የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በትላንትናው ዕለት የተካሄደው ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ፣ “ሰላማዊ”፣ “አሳታፊ”፣ “ዲሞክራሲያዊ” እና “አካታች” እንደነበር ገለጸ። ኮሚሽኑ ምርጫው “መሰረታዊ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ያልተፈጸመበት” እና “የተለመዱ ዓለም አቀፍ የምርጫ መስፈርቶችን ባሟላ” ሁኔታ የተካሄደ መሆኑንም አረጋግጬያለሁ ብሏል።
ኢሰመኮ ይህን የገለጸው፤ በምርጫው ዕለት ያደረገውን ክትትል የተመለከተ የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት ዛሬ ማክሰኞ ግንቦት 25፤ 2018 ይፋ ሲያደርግ ነው። ሪፖርቱን ለመገናኛ ብዙሃን ያቀረቡት የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር አቶ ብርሃኑ አዴሎ ናቸው።
እርሳቸው የሚመሩት መንግስታዊ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን፤ የትላንቱን ምርጫ ከታዘቡ ተቋማት አንዱ ነው። ኮሚሽኑ በኢፌዲሪ ህገ መንግስት እና በተቋቋመበት አዋጅ፤ በኢትዮጵያ የሚካሄዱ ሀገራዊ እና አካባቢያዊ ምርጫዎች “በሰብአዊ መብቶችን መርሆዎች መሰረት መከናወናቸውን የመከታተል” ስልጣን ተሰጥቶታል።

ተቋሙ በሚያደርጋቸው ክትትሎች፤ ምርጫዎቹ “ዓለም አቀፍ መስፈርቶችን ማሟላታቸውን” የማረጋገጥ ኃላፊነትም ተጥሎበታል። በዚህም መሰረት ኢሰመኮ ከ320 በላይ አባላት የያዙ፣ 104 የክትትል ቡድኖችን በምርጫው ዕለት ማሰማራቱን አስታውቋል።
እነዚህ ታዛቢዎች ከ180 በላይ በሆኑ የምርጫ ክልሎች ስር ባሉ ሶስት ሺህ ገደማ የምርጫ ጣቢያዎች ላይ ተሰማርተው የክትትል ስራቸውን ማከናወናቸውን እንደነበር አቶ ብርሃኑ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። ኮሚሽኑ ከዚህ በተጨማሪ የተቋሙ ከፍተኛ አመራሮችን በያዘ “ልዩ የክትትል ቡድን” አዋቅሮ ምርጫውን መታዘቡን ገልጸዋል።
“የክትትል ስራው በመስክ ከተሰማራው በተጨማሪ በዋና እና ምክትል ኮሚሽነሮች፣ በአራት የዘርፍ ኮሚሽነሮች የተዋቀረ ልዩ የክትትል ቡድን በማቋቋም፣ በሁኔታዎች መከታተያ ክፍል (situation room) እና በምስክ ምልከታ ስራውን በአግባቡ መርቷል” ሲሉ አቶ ብርሃኑ በዛሬው መግለጫቸው አመልክተዋል።

“ልዩ የክትትል ቡድኑ” በአማራ ክልል ባህር ዳር እና ጎንደር ከተሞች፣ በኦሮሚያ ክልል ጅማ እና ጎማ አጋሮ ከተሞች እንዲሁም በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በአርባ ምንጭ ዙሪያ ተገኝቶ ምርጫውን መከታተሉን ዋና ኮሚሽነሩ አስታውቀዋል። ኮሚሽኑ ምርጫውን የተመለከቱ 104 አቤቱታዎች እንደቀረቡለት የገለጹት አቶ ብርሃኑ፤ ከእነዚህ ውስጥ 93ቱ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጋር በነበረ የጋራ መረጃ ልውውጥ አማካኝነት “መፍትሔ እንዳገኙ” ገልጸዋል።
ዋና ኮሚሽነሩ “እልባት አግኝተዋል” ካሏቸው ችግሮች መካከል፤ የታዛቢዎች ስምሪት፣ የባጅ አሰጣጥ እና ከኦንላይን ምዝገባ ጋር በተያያዘ የተፈጠሩ ረጃጅም ሰልፎችን የተመለከቱ ይገኙበታል። ኮሚሽኑ ከቀረቡለት አቤቱታዎች ውስጥ አራቱ “በሂደት ላይ” መሆናቸውን እና ሰባቱ ደግሞ “ተጨማሪ መረጃ የሚሹ” እንደሆኑም አቶ ብርሃኑ አክለዋል።
አቶ ብርሃኑ በምርጫው ሂደት “መለስተኛ ግድፈቶች” መስተዋላቸውን በመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርታቸው ቢገልጹም፤ በዝርዝር ከመግለጽ ተቆጥበዋል። “በአጠቃላይ አልፎ አልፎ የተከሰቱ ችግሮችን በማጠቃላይ ሪፖርታችን የሚጠቀሱ መሆናቸው እንደተጠበቀ ሆኖ፤ በሂደቱ የተስተዋሉ መለስተኛ ግድፈቶችን ማረም ተችሏል” ብለዋል ዋና ኮሚሽነሩ በመግለጫቸው።

ኢሰመኮ በምርጫው ዕለት ባካሄደው ክትትል፤ ምርጫው “ሰላማዊ”፣ “አሳታፊ”፣ “ዴሞክራሲያዊ” እና አካታች” ሆኖ እንዳገኘውም አቶ ብርሃኑ ገልጸዋል። ምርጫው “መሰረታዊ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ያልተፈጸመበት” እንደሆነ ኢሰመኮ ማረጋገጡንም ዋና ኮሚሽነሩ አስታውቀዋል።
በትላትናው ዕለት የተካሄደው ምርጫ “የተለመዱ ዓለም አቀፍ የምርጫ መስፈርቶችን ያሟላ” እንደሆነ ተቋማቸው ማረጋገጡንም አቶ ብርሃኑ በዛሬው ጋዜጣዊ መግለጫቸው ላይ ይፋ አድርገዋል። ዋና ኮሚሽነሩ መግለጫቸውን ያጠቃለሉት ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ውጭ ያለ “ማንኛውም አካል”፤ “ያልተረጋገጠ ወይም በትንቢያ ላይ የተመሰረተ ውጤት” ከመግለጽ እንዲቆጠብ በማሳሰብ ነው። (ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)




