የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለሰባተኛ ጊዜ የሚካሄደውን ሀገር አቀፍ ምርጫ፤ በመጪው ግንቦት 24፤ 2018 ለማድረግ ምክረ ሃሳብ አቀረበ። ቦርዱ በምርጫው የሚገኘውን ውጤት ይፋ ለማድረግ፤ በረቂቅ የጊዜ ሰሌዳው ያስቀመጠው ዕለት ሰኔ 3፤ 2018 ነው።
ብሔራዊው ምርጫ ቦርድ የጠቅላላ ምርጫውን ረቂቅ የጊዜ ሰሌዳ አዘጋጅቶ ለውይይት ያቀረበው፤ ከትላንት በስቲያ ሰኞ ጥቅምት 10፤ 2018 ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ባደረገው ምክክር ላይ ነበር። በአዲስ አበባው ስካይ ላይት ሆቴል በተካሄደው በዚህ ውይይት ላይ ከ60 በላይ በህጋዊ መንገድ የተመዘገቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች መሳተፋቸውን፤ በመድረኩ የታደሙ ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
መገናኛ ብዙሃን ባልተገኙበት በዚህ የውይይት መድረክ ላይ፤ ምርጫ ቦርድ የሰባተኛውን ሀገር አቀፍ ምርጫ ዝርዝር የጊዜ ሰሌዳ አቅርቧል። “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተመለከተችው የጊዜ ሰሌዳ፤ 37 ተግባራት የሚከናወኑባቸውን ጊዜያት በቀን እና በወራት ከፋፍሎ አስቀምጧል።

ምርጫ ቦርድ ለዘንድሮ ምርጫ የሚሆን ዝግጅት ማድረግ የጀመረው ካለፈው ዓመት የካቲት ወር ጀምሮ እንደሆነ በጊዜ ሰሌዳው ላይ ተቀምጧል። ቦርዱ በየካቲት 2017 ዓ.ም. የጀመረውን የምርጫ ጽህፈት ቤቶችን የማደራጀት ተግባር ለማጠናቀቅ ያቀደው፤ ከሁለት ወራት በኋላ በታህሳስ 15፤ 2018 እንደሆነ በጊዜ ሰሌዳው ላይ ሰፍሯል።
ባለፈው ዓመት የተጠናቀቀው ሌላው ከምርጫ ጋር የተያያዘ ክንውን፤ የመራጮች ትምህርት የሚሰጡ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምዝገባ ነው። በነሐሴ ወር መግቢያ የተጀመረው ይህ ተግባር በዚያው ወር መጨረሻ ላይ መገባደዱን በጊዜ ሰሌዳው ላይ ተመልክቷል።
በነሐሴ ወር አጋማሽ የተጀመረው የምርጫ ታዛቢ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምዝገባም፤ ባለፈው መስከረም ወር አጋማሽ እንደተጠናቀቀ ቦርዱ በጊዜ ሰሌዳው ላይ አስታውቋል። ምርጫ ቦርድ በተያዘው ጥቅምት ወር ስምንት ተግባራትን ለማከናወን ማቀዱ በረቂቅ የጊዜ ሰሌዳው ላይ ተዘርዝሯል።

ቦርዱ በረቂቅ የምርጫ ጊዜ ሰሌዳው ላይ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ያደረገው ውይይት እና በቀጣይነት ከሲቪል ማህብረሰብ ድርጅቶች ጋር የሚያደርገው ምክክር ለዚህ ወር ከተያዙ ክንውኖች ይጠቀሳሉ። የመራጮች ትምህርት ለሚሰጡ የሲቪል ማህብረሰብ ድርጅቶች ዕውቅና ለመስጠት ቦርዱ ያቀደውም በዚሁ በጥቅምት ወር ነው።
በጥቅምት ወር አጋማሽ እንዲጀመር የታሰበው የምርጫ አስፈጻሚዎች ምልመላ እስከ ጥር 7፤ 2018 ባለው ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ መታቀዱም እንዲሁ በጊዜ ሰሌዳው ላይ ተመልክቷል። የፖለቲካ ፓርቲዎች “ሲስተም” በመጠቀም የዕጩዎች ምዝገባ የሚያከናውኑላቸውን ባለሙያዎች ለቦርዱ እንዲያሳውቁ ጥሪ የሚደረግላቸው በተያዘው ወር መሆኑን የቦርዱ የጊዜ ሰሌዳ ያሳያል።
ለመራጮች ምዝገባ የሚያስፈልገው የመራጮች ትምህርት፤ በጥቅምት ወር ተጀምሮ ለአምስት ወራት እንደሚቆይም በረቂቅ የጊዜ ሰሌዳው ላይ ተቀምጧል። ለምርጫ ታዛቢ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ዕውቅና መስጠት እና በቴክኖሎጂ ምዝገባ የሚከናወንባቸው (self-registration) የምርጫ ጣቢያዎች ዝርዝር ለህዝብ ይፋ ማድረግም ጊዜ የተያዘላቸው በዚሁ ወር መገባዳጃ ላይ ነው።

በቴክኖሎጂ የታገዘ (self registration) የመራጮች ምዝገባ ደግሞ በቀጣዩ ህዳር ወር አጋማሽ ተጀምሮ እስከ የካቲት መጨረሻ ድረስ የሚቆይ መሆኑ በጊዜ ሰሌዳው ላይ ሰፍሯል። መደበኛው የመራጮች ምዝገባ እንዲካሄድ የታሰበው ከየካቲት መጀመሪያ እስከ መጋቢት መጀመሪያ ባለው ጊዜ ውስጥ ነው።
በረቂቅ የጊዜ ሰሌዳው፤ ከህዳር መጀመሪያ እስከ ወሩ አጋማሽ ድረስ በምርጫ ለሚወዳደሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የግል ዕጩዎች የምዝገባ ጥሪ ለማድረግ ታቅዷል። የምርጫ አስፈጻሚዎችን ዝርዝር ለፖለቲካ ፓርቲዎች እና ለህዝብ ይፋ ማድረግ፤ ህዳር 19 ተጀምሮ በጥር የመጀመሪያ ሳምንት ላይ ለማጠናቀቅ ታስቧል። ይህ መርሃ ግብር በሁለት ዙር የሚከናወን መሆኑ በረቂቅ የጊዜ ሰሌዳው ላይ ተመልክቷል።
በምርጫ የሚሳተፉ ዕጩዎች ምዝገባ እንዲከናወን የታቀደው ከታህሳስ መጀመሪያ እስከ ጥር መጀመሪያ ባለው ጊዜ ውስጥ ነው። የምረጡኝ ቅስቀሳ ወይም የምርጫ ዘመቻ ከታህሳስ 10 እስከ ግንቦት 19 ድረስ እንዲከናወን ያቀደው ምርጫ ቦርድ፤ ከግንቦት 20 እስከ 23 ያሉትን ቀናት ለጥሞና ጊዜ መድቧል። በእነዚህ ሶስት ቀናት ቅስቀሳ ማድረግ አይቻልም።

የድምጽ መስጫ ቀን አሊያም ምርጫ የሚከናወንበት ቀን እንዲሆን የታቀደው፤ ግንቦት 24፤ 2018 ነው። በዚሁ ዕለት እና በማግስቱ፤ የምርጫ ውጤት በምርጫ ጣቢያ ይፋ ለማድረግ ታቅዷል። በምርጫ ክልል ደረጃ ጊዜያዊ ውጤት ይፋ እንዲደረግ የታሰበው ደግሞ፤ ከግንቦት 25 ጀምሮ ባሉት አምስት ተከታታይ ቀናት ነው።
ከግንቦት 26 እስከ ሰኔ 1 ያሉት ቀናት ደግሞ በምርጫ ክልል የተሰበሰቡ ውጤቶች ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የማስረከቢያ ጊዜ እንዲሆን ተመድበዋል። የምርጫ ውጤቱን በምርጫ ቦርድ ደረጃ የማረጋገጥ ስራ ይከናወናል ተብሎ የሚጠበቀው ከግንቦት 27 እስከ ሰኔ 2 ድረስ ባለው አንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ነው።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ ይፋዊ ውጤት መግለጫ እንዲሰጥ ቀነ ቀጠሮ የተያዘለት ለሰኔ 3፤ 2018 ነው። ይፋዊ ውጤቱ እስከሚገለጽበት ዋዜማ ድረስ ያሉት ዘጠኝ ተከታታይ ቀናት፤ ቅሬታ የማቅረቢያ ጊዜ እንደሚሆኑ በረቂቅ የጊዜ ሰሌዳው ላይ ተመልክቷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)




