የአፍሪካ ኅብረት ታዛቢዎች ልዑክ በዛሬው ዕለት ግንቦት 17ቀን 2018 ዓ.ም እና ግንቦት 18 ቀን 2018 ዓ.ም አዲስ አበባ እንደሚገባ ኅብረቱ ለ”ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጿል።
የምስራቅ አፍሪካ የበይነ መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ/IGAD) በበኩሉ 24 ታዛቢዎቹን በመጪው ግንቦት 21 ቀን 2018 ዓ.ም እንደሚልክ የድርጅቱ የሰላም እና ደኅንነታ ዲቪዥን ዳይሬክተር ኮማንደር አበበ ሙሉነህ ለ”ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል።
ታዛቢዎቹ ከጂቡቲ፣ ከሶማሊያ፣ ከኬንያ፣ ከደቡብ ሱዳን፣ ከኡጋንዳ እና ከሱዳን የተወጣጡ መሆናቸውንም ኮማንደር አበበ ገልጸዋል። ታዛቢዎቹ ዓለም ዐቀፍ መርሕን በተከተለ መንገድ ሥራቸውን እንደሚሠሩ የገለጹት ኮማንደር አበበ፣ ኢጋድ ምርጫው ነጻ እና ገለልተኛ እንዲሆን ያግዛል ብለዋል።
የአፍሪካ ኅብረትም በበኩሉ፣ የታዛቢ ልዑኩ አዲስ አበባ እንደደረሰ ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሚሰጥ ለ”ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” በጽሑፍ አሳውቋል። ምን ያኽል ታዛቢዎችን እንደሚያሰማራ ያልገለጸው የአፍሪካ ኅብረት፣ ዝርዝር ጉዳዮችን ለመገናኛ ብዙኃን በሚሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ይፋ እንደሚያደርግ አሳውቋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዋና ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ ሚያዚያ 15 ቀን 2018 ዓ.ም በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ላይ የአፍሪካ ኅብረት እና ኢጋድ በታዛቢነት እንደሚሳተፉ አስታውቀው ነበር።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ “ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የአውሮፓ ኅብረት ታዛቢ ይልክ እንደሆነ በጽሑፍ የጠየቀች ሲሆን፣ ኅብረቱ ታዛቢዎችን እንደማይልክ በሰጠው በጽሑፍ ምላሽ አረጋግጧል። ይሁን እንጂ የተወሰኑ የአውሮፓ ኅብረት ባለሙያዎች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው የምርጫውን ድባብ እንደሚመለከቱ “ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ከኅብረቱ ምንጮች ያገኘችው መረጃ ያመለክታል።
ባለፉት ዓመታት በተካሄዱ አገራዊ ምርጫዎች ላይ የዓለም ዐቀፍ ታዛቢዎች በቋሚነት ባይባልም አልፎ አልፎ ተገኝተው መታዘብ ችለው እንደነበር መረጃዎች ያመላክታሉ።
በ1987 ዓ.ም በተካሄደው የመጀመሪያው ጠቅላላ ምርጫ ላይ ከ23 አገራት የተወጣጡ የምርጫ ታዛቢዎች በዓለም ዐቀፉ የምርጫ ታዛቢዎች ጥምረት በኩል ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት መታዘባቸውን መረጃዎች ይታወቃል።
እንዲሁም የዓለም ዐቀፉን ማኅበረሰብ ትኩረት ስቦ በነበረው እና ሰፊ የምርጫ ፉክክር በተደረገበት 1997ቱ ጠቅላላ ምርጫ ላይ በርካታ ዓለም ዐቀፍ ታዛቢዎች ተሳትፈው ነበር። በምርጫ 97 የኢትዮጵያ መንግሥት ባደረገው ግብዣ መሠረት ከአውሮፓ ኅብረት፣ ከአፍሪካ ኅብረት፣ እና ከካርተር ማዕከል የተወጣጡ 319 የዓለም ዐቀፍ ታዛቢዎች የተሰማሩ ሲሆን፣ ይህ ቁጥር ከፍተኛ የዓለም ዐቀፍ ታዛቢዎች የተሳተፉበት የኢትዮጵያ ምርጫ ሆኖ ተመዝግቧል።
በ2002ቱ ጠቅላላ ምርጫ ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ መንግሥት የአውሮፓ ኅብረት እንዲታዘብ ፍቃድ ሰጥቶት የነበረ ቢሆንም፣ ኅብረቱ ግን ሳይሳተፍ ቀርቷል። በተመሳሳይ በ2007 በተካሄደው 5ኛው ጠቅላላ ምርጫ ላይ የአውሮፓ ኅብረት እና የካርተር ማዕከል በታዛቢነት ሳይሳተፉ ቢቀሩም፣ የአፍሪካ ኅብረት ግን ታዛቢዎችን አሰማርቶ ነበር።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ በ2013 በተደረገው 6ኛው ጠቅላላ ምርጫ ላይም የአውሮፓ ኅብረት እና የአሜሪካው ዓለም ዐቀፍ ተራድዖ ድርጅት ለመሳተፍ ጥያቄ አቅርበው የነበረ ቢሆንም፣ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በሁኔታዎች ባለመግባባታቸው ምክንያት ታዛቢ ሳይልኩ ቀርተዋል። ይሁን እንጂ የአፍሪካ ኅብረት እና ዓለም ዐቀፍ ሪፐብሊካን ኢንስቲትዩት (IRI) ግን ታዛቢዎችን ማሰማራታቸው ይታወሳል።
እስካሁን “ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ባደረገችው ማጣሪያ መሠረት 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ ለመታዘብ ከአፍሪካ ኅብረት እና ኢጋድ ውጪ ሌሎች ታዛቢዎች መኖራቸውን ማረጋገጥ አልቻለችም። [ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር]




