(ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር) ነገ፣ ግንቦት 24፣ 2018 በሚካሄደው 7ኛው ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ፣ ለፓርላማ ምርጫ የሚካሄድባቸው የፓርላማ ወንበሮች 501 መሆናቸው ታውቋል፤ ይህም የሆነው የትግራይ 38 እና የአማራ 8 ወንበሮች ምርጫ ስለማይካሄድባቸው ነው። ብልፅግና ፓርቲ ለፓርላማ ያቀረባቸው ዕጩዎች ብዛት 461 ነው፤ ሆኖም፣ በአማራ ክልል ምርጫ አይካሄድባቸውም የተባሉት 8 የምርጫ ክልሎች ከመታወቃቸው በፊት የተመዘገበ የዕጩዎች ቁጥር ስለሆነ ከምርጫው ጋር አብረው የተሰረዙ ዕጩዎች መኖራቸውን ለጊዜው ማረጋገጥ አልተቻለም።
ይሁን እንጂ የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ በአማራ ክልል ምርጫ ከማይካሄድባቸው አካባቢዎች መካከል ደቡብ እና ምዕራብ ጎንደር፣ አምባሰል እና ደጋ ዳሞት እንደሚገኙበት ተናግረዋል።
በዚህ መሠረት ሲሰላ፣ ከ40 እስከ 48 የሚሆኑ የፓርላማ ወንበሮች በተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ወይም በግል ተወዳደሪዎች ሊወሰዱ እንደሚችሉ ይገመታል። በሌላ በኩል 75 ዕጩዎች ያለተፎካካሪ እንደሚወዳደሩ ሲታወቅ፣ ከነዚህ ውስጥ 65ቱ የብልፅግና ተወዳዳሪዎች ናቸው። ከቀሪዎቹ 10 ዕጩዎች መከካከል ሁለት የግል ተወዳዳሪዎች እና ስምንት የተቃዋሚ ፓርቲ ወኪሎች ከወዲሁ ያለተፎካካሪ ወደ ፓርላማ እንደሚገቡ ተገምቶ ነበር። ሆኖም ደጋ ዳሞት የምርጫ ክልል ውስጥ ነገ ምርጫ እንደማይካሄድ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ስለተገለጸ፣ የትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት ዕጩ የሆኑት በአማራ ክልል ደጋ ዳሞት የምርጫ ክልል የቀረቡት ይልቃል አስቻለ፣ ብቻቸውን ተወዳድረው ፓርላማ የመግባት ዕድላቸው ተስተጓጉሏል።
እነዚህ በምርጫ ክልላቸው ሌላ ተወዳዳሪ ዕጩ ባለመኖሩ፣ በእነዚህ አካባቢዎች ምርጫው ካልተደናቀፈ በቀር በመጪው ፓርላማ ያለተቀናቃኝ የሚገቡት 9 ዕጩዎች የሚከተሉት ናቸው፤
- ቀጄላ መርዳሳ፣ በኦሮሚያ መንዲ የምርጫ ክልል፣ የግል ዕጩ
- አራርሶ ቢቂላ፣ በኦሮሚያ ደደር 2 የምርጫ ክልል፣ የግል ዕጩ
- ሰለሞን ታፈሰ፣ በኦሮሚያ ኮፈሌ 2 የምርጫ ክልል፣ የአዲስ ትውልድ ፓርቲ ዕጩ
- ዮሐንስ ጥላሁን፣ በአማራ ክልል አማኑኤል የምርጫ ክልል፣ የትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት ዕጩ
- ዳምጠው ተሰማ፣ በአማራ ክልል መሐል ሜዳ የምርጫ ክልል፣ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ዕጩ
- ሙሐመድ ቡሽራ፣ በአማራ ክልል ሳይንት 2 የምርጫ ክልል፣ የነፃነት እና እኩልነት ፓርቲ ዕጩ
- እንደግ አዳነ፣ በአማራ ክልል ግንደ ወይን የምርጫ ክልል፣ የኢዜማ ዕጩ
- መኮንን ጎለሣ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ካማሺ የምርጫ ክልል፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የጉሙዝ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ዕጩ
- ዘካሪያስ አንበሴ፣ በደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ዳሰነች የምርጫ ክልል፣ የኢዜማ ዕጩ




