“የበጀት እጥረት” ያቀዛቀዘው የሐረር ከተማ የምርጫ ድባብ

በሐረር ከተማ የመስክ ቅኝት ለማድረግ የተንቀሳቀሰው የ“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢ፣ በከተማዋ የምርጫው ድባብ ካለፉት ምርጫዎች አንፃር መቀዛቀዙን አስተውሏል።

ይህንን አስመልክቶ ጥያቄ ያቀረበላቸው ነፃነት እና እኩልነት ፓርቲ (ነእፓ)፣ ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ፓርቲ (ኢብአፓ) ፓርቲዎች የበጀት እጥረትን እንደ ዋነኛ ምክንያት ጠቅሰውለታል። ዘጋቢያችን የፖለቲካ ፓርቲዎች በተለይ ከኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ የሚለቀቀው የፋይናንስ ድጋፍ ላይ ጥገኛ መሆናቸውን ያስተዋለ ሲሆን፣ ከበጀት እጥረት በተጨማሪም በከተማው እየተንቀሳቀሱ የምርጫ ቅስቀሳ ለማድረግ ተሽከርካሪ ማግኘት እንደተቸገሩ ከፓርቲዎቹ ለመረዳት ችሏል።

በዚህም ምክንያት ለ7ኛው ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ የሚሳተፉ ፓርቲዎች፣ ከገዢው ብልፅግና ፓርቲ በስተቀር የአደባባይ የምርጫ ቅስቀሳ እያደረጉ አይደለም።

ከብልፅግና ፓርቲ ውጪ ባለፈው ሳምንት ዕጩዎቹ የተሰረዙበት የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራሲ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) ሚያዚያ 17፣ 2018 ዓ.ም በሐረር ከተማ ባደረገው ቅስቀሳ በሐረሪ ክልል እስካሁን የአደባባይ ቅስቀሳ ያደረገ ብቸኛው የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ ሆኗል። ሌሎቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች የአደባባይ ቅስቀሳዎችን፣ ሰላማዊ የድጋፍ ሰልፎችን፣ የአዳራሽ ስብሰባዎችን፣ የከተማ ቅስቀሳዎችን ካለማድረጋቸውም ባሻገር፣ በራሪ ወረቀቶች ሲበትኑ አለመመልከቱን የ“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢ ገልጿል።

ለመሆኑ ‘በሐረሪ ክልል የምርጫ ቅስቀሳው ለምን ተቀዛቀዘ?’ ስትል “ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎችን የጠየቀች ሲሆን፣ በዋነኝነት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለፓርቲዎች የሚያከፋፍለውን የፋይናንስ ድጋፍ ሙሉ በሙሉ ባለመልቀቁ፣ የየፓርቲዎቹ “የቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ቅስቀሳ ማድረግ አልቻልንም” ሲሉ ገልጸዋል።

ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት 30% የሚሆነው የፋይናንስ ድጋፍ ብቻ እንደተለቀቀለት ገልጾ፣ ቀሪው 70 በመቶ ባለመለቀቁ እስካሁን በሐረሪ ክልል ቅስቀሳ ማድረግ እንዳልቻለ አሳውቋል። ኢብአፓም በተመሳሳይ የተለቀቀው የፋይናንስ ድጋፍ ትንሽ በመሆኑ ለክልል ቅርንጫፎች መድረስ አልቻለም ብሏል።

የኢብአፓ ሐረር ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሰብሳቢ የሆኑት ወይዘሮ ሐሰነት ሙሜ አጠቃላይ የምርጫውን ሂደት በተመለከተ በሰጡን ማብራሪያ “ዕጩዎቻችንን ማስተዋወቅ፣ ሊመርጠን ከሚችለው ማኅበረሰብ ጋር ተገኝተን የፓርቲያችንን ዓላማ ማስተዋወቅና አዳዲስ አባላትን ማፍራት የሚጠበቅብን ሰዓት ቢሆንም፣ [የፋይናንስ ድጋፍ] ስላልተለቀቀልን ቤት ለቤት ሄዶ ከማስተዋወቅ ውጪ አንድም እንቅስቃሴ እያደረግን አይደለም” ብለዋል።

ቦርዱ ሚያዚያ 15 ቀን 2018 ዓ.ም በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫው፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቅስቀሳ ለማድረግ የፋይናንስ ድጋፍ እንዳልተለቀቀላቸው መጥቀሳቸውን ተከትሎ፣ ‘እንዲህ ያለ ጥያቄ ቀርቦልኝ አያውቅም’ የሚል ምላሽ መስጠቱን መዘገባችን ይታወሳል።

በመግለጫው የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች በመደበኛ ጊዜ የሚሰጣቸው ገንዘብ እና በምርጫ ወቅት የሚሰጣቸው የፋይናንስ ድጋፍ የተለያየ መሆኑን ገልጸው፣ “የመጀመሪያ ዙር 30 በመቶውን ከፍለናል። የሚቀረውን በተለያየ ክፍፍል የሚሰጠውን ለመስጠት የመረጃ ክፍተት ገጥሞናል” ብለዋል።

የቦርዱ ሰብሳቢ የአካል ጉዳተኛ ዕጩዎች ቁጥር መረጃ በደንብ አጥርተው ያቀረቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ባለመኖራቸው በጀቱን ማከፋፈል እንዳስቸገረ የገለጹ ሲሆን፣ የፋይናንስ ድጋፍ መስጠት መጀመራቸውን ግን “36 ለሚሆኑት ፓርቲዎች ከፍለናል፤ ለቀሪዎቹም የምንከፍል ይሆናል” በማለት አስረድተዋል።

ሰብሳቢዋ ለ32 የፖለቲካ ፓርቲዎች በንግድ ባንክ በኩል 81 ሚሊዮን ብር ገደማ የፋይናንስ ድጋፍ መሰራጨቱን ገልጸው፣ ለቀሪዎቹ “በሌላ ባንክ የሚከፈል በመሆኑ እየተከታተልን መክፈላችንን እንቀጥላለን” ብለዋል። ሆኖም ፓርቲዎቹ የሴት ዕጩዎቻቸውን ቁጥር በትክክል ያሳወቁ ቢሆንም፣ የአካል ጉዳተኛ ዕጩዎቻቸውን “ማስረጃ ማቅረብ ባለመቻላቸው እና ይህንን ከፓርቲዎች በሰነድ ማረጋገጥ ባለመቻሉ ክፍያው ዘግይቷል” ብለዋል።

በሌላ በኩል የኢብአፓ ሐረር ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሰብሳቢ “በገዢው ፓርቲ የሚደረጉ ቅስቀሳዎች በመንግሥት መኪና፣ በመንግሥት ሥርዓት የተጠቀሙ የባለሀብት መኪኖች እንደሆኑ የምንመለከተው ሐቅ ነው” ያሉ ሲሆን፤ “በዚህም ገዢው ፓርቲ ቅስቀሳ ለማድረግ ቀሎታል። እኛ ግን ያለብንን የበጀት ችግር ተጋፍጠን እንኳን በከተማ ቅስቀሳ ለማድረግ መኪና የሚያከራየን የለም” በማለት አስረድተዋል።

በተጨማሪም “ከዚህ በፊት ምርጫ ሲደረግ የተለያዩ የምርጫ ክርክሮች፣ ማኒፌስቷችንን ማስተዋወቅ በሚዲያዎች ላይ ይደረጉ ነበር። አሁን ግን ሚዲያው አየር ሰዓቱን ከመፍቀድ ውጪ ማኒፌስቷችንን በግል ወጪ [ወደ] ‘ኦዲዮ ቪዥዋል’ አሠርተን እንድናመጣ አቅጣጫ በመቀመጡ ምክንያት ከአንድ ቀን የቴሌቪዥን ክርክር ውጪ እስካሁን ዋና የመንግሥት ሚዲያዎችን መጠቀም አልቻልንም” ብለዋል።

የትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት ፓርቲ ሐረር ቅርንጫፍ ሰብሳቢ አቶ ኢዮኤል አበበ በበኩላቸው “በክልሎች ከብልፅግና ቀጥሎ ብዙ ዕጩዎችን ማስመዝገብ ብንችልም፣ ሊመርጠን የሚችለው ማኅበረሰብ ጋር ከማኅበራዊ ሚዲያ ውጪ መገናኘት አልቻልንም” ብለዋል።

የ7ኛው ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ የካቲት 28፣ 2018 ጀምሮ እስከ ሚያዝያ 14 ድረስ የተካሄደ ሲሆን፣ ከ50 ሚሊዮን በላይ መራጮችን መዝግቦ ማጠናቀቁ የሚታወስ ነው።

በ7ኛው ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ ላይ ለመሳተፍም በሐረሪ ክልል ከ12 በላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደሚወዳደሩ ታውቋል። ግንቦት 24 ለሚደረገው ምርጫ፣ ለሐረሪ ክልል በአዲስ አበባ፣ በድሬ ዳዋ እና በሐረሪ ክልል በሚገኙ 16,573 የምርጫ ጣቢያዎች ላይ የመራጮች ምዝገባ በአብዛኛው በዲጂታል ሥርዓት የተካሄደ ሲሆን፣ በነዚሁ ጣቢያዎች ድምፅ የመስጠቱ ሂደት በአካል እንደሚከናወን ምርጫ ቦርድ ቀደም ሲል ማሳወቁ ይታወሳል።

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የጊዜ ሰሌዳ መሠረት የፖለቲካ ፓርቲዎች የቅስቀሳ ጊዜ ሊጠናቀቅ የቀሩት ሁለት ዐሥርት ቀናት ብቻ ናቸው። [ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር]