተ። ቦርዱ ይፋ ባደረገው በዚህ መረጃ መሠረት፣ ከጠቅላላው የፓርላማ ዕጩዎች መካከል 481ዱ (23 በመቶ) ብቻ ሴቶች ሲሆኑ፣ ቀሪዎቹ 1,599ኙ ወንዶች ናቸው።

ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዕጩ ካስመዘገቡ 40 የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ጥምረቶች መካከል፣ 12ቱ አንድም ሴት ዕጩ ለፓርላማ ውድድር አላስመዘገቡም።

በአንፃሩ ጥቂት ፓርቲዎች ሴት ዕጩዎች በማቅረብ ረገድ ተሽለው ታይተዋል። የወለኔ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ምንም እንኳን ለፓርላማ ያቀረባቸው ዕጩዎች ብዛት ሦስት ብቻ ቢሆንም፣ ሁለቱ ሴቶች ናቸው። የሲዳማ አንድነት ፓርቲም ከ15 የፓርላማ ዕጩዎቹ ዘጠኙን ሴቶች ለማድረግ በቅቷል። ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የፓርላማ ዕጩዎችን ካስመዘገቡ 4 ፓርቲዎች መካከል ገዢው ብልፅግና ፓርቲ ከ461 ጠቅላላ የፓርላማ ዕጩዎቹ መካከል 196ቱ (43 በመቶ) ሴቶች በማድረግ የተሻለ ፆታዊ ምጥጥን ሲፈጥር፣ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) 10 በመቶ፣ ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት 19 በመቶ፣ እና ነፃነት እና እኩልነት ፓርቲ (ነእፓ) 9 በመቶ ብቻ ሴት ዕጩዎችን ለውድድር በማቅረብ ዝቅተኛ የሴቶች ውክልናን አሳይተዋል። [ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር]