7ኛው ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ ዛሬ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም. ከጠዋቱ 12፡00 ሰዓት ጀምሮ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በይፋ መካሄድ የጀመረ ሲሆን፣ መራጮች ከማለዳው 11፡30 ጀምሮ በምርጫ ጣቢያዎች ተገኝተው ረጅም ሰልፎችን በመያዝ ቦታቸውን መያዛቸው ተስተውሏል። በአዲስ አበባ ከተማ፣ በባሕር ዳር እና በሐረር ከተሞች የሚገኙ መንገዶች ከወትሮው በተለየ መልኩ ረጭ ያሉ ሲሆን፣ በተለይም በባሕር ዳር ከተማ ከመንግሥት ተሽከርካሪዎች ውጪ ምንም ዓይነት የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት እንደሌለና በሐረርም እስከ ረፋድ ድረስ የእንቅስቃሴ መገታት መኖሩ ተግንዝቧል። በሐረር ከተማ የባጃጅ እንቅስቃሴም መከልከሉን የከተማው ፖሊስ አሳውቋል።
በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ ክፍለ ከተሞች ድምፅ የመስጠት ሂደቱ ማለዳ ላይ የተጀመረ ቢሆንም፣ በአንዳንድ ጣቢያዎች ላይ ግን የቅድመ ዝግጅት መዘግየቶች ታይተዋል። ለምሳሌ በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 ቤቶች ኮርፖሬሽን ምርጫ ጣቢያ ድምፅ መስጠት የተጀመረው በቅድመ ዝግጅት መዘግየት ምክንያት ከጠዋቱ 12፡25 ላይ ነበር። በተመሳሳይ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ “ሰላም ግሮሰሪ” ምርጫ ጣቢያ እና በወረዳ 15 “ኦሮሚያ ኮንዶሚኒየም” ምርጫ ጣቢያዎች ከፍተኛ ቁጥር ያለው መራጭ የተሰለፈ ቢሆንም፣ የድምፅ አሰጣጥ ሂደቱ እጅግ በዝግታ እየተከናወነ መሆኑ ተስተውሏል። በአንጻሩ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 “ሸማች ሱፐርማርኬት” ጎን በሚገኘው ምርጫ ጣቢያ ከጠዋቱ 12፡23 የተገኘው ዘጋቢያችን መራጮች ያለምንም እንግልት ድምፅ መስጠት መጀመራቸው ተመልኳል።
በምርጫ ጣቢያዎቹ የተገኘው የታዛቢዎች ውክልና አብዛኛው በገዢው ብልፅግና ፓርቲ እና በአገር ውስጥ ሲቪክ ማኅበራት የተወሰነ መሆኑ ታዝቧል። በለሚ ኩራ (ቤቶች ኮርፖሬሽን) እና በንፋስ ስልክ ላፍቶ (ቢላል መስጂድ) ምርጫ ጣቢያዎች ከብልፅግና ፓርቲ ውጪ የሌሎች ፖለቲካ ፓርቲዎች ታዛቢዎች ያልተገኙ ሲሆን፣ በአንጻሩ የአዲስ አበባ ወጣቶች ማኅበር እና የሴቶች ማኅበር ታዛቢዎች በቦታው ተገኝተዋል።
በላፍቶ ወረዳ 12 ቢላል መስጂድ አጠገብ ያለ የምርጫ ጣቢያ አንዲት መራጭ የምርጫ ካርድ ቢኖራትም ስሟ በዲጂታል መዝገብ ላይ አልተገኘም። ሆኖም የምርጫ አስፈጻሚዎች በምዝገባ ወቅት የመራጮች ሦስት ቀናት ሲስተም ጠፍቶ ስለነበር የ40 ያህል መራጮች ስም መሰረዙን ገልጸውላታል። ሆኖም በኋላ ላይ በስልክ በተላከላት መለያ ቁጥር መሠረት እንድትመርጥ መደረጉን የ“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢ ተመልክታለች።
የአፍሪካ ኅብረት የምርጫ ታዛቢዎች ቡድን መሪ የቀድሞው የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ በማለዳው በአዲስ አበባ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ በሚገኘው ፒተር ፓን ትምህርት ቤት እና በፒኮክ መናፈሻ ምርጫ ጣቢያዎች ተገኝተው ሂደቱን ታዝበዋል። ኡሁሩ ኬንያታ ከምልከታዎቻቸው በኋላ በሰጧቸው አጫጭር መግለጫዎች፣ ምርጫው በሰዓቱ በጥሩ ዝግጅት መጀመሩን ጠቅሰው፣ በፒኮክ ጣቢያ ግን የተወሰነ መዘግየት ቢኖርም አጠቃላይ ሂደቱ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የአገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት እና ታዋቂ ፖለቲክኞችም በማለዳው ድምፅ መስጠታቸውን ዘጋቢዎቻችን ተመልክተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በኦሮሚያ ክልል ጅማ ዞን በሻሻ ከተማ (ጎማ 2 የምርጫ ክልል) ተገኝተው መርጠዋል። ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ በአራዳ ክፍለ ከተማ ወጣት ማዕከል 1/9 ጣቢያ፣ እንዲሁም ከንቲባ አዳነች አቤቤ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ፣ ጄነራል ጃጋማ ኬሎ ጤና ጣቢያ ምርጫ ጣቢያ ድምፅ ሰጥተዋል።
በባሕር ዳር ከተማ፣ “ህዳሴ” የምርጫ ጣቢያ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ እና የኢትዮጵያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ከጠዋቱ 2፡00 ሰዓት ገደማ መምረጣቸውን ዘጋቢያችን ተመልክቷል። በተመሳሳይ የኢዜማ መሪ አቶ ኢዮብ መሳፍንት፣ በአዲስ አበባ ከተማ፣ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ፣ ምርጫ ክልል 18፣ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የምርጫ ጣቢያ ከጠዋቱ 3፡00 ተገኝተው መምረጣቸውን ዘጋቢያችን ተመልክቷል።
በክልል ከተሞች በሐረር (ቀበሌ 10 ደን ልማት ጣቢያ) ከጠዋቱ 12፡08 ላይ ድምፅ መስጠት የተጀመረ ሲሆን፣ የምርጫ መዝገቡና ወረቀቶቹ በታዛቢዎች ፊት ከእሽግ ሲፈቱ ዘጋቢያችን ተመልክቷል። በሁሉም የኢትዮጵያ ኢንሳይደር ዘጋቢዎች በደረሱባቸው የምርጫ ጣቢያዎች፣ ማለዳ ላይ ድምፅ ለመስጠት በስፋት የተገኙት አዛውንቶች እና አብዛኞቹ ሴቶች መሆናቸውን ለመታዘብ ተችሏል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የዘገባ ፈቃድ ባጅ እና የኢትዮጵያ ኢንሳይደርን መታወቂያ የያዘው የ“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢ፣ በአንድ የምርጫ አስፈፃሚ ፎቶ እንዳያነሳ ተከለከለ። ዘጋቢያችን ዛሬ ጠዋት 4፡00 ሰዓት ገደማ፣ የምርጫ ክልል 12/13፣ ወረዳ 6፣ የኢትዮጵያ ዓይነ ስውራን ጽ/ቤት ጊቢ የሚገኘው የምርጫ ጣቢያ ተገኝቶ ሥራውን እያከናወነ ሳለ፣ በምርጫ አስፈፃሚው “ፎቶ ማንሳት አይቻልም፤ አንሱ ከተባለ የፈቀድልህን አካል ጠይቅ” የሚል ክልከላ ደርሶበታል።
በሐረር ከተማ የነፃነትና እከልነት ፓርቲ (ነእፓ) ተንቀሳቃሽ ታዛቢ የሆኑት አቶ አምራች ታደሰ በዛሬው ዕለት 4:00 ሰዓት ገደማ ታስረው እንደተፈቱ የፓርቲው ሰብሳቢ ዶክተር ከሪሙዲን ሙባረክ ለ”ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገለጹ። የፓርቲው ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊው እንደገለፁት የመረጥናቸውን ታዛቢዎች በቦታቸው ሰዓት አክብረው ቢገኙም መታዘብ እንዳይችሉ ከመደረጋቸው ባሻገር በ06 ቀበሌ አዴ መሐመድ ቤት ምርጫ ጣቢያ በፖሊስ እና በወረዳ አመራሮች ታዛቢያቸው ለእስር እንደተዳረገ ገልፀዋል፡፡
“የታሰረብን ታዛቢ ከእስር ቢለቀቅም እንግልቱ አሁንም አልቆመም” የሚሉት ኃላፊው “ፍትሐዊ የምርጫ ውድድር ሳናደርግ የምንጠብቀው ውጤት የለንም፣ የምርጫ አስፈፃሚው በገለልተኝነት ለሁሉም ፓርቲዎች ሊሰሩ ይገባል” ብለዋል። (ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)




