በነገው ዕለት ለሚካሄደው ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በአዲስ አበባ ከተማ የተደረገውን ዝግጅትን ለመቃኘት፣ የ“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢዎች ዛሬ እሁድ በቦሌ፣ አራዳ፣ ልደታ፣ ቂርቆስ፣ የካ እና ንፋስ ስልክ ክፍለ ከተሞች የመስክ ቅኝት አድርገዋል። ዘጋቢዎቻችን በተመለከቷቸው ሁሉም የምርጫ ጣቢያዎች፣ ከፌደራል ፖሊስ፣ ከአዲስ አበባ ፖሊስ እና ከደንብ ማስከበር የተውጣጡ የጸጥታ ኃይሎች ለጥበቃ መሰማራታቸውን ታዝበዋል።
ዛሬ ከሰዓት በብዙዎቹ የምርጫ ጣቢያዎች የምርጫ አስፈጻሚዎች በስፍራው ላይ አልነበሩም። ብዙዎቹ የምርጫ አስፈጻሚዎች ዝግጅታቸውን አስቀድመው አጠናቅቀው ወደ ቤታቸው መሄዳቸውን ዘጋቢዎቻችን ተገንዝበዋል። በአንድ የምርጫ ጣቢያ የነበሩ ኃላፊ የምርጫ ቁሳቁሶችን ለመረከብ ወደ ክፍለ ከተማ እንደሄዱ ለዘጋቢያችን ተነግሯታል።
ይህ የምርጫ ጣቢያ የሚገኘው በልደታ ክፍለ ከተማ የፍሬህይወት ቅድመ አንደኛ፣ መጀመሪያ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው። ዘጋቢያችን በዚህ የምርጫ ጣቢያ በተገኘችበት ከቀኑ ስምንት ሰዓት ተኩል አካባቢ ከትምህርት ቤቱ ቅጥር ግቢ ራቅ ብሎ ጥበቃ ከሚያደርጉ የተወሰኑ ፖሊሶች ውጭ የጎላ እንቅስቃሴ አልነበረም።
ዘጋቢያችን በስፍራው በነበራት ቆይታ አንድ የብልጽግና ፓርቲ ታዛቢ፣ አንድ የምርጫ አስፈጻሚ እና የአካባቢው ነዋሪ ወደ ጣቢያው ሲመጡ ተመልክታለች። የገዢው ፓርቲ ታዛቢ እና የአካባቢው ነዋሪ በትምህርት ቤቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ የተተከለውን የድምጽ መስጫ ድንኳን እየተዟዟሩ ከተመለከቱ በኋላ የመብራት አምፖል ሲያስተካክሉ ታይተዋል።
በልደታ ክፍለ ከተማ በሚገኘው ሊዛ ትምህርት ቤት ቅጽር ግቢ ውስጥ በተቋቋመው የምርጫ ጣቢያ የነበረው ድባብም ተመሳሳይ ነበር። በዚህ የምርጫ ጣቢያ፣ የምርጫ አስፈጻሚዎችም ሆነ የምርጫ ታዛቢዎች አልነበሩም። በዚሁ ክፍለ ከተማ በሚገኙ ሌሎች ሁለት ምርጫ ጣቢያዎች በአንጻሩ የምርጫ አስፈጻሚዎች ቁሳቁሶችን አደራጅተው ማጠናቀቃቸውን ታዝባለች።

እነዚህ የምርጫ ጣቢያዎች፣ በክፍለ ከተማው ወረዳ 7 የወጣት ስብዕና መገንቢያ ማዕከል እና የወጣት ማዕከል ውስጥ የሚገኙ ናቸው። በጥቂት እርምጃ ልዩነት ተራርቀው የሚገኙትን እነዚህን የምርጫ ጣቢያዎች አመሻሽ አስራ አንድ ሰዓት ገደማ የጎበኘችው ዘጋቢያችን፣ ሁለት የብልጽግና ፓርቲ ታዛቢዎች መሆናቸውን የገለጹ ግለሰቦችን አግኝታለች።
እነዚህ የገዢው ፓርቲው ታዛቢዎች ዘጋቢያችን ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተሰጣትን የዘገባ ፍቃድ (ባጅ) እና የስራ መታወቂያዋን ቢመለከቱም፤ ወደ ጣቢያው የምትገባው “ከበላይ አቅጣጫ ሲሰጣቸው” መሆኑን በመግለጽ ለደቂቃዎች እንድትጠብቅ አድርገውታል። ዘጋቢያችን ከቆይታ በኋላ ወደ ምርጫ ጣቢያ መግባት እንደምትችል የተነገራት ቢሆንም፣ ዝግጅቱን በምስል ለማስቀረት ግን በድጋሚ ክልከላ አጋጥሟታል።
በወጣት ስብዕና መገንቢያ ማዕከል የነበሩ የምርጫ ጣቢያ አስፈጻሚዎች፤ ፎቶግራፍ ለማንሳት እና ቪዲዮ ለመቅረጽ “ልዩ ፈቃድ ያስፈልጋል” የሚል ማሳሰቢያ ለዘጋቢያችን ሰጥተዋታል። ሆኖም ዘጋቢያችን ባቀረበችው ጥያቄ መሰረት የምርጫ ጣቢያ አስፈጻሚዎቹ በስልክ ማብራሪያ ከጠየቁ በኋላ ፎቶ እንድታነሳ ፈቅደውላታል።
በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 በሚገኘው የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ልማት ማኅበር ጽሕፈት ቤት ቅጽር ግቢ ውስጥ የተቋቋመውን የምርጫ ጣቢያ የተመለከቱት ዘጋቢያዎቻችንም ተመሳሳይ ተግዳሮት አጋጥሟቸዋል። በዚህ የምርጫ ጣቢያ የነበሩ የጸጥታ ኃይሎች፣ የዘጋቢዎቻችንን የምርጫ ቦርድ ሕጋዊ የዘገባ ፍቃድ (ባጅ) እና መታወቂያ ተቀብለው ፎቶ አንስተዋቸዋል።
በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ምርጫ ክልል 21/22 የሚገኘው “13 ዳቦ ቤት” ተብሎ በሚጠራው ምርጫ ጣቢያ የተመደቡ የፖሊስ አባል፣ የዘጋቢያችንን የምርጫ ቦርድ ባጅ ቢመለከቱም በስፍራው ሆኖ መዝገብም ሆነ ፎቶም ማንሳትም ከልክለዋታል። የፖሊስ አባሉ ይህን ክልከላ ያደረጉት ወደ ሌሎች የፖሊስ አባላት ስልክ ደውለው ከተነጋገሩ በኋላ ነው።
በተመሳሳይ፣ በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ በወረዳ አራት የሚገኘውን ምርጫ ጣቢያ ዛሬ ከሰዓት የጎበኘው ዘጋቢያችን፣ የምርጫ አስፈጻሚዎች የምርጫ ቁሳቁሶችን ከቆለፉ በኋላ ለጠባቂ ፖሊሶች አስረክበው ወደ ቤታቸው መሄዳቸውን በስፍራው ያሉ ፖሊሶች ለዘጋቢያችን ነግረውታል። ሆኖም፣ ምንም እንኳን ዘጋቢያችን ከምርጫ ቦርድ የተሰጠውን የዘገባ ፈቃድ (ባጅ) የያዘ መሆኑን ቢያሳያቸውም፣ ፖሊሶቹ የምርጫ ዝግጅቱን የሚያሳይ ፎቶ እንዳያነሳ ዘጋቢያችንን ከልክለውታል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዛሬ፣ እሁድ ምሽት ባወጣው ማሳሰቢያ ጋዜጠኞችን “ከዘገባ ሥራቸው ማስቆም በውስን አካባቢ መስተዋሉን” አረጋግጧል። ይህ አካሄድ “የተሳሳተ” እንደሆነ የገለጸው ቦርዱ፣ ሚዲያዎች በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን “የተመዘገቡ መሆናቸው ብቻ” ምርጫ ለመዘገብ እንደሚያስችላቸው አስታውቋል። “በምርጫ ጣቢያ 200 ሜትር ንፍቀ ክበብ ውስጥ መዘገብ የሚችለው ከቦርዱ የዕውቅና ባጅ ያለውና የሚሠራበት የመገናኛ ብዙኃን ተቋም መታወቂያ የያዘ ብቻ ነው” ሲል ቦርዱ “ለሚመለከተው ሁሉ” ባስተላለፈው ማሳሰቢያ ላይ አስገንዝቧል።
በቦሌ ክፍለ ከተማ፣ ወረዳ 3፣ ከቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ኤርፖርት ፊት ለፊት እና በሞኤንኮ ጀርባ በሚገኙ የድምጽ መስጫ ጣቢያዎች የተገኙ ዘጋቢዎቻችን በበኩላቸው፤ የድምጽ መስጫ ድንኳኖች ተጥለው፣ ወንበር እና ጠረጴዛዎች ተሰናድተው እንዲሁም የምርጫ ቁሳቁሶች ተሟልተው በስፍራው መድረሳቸውን ታዝበዋል። በአራዳ ክፍለ ከተማ፣ ወረዳ 9፣ ሜትሮፖሊታን ኮሌጅ አካባቢ እንዲሁም በየካ ክፍለ ከተማ፣ ወረዳ 6፣ አምስት ኪሎ አጸደ ሕፃናት ትምህርት ቤት የሚገኙ ምርጫ ጣቢያዎችም ተመሳሳይ ዝግጅት ማድረጋቸውንም ተመልክተዋል። በየካ ክፍለ ከተማ ምሥራቅ ፖሊ ቴክኒክ 1 እና 2 ምርጫ ጣቢያዎች ለነገው ድምጽ መስጪያ የሚሆኑ ድንኳኖች የተተከሉ ቢሆንም፣ ከአንድ ወር በፊት የተጠናቀቀውን “የመራጮች ምዝገባ” የሚያሳይ ባነር አለመነሳቱም ተስተውሏል። (ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)




