የጎጎት ለጉራጌ አንድነት እና ፍትሕ ፓርቲ (ጎጎት) “በጉራጌ ዞን እዣ 1 እና 2 ምርጫ ጣቢያ የሚገኙ ምርጫ አስፈፃሚዎች በአብዛኛው የገዢው ፓርቲ አባላት” መሆናቸውን ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማሳወቁን፣ ለ “ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጿል።
የፓርቲው ፕሬዝዳንት አቶ መሐመድ አብራር ከ “ምርጫ-2018 ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጋር በነበራቸው ቆይታ “አስፈፃሚዎቹ የብልጽግና ፓርቲ አባል እንደሆኑ እናውቃለን፤ ይህንን ግን ማረጋገጥ የሚችለው ፓርቲው እና ቦርዱ ብቻ ናቸው” ብለዋል።
“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ለተነሱት ቅሬታ ምላሽ እንዲሰጣት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን የጠየቀች ሲሆን፣ ቦርዱ በላከው የጽሑፍ ምላሽ፣ ጎጎት “ጉራጌ ዞን እዣ 1 እና 2 የምርጫ አስፈፃሚዎች የብልፅግና ፓርቲ አባላት ሆነው አግኝተናቸዋል” ብሎ ያቀረበውን አቤቱታ ተከትሎ “ቦርዱ ሲያጣራ ፓርቲው ቅሬታ ያቀረበባቸው አስፈፃሚዎች በተጠቀሱት ምርጫ ጣቢያ የማይሠሩ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ተችሏል” ሲል ገልጿል።
ቦርዱ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ላይ በምርጫ አስፈፃሚነት ተቀጥረው ለመሥራት ፍላጎት ላላቸው ሁሉ አግባብነት ያላቸውን መሥፈርቶች ሁሉ በማሳወቅ በይፋ ጥሪ በማድረግ አስፈፃሚዎችን መመልመሉን ገልጿል። ከዚያም ገለልተኝነታቸው ላይ በፓርቲዎች ጥያቄ የቀረበባቸውን በመተካት ሥራውን እንደቀጠለ አስረድቷል።
ቦርዱ አስቀድሞ ለፓርቲዎች የምርጫ አስፈፃሚዎችን ዝርዝር ልኮ ገለልተኝነታቸውን አስተያየት እንዲሰጡበት ማድረጉን የገለጸ ሲሆን፣ አሁንም ቢሆን ፓርቲዎች አስተያየት እንዲሰጡባቸው ተደርጎ ገለልተኝነታቸው ላይ ጥያቄ ካልተነሳባቸው እና ወደ ሥራ እንዲገቡ ከተደረጉት ውስጥ የገለልተኝነት ጥያቄ በፓርቲዎች ከተነሣ ቦርዱ እንደሚያስተናግድ አስታውቋል።
ከጎጎት በተጨማሪ፣ በእዣ ወረዳ ቅሬታ በተመደቡ የምርጫ አስፈፃሚዎች ቅሬታ እንዳላቸው የገለጹት የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ዕጩ ሆነው በጉራጌ ዞን እዣ ወረዳ የቀረቡት እና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባሉ ዶ/ር አብርሃም በርታ ናቸው። ዶ/ር አብርሃም፣ “በእዣ ወረዳ የምርጫ አስፈፃሚዎቹ ገለልተኛ አይደሉም፤ የብልፅግና ፓርቲ አባል የነበሩ እንዲሁም የፓርቲ መዋጮ ሲከፍሉ የነበሩ በኃላፊነት የሰሩ ሰዎች ናቸው” በማለት ወቅሰዋል።
ዶ/ር አብርሃም፣ በእዣ ወረዳ ቅስቀሳ ለማድረግ በተገኙበት ወቅት፣ ከፍተኛ የሆነ “አፈና እና እንግልት” መኖሩን ገልጸው፣ “በወረዳው የመንግሥት ጠርናፊዎች ወይንም ካድሬዎች ታርጋ በሌላቸው ሞተሮችን በመጠቀም በሰላም እንዳንቀሳቀስ እንቅፋት ሆነውብናል” ሲሉ ሁኔታውን ገልጸዋል።
በጉራጌ ዞን እዣ ወረዳ በ2013 ዓ.ም በነበረው ሀገራዊ ምርጫ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ማሸነፉ የሚታወቅ ሲሆን፣ “ይህ ሁኔታ በዘንድሮ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ እንዳይደገም ጫናው በርትቷል” ሲሉ የምክር ቤት አባሉ ተናግረዋል።
ጉዳዩን ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለማሳወቅ በሂደት ላይ መሆናቸው ገልጸው፣ “የቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊው የብልፅግና ፓርቲ አባል የነበረ በመሆኑ ቅሬታችንን ለመቀበል ፍቃደኛ አይደለም” ብለዋል።
“ብልፅግናን ካልመረጣችሁ ማዳበሪያ አታገኙም፤ ከዚህ ምርጫ በኋላ የትኛውም ተቃዋሚ ፓርቲ መጥቶ አያድናችሁም በሚል ከፍተኛ ጫና ሕዝቡ ላይ እያደረጉበት ይገኛል” ሲሉ ገልጸዋል።
በብልፅግና ፓርቲ ላይ የቀረበውን ቅሬታ በተመለከተ የጉራጌ ዞን ብልፅግና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ናስር ሐሰንን “ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የጠየቀች ሲሆን “ጋዜጠኛ መሆናቸሁን የሚያረጋግጥ መታወቂያ ላኩልኝ” ካሉ በኋላ ምላሽ ለመስጠት ፍቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።
አቶ ናስር በእዣ ወረዳ የብልፅግና ፓርቲ ዕጩ ሆነው በዛው አካባቢ የሚወዳደሩ መሆናቸው “ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ማረጋገጥ ችላለች።
ጎጎት ፓርቲ እያደረገ ያለውን ዝግጅት በተመለከተ በምርጫው ለመሳተፍ ከመወሰናቸው በፊት በሀገሪቱ ለምርጫ “አስቻይ” ሁኔታ የለም የሚል ድምዳሜ ላይ መድረሳቸውን ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል።
“አንዳንድ ቦታዎች ላይ የሚታይ ግጭት ሌሎች ቦታዎች ደግሞ ግጭት ባይኖርም ከፍተኛ ስጋቶች ይታያሉ” ያሉት ፕሬዝዳንቱ መንግሥትንም ሆነ ምርጫ ቦርድን ቅድሚያ ለሰላም እንዲሰጡ” ጠይቀው እንደነበር ገልጸው፣ ዕጩዎች ከተመዘገቡ በኋላም ራሳቸውን ከምርጫው ለማግለል እስከመድረስ መገደዳቸውን ተናግረዋል።
ፓርቲው የምርጫ ቅስቀሳውን በሚያከናውንበት ወቅት በርካታ ተግዳሮቶች እያጋጠሙት መሆኑን የገለጹት አቶ መሐመድ፣ ከችግሮቹ መካከልም አዳራሾችን መከለከል፣ አባላትን ማስፈራራት የሚሉትን ዘርዝረዋል።
ከዚህ ቀደም ምርጫ ለማሸነፍ ገዢው ፓርቲ “ኮሮጆ ነበር የሚገለብጠው። አሁን ግን ቀድሞ ነው ምርጫውን ለማጭበርበር የሚሠራው። እኔ ባላሸንፍ እንኳን ‘እኔ ያስቀመጥኳቸው ያሸንፉ’ በሚል አንዳንድ ቦታዎችን ለሚያምናቸው ሰዎች እስከመተው እየደረሰ ነው” ሲሉ ድርጊቱን ኮንነዋል።
ፓርቲው 82 ዕጩዎችን ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ያቀረበ ሲሆን፣ 21ዱ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት (ፓርላማ)፣ ቀሪው ደግሞ ለክልል ምክር ቤት ማቀረቡን አሳውቋል። ዕጩዎቹም የሚወዳደሩት በማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ አዲስ አበባ፣ ሲዳማ እና ደቡብ ኢትዮጵያ መሆኑን ገልጿል።
በአንፃራዊነት ሰላም ባላባቸው ቦታዎች ላይ ለመወዳደር ሞክረናል ያሉት አቶ መሐመድ “በፓርቲው ቀደም ያሉ ግምገማዎች የፀጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች ለዕጩዎች ደኅንነት” በሚል አለመወዳደራቸውን ገልጸው፣ “አንዳንድ ቦታዎች ላይ ደግሞ በፓርቲው አባላት በሚመጣ ስጋት” አለመወዳደራቸውን ተናግረዋል።
ጎጎት ፓርቲ ለመጀመሪያ ጊዜ ተሳታፊ በሆነበት በዚህ የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ “የፓርቲውን ሕዝባዊነት ማስጠበቅ” ቀዳሚው ተግባር መሆኑን ፕሬዝዳንቱ አስረድተዋል። ፓርቲው በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ እንደ ግብ ያስቀመጠው የፓርቲውን ተደራሽነት በማስፋት፣ በሚወዳደርባቸው ቦታዎች ላይ ደግሞ ወንበሮችን ማሸነፍ እንደሆነም ተናግረዋል።
ፓርቲያቸው “ተራማጅ ሊበራል” እንደሆነ የገለጹት አቶ መሐመድ አብራር “ኢትዮጵያ ውስጥ ሁለት መሠረታዊ” ነገሮች “የብዙዎቹ ችግሮች መፈልፈያ ናቸው” ብለዋል። እነዚህም፣ “የፖለቲካ አፈና እና ድህነትና ኋላቀርነት ናቸው” በማለት ፓርቲው ይህንን ለመቅረፍ እንደሚሠራ ተናግረዋል። [ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር]




