የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሲዳማ አርነት ንቅናቄ (ሲአን) ጠቅላላ ጉባዔ እንዲያደርግ እና የፀጥታ ድጋፍ እንዲሰጠው ለሲዳማ ክልል ፕሬዝዳንት እና ለክልሉ ፀጥታ ቢሮ ግንቦት 10 ቀን 2018 ዓ.ም. ደብዳቤ ቢልክም፣ በአዳራሽ እጦት እና የፀጥታው ኃይል “አልፈቀድኩም” በማለቱ፣ ጉባዔው እንደማይካሄድ አቶ ደሳለኝ ሜሳ ለ“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል።
ጉዳዩ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ድረስ በመሄድ በክርክር የተረታው ምርጫ ቦርድ በጻፈው ደብዳቤ ላይ፣ ከዚህ ቀደም ዕውቅና ተሰጥቶት የነበረው የሐምሌ 8 ቀን 2015ቱ ጠቅላላ ጉባዔ እና በዚያው ጉባዔ የተላለፉ ውሳኔዎች በሙሉ ሕጋዊ ውጤት የሌላቸው መሆኑን ገልጿል።
የፓርቲው የቀድሞ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ሜሳ፣ ሲአን በነገው ዕለት ግንቦት 15 ቀን 2018 ዓ.ም. ጠቅላላ ጉባዔ ለማድረግ ኮሚቴው በዝግጅት ላይ መሆኑን ተናግረው ነበር። አቶ ደሳለኝ በክልሉ ምሥራቃዊ ክፍል እና በኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ግጭት በመከሰቱ ምክንያት የፀጥታው ሁኔታ ስጋት መፍጠሩን ቢገልጹም፣ ጉባዔው ለመስተጋጓጎል የተዳረገው በአዳራሽ እጦት እና በፀጥታ ኃይሉ አለመተባበር እንደሆነ ለ“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዛሬ ከመሸ በላኩት መልዕክት አሳውቀዋል።
አቶ ደሳለኝ ያስተላለፉት መልዕክት “የክልሉ መንግሥትና የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር አዳራሽ በመከልከል፣ የሲዳማ አርነት ንቅኔቄ ጉባዔ ዝግጅት እንዲደናቀፍ እያደረጉ ነው። በኪራይም ማግኘት አልተቻለም። ቢገኝም የፀጥታው ኃይል አልፈቀድኩም ብሏል” ይላል።
ለነገ የታቀደውን ጠቅላላ ጉባዔ በተመለከተ የወቅቱ የፓርቲው ፕሬዝዳንት አቶ ለገሠ ላንቃሞ ከቦርዱ ይሁንታ ማግኘቱን ሲቃወሙ የነበረ ሲሆን፣ ድርጊቱን “ትልቅ ሕገ ወጥ ድርጊት ነው” ብለውታል። ፕሬዝዳንቱ አክለውም “ጉባዔ ለመጥራት የፓርቲው ማኅተም ያስፈልጋል፤ ሕጋዊ አካል የፈረመበት ደብዳቤ ያስፈልጋል፤ በባዶ ወረቀት ማድረግ ይቻላል ወይ?” ሲሉ ጠይቀውም ነበር።
የፍርድ ቤቱን የክስ ሂደት በግላቸው ተከታትለው እንደማያውቁ የገለጹት አቶ ደሳለኝ ሜሳ በበኩላቸው፣ ጉዳዩ አሁን ባለው አሠራር በቦርዱ እና በአዘጋጅ ኮሚቴው መካከል የሚከናወን መሆኑን ጠቁመው ነበር። ፍርድ ቤቱ ቀደም ሲል ተካሂዶ የነበረውን ጉባዔ ከሰረዘ በኋላ፣ ሲአን እና የጠቅላላ ጉባዔ አዘጋጅ ኮሚቴው በጋራ በመሆን አዲስ እና ሕጋዊ ጠቅላላ ጉባዔ እንዲያካሂዱ አዟል።
ምርጫ ቦርድም አዲሱ ጉባዔ በሕግ አግባብ፣ በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ እና በገለልተኛ ታዛቢዎች ፊት እንዲከናወን ክትትል እና ድጋፍ እንዲያደርግ ፍርድ ቤቱ መመሪያ ሰጥቷል። በ2015 ዓ.ም. ተደርጎ የነበረው ጠቅላላ ጉባዔ ተቀባይነት እንዳያገኝ ምክንያት የሆኑት ነጥቦች፣ ሂደቱ ግልጽነት የጎደለው መሆኑ፣ ሕጋዊ የሆኑ የፓርቲው አመራሮች እንዲገለሉ መደረጉ እና በጉባኤ አዘጋጅ ኮሚቴው ውስጥ የነበሩ አለመግባባቶች ናቸው ተብሏል።
የፓርቲውን ወቅታዊ ሕልውና በተመለከተ አቶ ደሳለኝ ሲያብራሩ ፓርቲው በአሁኑ ሰዓት በማንም እጅ ላይ እንዳልሆነ ገልጸው፣ ይሁን እንጂ በሐምሌ 8 ቀን 2015 ዓ.ም. የተመረጡ ሕገወጥ አካላት ዕጩዎችን መልምለው በድርጅቱ ስም ቅስቀሳ እያደረጉ ቢሆንም ድርጊቱ ሕጋዊ እንዳልሆነ ሞግተዋል።
አቶ ደሳለኝ “በሕገወጥ መልኩ የተመረጡ አካላት በድርጅቱ አባልነት የማይታወቁ ዕጩ ማቅረባቸው እየገለጹ ነው። የዚህ ሁሉ ድርጊት ዋናው ዓላማ ብልፅግና እንዲያልፍ ያማከለ” ሥራ ነው በሚል ወቀሳ የሰነዘሩ ሲሆን፣ እነዚህ የቀረቡት ዕጩዎች በሕግ እንዲታገዱ እንደሚሠሩም አስረድተው ነበር።

በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ መሠረት፣ አንድ ጠቅላላ ጉባዔ ሕጋዊ ሆኖ ለመካሄድ ቢያንስ 200 የፓርቲው አባላት በጉባዔው ላይ መገኘት ይኖርባቸዋል። ጉባዔው ከመካሄዱ በፊት በአዘጋጅ ኮሚቴ አማካኝነት ተገቢው ዝግጅት ተደርጎለት፣ ለፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ ቀርቦና ታይቶ ለጉባዔው መቅረብ ያለበት ቢሆንም፣ የወቅቱ ፕሬዝዳንት አቶ ለገሠ ላንቃሞ ግን ክስ እያቀረቡ የሚገኙት የአዘጋጅ ኮሚቴዎች “እንደ ሎጅስቲክ ያሉ ጉዳዮችን የማስተካከል እንጂ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ሥራ የሚሠሩ አይደሉም” በማለት ተከራክረዋል።
በሐምሌ 8 ቀን 2015 ዓ.ም. ጠቅላላ ጉባኤ ሲከናወን ከነበሩት ሰባት የአዘጋጅ ኮሚቴ አባላት መካከል አምስቱ ጉባዔውን አንቀበልም በማለት ክስ መስርተው እንደነበር ይታወሳል።
አቶ ለገሠ ላንቃሞ አክለውም “አቶ ደሳለኝ ሜሳ የተባሉት ግለሰብ በ2013 ዓ.ም በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከፓርቲው የታገዱ፣ በአሁን የፍርድ ቤት ክርክርም የሌሉበት ቢሆንም አምስቱን የአዘጋጅ ኮሚቴ የሚያሠማሩት እሳቸው ናቸው” ሲሉ አዲስ ክስ ሰንዝረዋል።
አቶ ደሣለኝ ሜሳ በ2013 ዓ.ም. በተደረገው 6ኛው ጠቅላላ ምርጫ ወቅት “ፓርቲው በገዢው ብልፅግና ስለተጠለፈ ከፓርቲው ወጥቻለሁ” በማለት ከዚህ ቀደም የገለጹ ቢሆንም፣ የፓርቲው ፕሬዝዳንት ግን “ምርጫ ቦርድ አግዷቸው እንጂ በገዛ ፈቃዳቸው ለቀው አልወጡም” ሲሉ ተሟግተዋል።
አቶ ለገሠ ደግሞ ክሱ በምርጫ ቦርድ እና በአዘጋጅ ኮሚቴው መካከል መሆኑን አስታውሰው፣ “ብንከሰስ ኖሮ ጣልቃ” እንገባ ነበር ካሉ በኋላ፣ ፓርቲው ቅስቀሳውን አጠናክሮ መቀጠሉን እና በሲዳማ ክልል ባሉ 19 የምርጫ ክልሎች ዕጩዎች በማቅረብ ለምርጫው ዝግጅት እያደረገ መሆኑን አሳውቀዋል።
ሐምሌ 8 ቀን 2015 ዓ.ም. ተካሄደ የተባለው ጠቅላላ ጉባዔ እና ቦርዱ ያጸደቀው የአዘጋጅ ኮሚቴ ውሳኔ መሠረታዊ የሕግ ስህተት የተፈፀመበት መሆኑን በመግለጽ፣ የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በቦርዱ መቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 1133/2011 መሠረት ውሳኔዎቹን በሙሉ ጥር 5 ቀን 2017 ዓ.ም. በሻረው ውሳኔ ማሳወቁ ይታወሳል።
ይህንን የሥር ፍርድ ቤት ውሳኔ የተቃወመው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ጉዳዩን ወደ ፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመውሰድ አቤቱታ አቅርቦ ነበር። ይሁን እንጂ ሰበር ሰሚ ችሎቱ የቦርዱን አቤቱታ መርምሮ በሥር ፍርድ ቤት ውሳኔ ላይ የተፈፀመ የሕግ ስህተት አለመኖሩን በመግለጽ፣ የቦርዱን አቤቱታ ውድቅ አድርጎ የሥር ፍርድ ቤት ውሳኔ እንዲፀና እና እግዱ እንዲነሳ መወሰኑን የሰነዱ መረጃ ያስረዳል።
የሲዳማ አርነት ንቅናቄ (ሲአን) የአራት ፓርቲዎች ግንባር የሆነው የመድረክ አባል ሲሆን፣ ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ 181 ዕጩዎችን (19 ለሕዝብ ተወካዮች እና 162 ለክልል ምክር ቤት) አቅርቧል። (ሲአን) ከመድረክ ግንባር አባል ፓርቲዎች መካከል ከፍተኛውን ዕጩ ያቀረበ ፓርቲ ሲሆን፣ ግንባሩ በጠቅላላው ካቀረባቸው 219 ዕጩዎች ውስጥ 181ዱን ያቀረበው እርሱው ነው። ኦፌኮ እና ዓረና በጋራ 6 ዕጩዎችን ብቻ ሲያቀርቡ፣ ቀሪዎቹ ዕጩዎች በአፋር ሕዝብ ለፍትሕ እና ለዴሞክራሲ ፓርቲ የቀረቡ ናቸው። ድርጅቱ የተመሠረተው በታዋቂው የሲዳማ የፖለቲካ መሪ በአቶ ወልደአማኑኤል ዱባለ መሪነት በ1961 ዓ.ም. መሆኑ ይታወሳል። [ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር]




