የገዢው ፓርቲ ብልጽግና ፕሬዝዳንት እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ይህን ያሉት በኦሮሚያ ክልል ጅማ ዞን በሻሻ ተገኝተው ድምጽ ከሰጡ በኋላ ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ ላይ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ጊዜ እንዳሉት “የጸጥታ ችግር እንዲፈታ ፓርቲዬ ቢመረጥም ባይመረጥም የሚሰራበት ጉዳይ ይሆናል” ሲሉ ተናግረዋል። ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የሁለም አካላት ጥረት ያስፈልጋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፉት ዓመታት የተሰደዱት እንዲመለሱ፣ የታሰሩትን በመፍታት ብዙ ተሰርቷል፤ ይሁንና ይቅርታውን እንደ ፍራቻ፣ ችግሮቻችንን ተሰብስበን እንፍታ ስንል እንደ ፍራቻ መውሰድ አለ። ሰላም በመንግሥት ፍላጎት ብቻ የሚመጣ ተደርጎ መወሰድ እንደሌለበትም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
“ምርጫው እንዲስተጓጎል ብዙ ተሰርቷል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ባለፉት ዓመታት በመቶዎች የሚቆጠሩ ቦንቦችን በየከተማው ስንለቅም ኖረናል” ሲሉም አክለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ “የዘንድሮ ምርጫ በዚህ በታሰበው መልክ ሰላማዊ ሆኖ እንዳይሄድ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች የሚገዟቸውን ኃይሎች ገዝተው በስፋት አሰማርተዋል፣ ፕሮፓጋንዳ ሰርተዋል። ኢትዮጵያ ውስጥ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ማድረግ አይቻልም የሚል እምነት እንድንይዝ ሙከራ መደረጉንም ተናግረዋል።
“ይህ አምስት ዓመት በኢትዮጵያ በርካታ የታሪክ እጥፋት የሚታይበት አምስት ዓመት ይሆናል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ “ቢያንስ የማትለምን፣ ራሷን ችላ የምትቆም፤ በከባቢው አንከር የሆነች ሀገር ለመሆን ብዙ ስራ ይጠይቃል” ብለዋል።
ባለፉት አምስት አመታት ኢትዮጵያ ውስጥ “ይቻላል” የሚለው የታየበት ካልሆነ በስተቀር “ለውጥ ያመጣንበት ጊዜ አልነበረም” ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ከትግራይ ክልል ውጪ በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች በመካሄድ ላይ ሲሆን ዜጎች በየምርጫ ጣቢያዎች ተገኝተው ድምጽ በመስጠት ላይ ናቸው። ልክ እንደ ጠቅላይ ሚኒሰትሩ የፌደራል እና ክልል ባለ ስልጣናት በጠዋት ድምጽ ሲሰጡ አርፍደዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በባህር ዳር፣ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀስላሴ እና ከንቲባ አዳነች አቤቤ አዲስ አበባ የሚገኙ ምርጫ ጣቢያዎች ተገኝተው ድምጽ ሰጥተዋል። (ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)




