በባሕርዳር ከተማ የሚገኙ ነዋሪዎች “በግዳጅ” ለድጋፍ ሰልፍ ውጡ መባላቸው ተገቢ እንዳልሆነ ተናገሩ

ግንቦት 18 ቀን 2018 በባሕር ዳር ከተማ መንግሥት “የድጋፍ ሰልፍ” ሲል የጠራው ትዕይንት በታላቁ ስታድየም የተካሄደ ሲሆን፣ ቤት ለቤት በተደረገ ቅስቀሳ በአስገዳጅ መልኩ ለሰልፍ ውጡ መባላቸውን “ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው ነዋሪዎች ገልጸዋል።

ገዢው ፓርቲ ብልፅግና “የድጋፍ ሰልፍ” ሲል የጠራውን ትዕይንት ለማከናወን ቅድመ ዝግጅት ሲያደርግ መቆየቱን የጠቀሱት ነዋሪዎቹ “የክፍለ ከተማ ደንብ ጽ/ቤት ኃላፊዎች ነን እያሉ ቤት ለቤት በማንኳኳት ስማቸውንና ስልካቸውን ሲመዘግቡ ነበር” ብለዋል።

ለደኅንነታቸው ሲባል ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁን የባሕር ዳር ከተማ ቀበሌ 13 ነዋሪ የሆኑት ግለሰብ “ከሰልፉ ዋዜማ ጀምሮ የፖሊስ አባላትን ጨምሮ ቁጥራቸው አምስት የሚደርሱ ሰዎች ቤቴን ሲያንኳኩ ከፈትኩላቸው፤ ከዛም ነገ ሰልፍ ስላለ መቅረት አይቻልም። የምትቀሪ ከሆነ ግን ቅጣት አለው አሉኝ” ሲሉ ገልጸዋል።

ሰልፉ ላይ የተገኘ እና ያልተገኘ ሰው ስም ይያዛል በሚል ምክንያት የግል ስልካቸውን መዝግበው እንደሄዱም አክለው ገልጸዋል።

በተመሳሳይ ሌላኛው የቀበሌ 08 ነዋሪ የሆኑ አባወራ “ለምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” በሰጡት መረጃ ሰልፉ በሚካሄድበት ዕለት ከጠዋቱ 12፡00 ጀምሮ የቀበሌ ሰዎችና የፖሊስ አካላት በየቤቱ እየዞሩ በሩን በኃይል እየደበደቡ “ለሰልፍ ወጡ” የሚል ጥሪ ያደርጉ አንደነበር አስረድተዋል።

የእርሳቸው በር ሲደበደብ ሰምተው ለመክፈት ከወጡ በኋላ ከቀበሌ አመራሮችና ከደንብ አስከባሪዎች ጋር በነበራቸው ምልልስ አለመግባባት መፈጠሩን አክለው ገልጸዋል።

“በፍቃደኝነት የሚወጣውን ሰው ይዛችሁ ሰልፉን ማድረጋችሁ መልካም ነው፤ ነገር ግን እኔ ሥራ ስላለኝ መሄድ አልችልም ስላቸው፣ አንተማ ፅንፈኛ ነህ ማለት ነው ብለው ማንገራገር ጀመሩ” ያሉት ነዋሪው “የደንብ ጽ/ቤት ኃላፊ ነኝ የሚል ግለሰብ ገፍትሮ ሊያስወጣኝ ሲሞክር ፖሊሶቹ ተሽለው ገላገሉኝ” በማለት አስረድተዋል።

“የበላይ አመራራሮች ይህን የሚየውቁ አይመስለኝም” ያሉ የቀበሌ 14 ነዋሪ በበኩላቸው፣ የክፍለ ከተማና የቀበሌ ሰዎች በየጊዜው እያደረጉ ባሉት ነገር እንደተማረሩ ገልጸዋል። “በምርጫ ምዝገባው ወቅት የእኔንም የቤት ተከራዮችንም ስም መዝግበው ኑ የምርጫ ካርድ ውሰዱ” እያሉ ይደውሉ እንደነበር ገልጸው፣ “ሰፈር ለሰፈር እየዞሩ ጡሩንባ ሁሉ እየነፉ ሰልፉ ላይ ያልተገኘ ቅጣት አለው የሚል ጥሪ ሲያደርጉ ከቆዩ በኋላ ጥቂት ቆይተው ደግሞ በመዘገቡት ስልካችን በቀጥታ እየደወሉ ማስፈራራት ጀመሩ” በማለት አብራርተዋል።

በጥዋት ተነስተው ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲጓዙ የነበሩ ጎረቤቶቻቸውን አስመልሰው ወደ ሰልፉ እንዲሄዱ ሲያስገድዱ በአይናቸው እንደተመለከቱ እኚሁ የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ “ለምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል።

የድጋፍ ሰልፍም ሆነ ሌሎች ሕዝባዊ ተሳትፎ የሚጠይቁ መንግሥታዊ ትዕይንቶች ሲኖሩ ፈቃድን መሠረት ያደረገ ከመሆን አልፈው ቤት ለቤት የሚደረጉ የግዳጅ ቅስቀሳዎች ተገቢ አለመሆናቸውን ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።

“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጉዳዩን በተመለከተ ሐሳባቸውን እንዲሰጡ ወደተጠቀሱት ክፍለከተማ ኃላፊዎች ተደጋጋሚ የስልክ ጥሪ ብታደርግም ምላሽ ማግኘት አልቻለችም።

ትላንት፣ ግንቦት 18፣ 2018 በባሕር ዳር እና ሌሎችም ከተሞች ብልፅግና ፓርቲ የምርጫ 2018 ቅስቀሳ መዝጊያ ሰልፎችን ማካሄዱ ይታወቃል። [ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር]