የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የ7ኛው ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ የድምፅ መስጫ ወረቀቶች መታተማቸውን ተከትሎ፣ ከምርጫው ራሳቸውን በገዛ ፈቃዳቸው የሚያገሉ ዕጩዎችን ጥያቄ በሕግ አግባብ እንደማይቀበል አስታወቀ። ቦርዱ ይህንን ያስታወቀው የትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት እና የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ዕጩ ለነበሩት ለአቶ ይስሃቅ ወልዳይ በደብዳቤ በሰጠው ይፋዊ ምላሽ ነው።
ምርጫ ቦርድ ግንቦት 11 ቀን 2018 ዓ.ም. ለዕጩው ለአቶ ይስሃቅ ወልዳይ በጻፈው እና በቦርዱ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ ተፈርሞ በወጣው ደብዳቤ፤ ዕጩው ግንቦት 10 ቀን 2018 ዓ.ም. ለቦርዱ በጻፉት ደብዳቤ ራሳቸውን ከዕጩነት ማግለላቸውን ማሳወቃቸውን ጠቅሷል።
ይሁን እንጂ ቦርዱ በሕጉ አግባብ መሠረት በወጣው የጊዜ ሰሌዳ፣ አንድ ዕጩ ከዕጩነት ሊለቅ ወይም ጥያቄው ሊስተናገድ የሚችለው እስከ ሚያዝያ 23 ቀን 2018 ዓ.ም. ድረስ በነበረው የጊዜ ገደብ ውስጥ ብቻ እንደነበር ገለጿል። አክሎም ቦርዱ “የድምፅ መስጫ ወረቀት አሳትሞ ወደ ሀገር ውስጥ አስገብቶ ለምርጫው 12 ቀን ሲቀረው የቀረበ ጥያቄ የሕግ መሠረት የሌለው በመሆኑ ቦርዱ ጥያቄውን ያልተቀበለው መሆኑን ያስታውቃል” ሲል በይፋ ውሳኔውን አሳውቋል።
በዚህም መሠረት፣ አቶ ይስሃቅ በአራዳ ክፍለ ከተማ የምርጫ ክልል 1/9 ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በትብብሩ ስም ተመዝግበው የነበረ ቢሆንም፣ በገዛ ፈቃዳቸው የመልቀቅ ጥያቄያቸው በቦርዱ ተቀባይነት ባለማግኘቱ ስማቸው እና ምስላቸው በድምፅ መስጫ ወረቀቱ ላይ ተካቶ ለሕዝብ ምርጫ እንደሚቀርብ ታውቋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት እና በኢሕአፓ በኩል በዕጩነት የቀረቡት ሌላኛው አቶ ኤፍሬም ካሳም ከምርጫው ራሳቸውን ማግለላቸውን “ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ከጻፉት ደብዳቤ ለመረዳት ችላለች። በሲዳማ ክልል በሀዋሳ የኢሕአፓ ሥራ አስፈጻሚ እና የትብብሩ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑት አቶ ኤፍሬም ካሳ፣ ትናንት ግንቦት 11 ቀን 2018 ዓ.ም. ለሲዳማ ክልል ምርጫ ቦርድ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት በጻፉት ደብዳቤ ከዕጩነት ራሳቸውን ማግለላቸውን አስታውቀዋል።
አቶ ኤፍሬም ለውሳኔያቸው የጠቀሱት ምክንያት ጥምረቱ ከዚህ ቀደም ካነሳቸው ስጋቶች ጋር ቀጥተኛ ተያያዥነት ያለው ነው። አቶ ኤፍሬም በደብዳቤያቸው ላይ “ፓርቲያችን ኢሕአፓም ሆነ ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት ምርጫው ታማኝና ፍትሐዊ እንዲሆን ከምርጫ አስቻይ ሁኔታዎች በተመለከተ ያስቀመጧቸው ቅድመ ሁኔታዎች ባለመሟላታቸው፣ ከዛሬ ጀምሮ ከጠቅላላው የምርጫ ሂደትም ሆነ ከዕጩነቴ ራሴን ያገለልኩ መሆኑን በአክብሮት አሳውቃለሁ” ሲሉ በጽሑፍ አስፍረዋል።
ይሁን እንጂ፣ የአቶ ኤፍሬም ካሳም የመልቀቂያ ጥያቄ ከሕጋዊው የጊዜ ገደብ (ከሚያዝያ 23) በኋላ የቀረበ መሆኑን ለመረዳት ተችሏል።
የትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት ከፍተኛ አመራሮች ትናንት በሰጡት መግለጫ “የምርጫውን ሂደት እስከ መጨረሻው እያጠናን እንቀጥላለን” ማለታቸው የሚታወስ ሲሆን፣ ከታች ባሉ የምርጫ ክልሎች ያሉ ዕጩዎች ግን በግላቸው የሚወስዱት እርምጃ የፓርቲው ወይም የትብብሩ ሳይሆን፣ የግላቸው መሆኑ ተገልጿል። [ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር]




