የቁጫ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቁሕዴፓ) አባላት እና ዕጩዎች በአልባሳቸው ምክንያት ለምርጫ ቅስቀሳ ወደ ወረዳው እንዳይገቡ ተከለከሉ

የቁጫ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቁሕዴፓ) ሚያዚያ 10 ቀን 2018 የምርጫ ቅስቀሳ ለማድረግ ወደ ጋሞ ዞን፣ ቁጫ ወረዳ የተጓዘ ቢሆንም በፀጥታ ኃይሎች ወደ ምርጫ ክልሉ እንዳይገባ መከልከሉን የፓርቲው ፕሬዚዳንት እና የኢትዮጵያ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት (ፓርላማ) አባሉ ፕሮፌሰር ገነነ ገደቡ ተናግረዋል። የፓርቲው ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ እና አባላቱ በሦስት መኪናዎች ከወላይታ ሶዶ በመነሳት ወደ ቁጫ የምርጫ ክልል ማምራታቸውን የገለጹት ፕሬዝዳንቱ፣ “ዳና በሚባለው አካባቢ ላይ በርካታ የፀጥታ አካላት መንገድ ላይ አስቁመውን የፓርቲውን አርማ እና ምልክቶች ይዛችሁ መግባት አትችሉም በሚል ወደ ምርጫ ክልሉ እንዳንገባ ተደርገናል” ሲሉ ገልጸዋል።

ፕሬዚዳንቱ አክለውም፣ “ጥቃቶች እና ክልከላዎች በዚሁ የሚቀጥሉ ከሆነ” ከ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ራሱን ሊያገል እንደሚችል ለ“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። የቁጫ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳንኤል ደሳለኝ በበኩላቸው የፓርቲው አባላት ወደ ምርጫ ክልሉ ሲመጡ “የቁጫ ብሔር በሚል በሕገ መንግሥቱ ዕውቅና የሌለው አልባሳት ለብሰው የተገኙ በመሆኑ፣ ቁጫ የሚባል ብሔር የለም በማለት ልብሱን አስተካክሉ ቢባሉም ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ተመልሰዋል” ብለዋል። ይሁን እንጂ “ፓርቲው ቅስቀሳ እንዳያደርግም ሆነ ማኒፌስቶውን እንዳያስተዋውቅ አልተከለከለም” ያሉት አቶ ዳንኤል፣ ፓርቲው “በተደጋጋሚ ለጻፈው ደብዳቤ ምላሽ በመስጠት ወደ ወረዳው በመምጣት ቅስቀሳ ማድረግ እንደሚችሉ ስንገልጽ ቆይተናል” የሚል ምላሽ ለ“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ሰጥተዋል።

በተጨማሪም ኃላፊው አክለውም “ግጭት ቀስቃሽ አርማ ከመልበሳቸው ባለፈ” ማንኛውም ወደ ምርጫ ክልል ለቅስቀሳ መግባት የሚፈልግ ፓርቲ “በጽሑፍ ምርጫ ክልሉ ላለበት የመንግሥት አካል ማሳወቅ እንዳለበት በግልፅ ቢታወቅም፣ ፓርቲው ይህንን አላደረገም” ብለዋል። የፓርቲው ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ገነነ ገደቡ ግን “በሕገ መንግሥቱም ሆነ በየትኛውም የሀገሪቱ ሕግ ያልተከለከልነውን ነገር መከልከል አይገባም የሚል ጥያቄ ለፀጥታ አካላቱ ብናስረዳም፣ አርማችሁን ካላወለቃችሁ ወደ ምርጫ ክልሉ መግባት አትችሉም በመባሉ ወደ አዲስ አበባ ተመልሰናል” ብለዋል።

“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” በፓርቲው ይፋዊ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጽ እና በአባላቱ፣ የቅስቀሳው ዕለት የተለቀቁ አልባሳትን የመረመረች ሲሆን፣ ሰማያዊ፣ ነጭ እና ቢጫ ቀለም ያላቸው በሽመና የተሰሩ ስካርፎችን እና የፓርቲው ሥምና አርማ፣ እንዲሁም “ቁሕዴፓን ይምረጡ” የሚል የምርጫ ምልክት የታተመባቸው ነጭ ቲ-ሸርቶችን ከመልበሳቸው እና የፓርቲውን የምርጫ ማኒፌስቶ ከመያዛቸው በቀር ሌሎች መልዕክቶች የተጻፈባቸው አልባሳቶች መኖራቸውን ማረጋገጥ አልቻለችም።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለፌደራል ፖሊስ ሚያዚያ 9 ቀን 2018 ዓ.ም በጻፈው ደብዳቤ፣ የቁሕዴፓ ስብሰባ ሚያዚያ 10 ቀን 2018 ዓ.ም በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ ጋሞ ዞን፣ ሰላም በር ከተማ እንደሚደረግ ጠቅሶ፣ ፌዴራል ፖሊስ ለአዳራሽ ስብሰባው ጥበቃ እንዲያደርግ ጠይቋል። ይህ ደብዳቤ በቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ንዋይ ሚያዚያ 9 ቀን 2018 የተጻፈ ቢሆንም፣ የፌዴራል ፀጥታ ኃይሎች ወደ ክልል ገብተው ሊሰማሩ የሚችሉት በክልሉ መንግሥት ግብዣ ወይም ጥሪ ብቻ ነው የሚሉ ቅሬታዎች ሲደመጡ ነበር።

ፓርቲው ወደ ዞኑ እንዳይገባ ክልከላ የተደረገበት በክልሉ የፀጥታ አካላት እንደሆነ ፕሬዚዳንቱ “ለምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ፕሮፌሰር ገነነ አክለውም፣ ቦርዱ ደብዳቤውን ለፌዴራል ፖሊስ መጻፉ ትክክል መሆኑን ገልጸው፣ “ከፌደራል ፖሊስ ያነጋገረን አካል [ግን] የለም” ብለዋል። “ብሔራዊ ምርጫ ቦርድንም ጠይቀን፣ ሥራችሁን ሥሩ የሚል ምላሽ ከቦርዱ ተሰጥቶናል” በማለት አብራርተዋል። ፕሮፌሰር ገነነ ለክልሉ የፀጥታ አካላት “በቀጥታ ምንም ዓይነት ጥያቄ አለማቅረባቸውን” ገልጸው፣ የምርጫ ቅስቀሳ የሚደረግለትን የፀጥታ አካላት ጥበቃ በተመለከተ አሠራሩ፣ “በቀጥታ ለፀጥታ አካላት ጠይቁ የሚል ሳይሆን”፣ በምርጫ ቦርድ በኩል “ማሳወቅ በቂ ነው” ሲሉ ተከራክረዋል።

ፕሮፌሰር ገነነ፣ ክልከላውን ቦርዱ እንዲያወቀው የማድረግ ሥራ እንደሚሰሩ የገለጹ ሲሆን፣ በቀጣይ የተፈጠረውን ችግር በተመለከተ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሪፖርት እንደሚያሳወቁ ተናግረዋል።

በ6ኛው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ ተመሳሳይ ተሳትፎ ያደረገው የቁጫ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቁሕዴፓ)፣ በቁጫ የምርጫ ክልል አንድ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት (ፓርላማ) እና ሦስት የክልሉ ምክር ቤት መቀመጫዎችን ማሸነፉ ይታወሳል። [ ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር]