በጸጥታ ችግር ምክንያት 143 የምርጫ ጣቢያዎች በዛሬው ዕለት አለመከፈታቸውን ምርጫ ቦርድ አሳወቀ

በጸጥታ ችግር ምክንያት 143 የምርጫ ጣቢያዎች በዛሬው ዕለት አለመከፈታቸውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ። በኦሮሚያ እና በአማራ ክልል “በተወሰኑ ቦታዎች” የድምጽ መስጠት ሂደቱ ከተጀመረ በኋላ የተቋረጠባቸው የምርጫ ጣቢያዎች እንዳሉም ቦርዱ ገልጿል።

ቦርዱ ይህን ያስታወቀው ዛሬ ሰኞ ግንቦት 24፤ 2018 ከጠዋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ እየተካሄደ ያለውን ሰባተኛ ጠቅላላ ምርጫ በተመለከተ በሰጠው መግለጫ ነው። መግለጫውን በአዲስ አበባው ስካይ ላይት ሆቴል የሰጡት የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ ናቸው።

ሜላትወርቅ በዚሁ መግለጫቸው፤ የዛሬውን የድምጽ መስጠት ሂደት ለማካሄድ 50,188 ምርጫ ጣቢያዎች በሰዓቱ ተከፍተዋል። ከ12 ሰዓት ከ30 እስከ ጠዋት አንድ ሰዓት ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ የተከፈቱ የምርጫ ጣቢያዎች ብዛት 695 መሆናቸውን ዋና ሰብሳቢዋ አመልክተዋል።

ድምጽ መስጠት ከተጀመረ በኋላ ባጋጠመ “የጸጥታ ችግር” ፤ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልል የተወሰኑ ቦታዎች የምርጫ ሂደቱ መቋረጡንም ሜላትወርቅ ተናግረዋል። ምርጫ ከተቋረጠባቸው ውስጥ ቢሎኖፓ፣ መኮሳቺ፣ ቀርሳ እና ኩታበር የተባሉ የምርጫ ጣቢያዎች እንደሚገኙበትም አክለዋል።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሰዳል ምርጫ ክልል እንዲሁም በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ዘልማም ምርጫ ክልል ባጋጠመ “የኔትወርክ ችግር” ምክንያት ቦርዱ በስልክ መረጃ ማግኘት አለመቻሉም በመግለጫው ላይ ተጠቅሷል። ሜላትወርቅ በዚሁ መግለጫቸው በአንድ የምርጫ አስፈጻሚ ላይ የደረሰን አደጋም በሀዘን አጋርተዋል።

አደጋው የደረሰበት የምርጫ አስፈጻሚ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል፣ በእነሞር እና ኤነር አንድ የምርጫ ክልል የተመደበ እንደነበረም ዋና ሰብሳቢዋ ገልጸዋል። ስሙ ያልተጠቀሰው የሎጀስቲክ ክፍል ሰራተኛ የሆነ የቦርዱ ተቀጣሪ፤ “በጠዋት ተነስቶ የክትትል ስራ ለመስራት በሞተር ሳይክል ሲሄድ በደረሰበት አደጋ ህይወቱ ማለፉን” ሜላትወርቅ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

የሞተር ሳይክል አደጋውን “በጣም የሚያሳዝን” እና “ለቦርዱ ትልቅ ሀዘን” ሲሉ ዋና ሰብሳቢዋ ገልጸውታል። “የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በዚህ በጣም ከፍተኛ ሀዘን ተሰምቶናል” ብለዋል። (ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)