የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን 4 ሺሕ ገደማ ተሳታፊዎችን ከሚያወያይባቸው ንዑስ አጀንዳዎች መካከል፣ በአጀንዳ ቁጥር ሁለት ስር “የፖለቲካ ውክልና እና የምርጫ ሥርዓት ጉዳዮች” ዋነኛው ነው። አሁን ኢትዮጵያ የምትከተለው የምርጫ ሥርዓት የአብላጫ ድምፅ (First-Past-the-Post – FPTP) የሚባለው ሲሆን፣ እንደ አማራጭ ደግሞ የተመጣጣኝ ውክልና (Proportional Representation – PR) ለምክክሩ ቀርቧል። የምክክሩ ዋነኛ የውይይት ጥያቄም “የትኛው ሥርዓት የተለያዩ የፖለቲካ አመለካከቶች እና የኅብረተሰብ ክፍሎች ፍትሐዊ ውክልና እንዲኖራቸው ያስችላል?” የሚል ነው።
“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ይህንን ጥያቄ ለመመለስ የ7ኛውን ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ ቁጥሮች በጥልቀት በመተንተን፣ በአብላጫ ድምፅ ሥርዓት የተገኘው ድምፅ በተመጣጣኝ ውክልና ሥርዓት ቢሰላ ኖሮ ምን ዓይነት ልዩነት ሊያመጣ እንደሚችል መርምራለች። በተጨማሪም የተለያዩ የምርምር ሥራዎችን በማገላበጥ የሁለቱን ሥርዓቶች ጠንካራ እና ደካማ ጎኖች አነጻጽራለች።
በኢትዮጵያ በተግባር ላይ ያለው የአብላጫ ድምፅ ሥርዓት በአንድ የምርጫ ክልል ውስጥ ከተፎካካሪዎቹ የበለጠ ድምፅ ያገኘውን ዕጩ ብቻ አሸናፊ የሚያደርግ ነው። ኢንሳይክሎፔዲያ ብሪታኒካን ጨምሮ ሌሎችም መዝገበ-ቃላት ይህንን ሥርዓት አሸናፊው “ሁሉንም ጠቅልሎ የሚወስድበት” (Winner-takes-all) አሠራር ሲሉ ይገልጹታል። ከዚህ በተቃራኒ የተመጣጣኝ ውክልና ሥርዓት የምክር ቤት ወንበሮች ስርጭት መራጮች ከሰጡት አጠቃላይ የድምፅ ስብጥር ጋር ተመጣጣኝ ድርሻ እንዲኖረው የሚያደርግ ነው። በዚህም መሠረት አንድ የፖለቲካ ፓርቲ 40 በመቶ የመራጮችን ድምፅ ካገኘ፣ በፍጹማዊ የተመጣጣኝ ውክልና ሥርዓት የሚኖረው የፓርላማ መቀመጫም እንዲሁ የወንበሮቹን 40 በመቶ ይሆናል።
የአብላጫ ድምፅ ሥርዓት በዩናይትድ ኪንግደም፣ ካናዳ እና ሕንድ ተግባራዊ ሲሆን፤ ኔዘርላንድ እና ስዊድንን ጨምሮ አብዛኞቹ የስካንዲኔቪያ ሀገራት ደግሞ የተመጣጣኝ ውክልና ሥርዓትን ይጠቀማሉ።
ይህንን መነሻ በማድረግ “ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የ7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ ውጤት ያሰላች ሲሆን፤ ይፋ ከተደረጉት 486 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ወንበሮች ውስጥ፣ በክልሎች የተገኙ የመራጮች ድምፆች ፓርቲዎች ባገኟቸው ድምፆች መቶኛ ቢሰሉ ኖሮ፣ የተቃዋሚ ወኪሎች ሊያገኟቸው ይችሉ የነበሩ 15 ወንበሮች በአብላጫ ድምፅ ሥርዓቱ ሳቢያ ወደ ብልፅግና ፓርቲ መግባታቸውን አረጋግጣለች።
በተለይ 40 በመቶ ገደማ የሚሆኑ መራጮች ድምፃቸውን ለተቃዋሚ ፓርቲዎች ወይም ለግል ዕጩዎች በሰጡባት አዲስ አበባ ከተማ፣ በአሁኑ የአብላጫ ድምፅ ሥርዓት ገዢው ፓርቲ ብልፅግና ከ23ቱ የፓርላማ ወንበሮች መካከል 20ዎቹን ያሸነፈ ቢሆንም፤ የምርጫ ሥርዓቱ ተመጣጣኝ ውክልና ቢሆን ኖሮ 14 ወንበሮችን ብቻ ያሸንፍ እንደነበር በቁጥሮቹ ተመላክቷል።
ከላይ በገላጭ ምስሉ እንደተመላከተው፣ የምርጫ ሥርዓቱ የአብላጫ ድምፅ በመሆኑ ብቻ ብልፅግና ፓርቲ በአዲስ አበባ 6፣ በደቡብ ኢትዮጵያ 3፣ በአማራ እና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ በእያንዳንዳቸው 2፣ እንዲሁም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና ጋምቤላ ክልሎች አንድ አንድ ወንበሮችን ካገኘው የድምፅ መቶኛ ምጣኔ በላይ አትርፏል።
በተቃራኒው ገዢው ፓርቲ ከ90 በመቶ በላይ ድምፅ ባገኘባቸው አፋር፣ ድሬዳዋ፣ ሐረሪ እና ኦሮሚያ፣ እንዲሁም ከ80 በመቶ በላይ ድምፅ ባገኘባቸው ማዕከላዊ ኢትዮጵያ (84%)፣ ሲዳማ (81%) እና ሶማሌ (85%) ክልሎች የተገኘው የመራጮች ድምፅ በተመጣጣኝ ውክልና ቢሰላም አሁን ካለው ውጤት የተለየ ለውጥ አያመጣም።
የመራጮችን ድምፅ መሠረት በማድረግ የምርጫ ሥርዓቱ ተመጣጣኝ ውክልና ቢሆን የትኞቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ያተርፉ እንደነበር “ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ባደረገችው ስሌት፤ ሰላም ለኢትዮጵያ ጥምረት 2 ተጨማሪ ወንበሮችን፣ እንዲሁም ነፃነት እና እኩልነት ፓርቲ (ነእፓ) እና ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት እያንዳንዳቸው 2 ተጨማሪ የፓርላማ ወንበሮችን ሊያገኙ ይችሉ እንደነበር ታውቋል።
በጥቅሉ 14 ፓርቲዎች በአሁኑ ሥርዓት ካገኟቸው ወንበሮች የበለጠ ተመጣጣኝ ውክልና ሊያገኙ ይችሉ የነበረ ሲሆን፤ በተቃራኒው ብልፅግና ፓርቲን ጨምሮ 5 ፓርቲዎች ደግሞ አሁን ካሸነፏቸው ወንበሮች ይቀንስባቸው ነበር።
የትኛው ሥርዓት ለኢትዮጵያ ያዋጣል?
ዓለም አቀፉ የዴሞክራሲ ተቋም አይዲኢኤ (International Institute for Democracy and Electoral Assistance – International IDEA) የምርጫ ሥርዓት ዲዛይን (“Electoral System Design”) በሚል ባሳተመው መመሪያው፣ “ለሁሉም አገር የሚሆን አንድ ወጥ የምርጫ ሥርዓት የለም” የሚል መሠረታዊ መርህ ያስቀምጣል። ሆኖም ኅብረ-ብሔራዊ፣ ክፍፍል የበዛባቸው ወይም ከግጭት በማገገም ላይ ያሉ አገራት የተመጣጣኝ ውክልና ወይም የሁለቱን ቅይጥ ሥርዓት ቢከተሉ አዋጭ መሆኑን ይመክራል።
በግጭት ውስጥ በቆዩ ማኅበረሰቦች ውስጥ “አሸናፊው ሁሉን ጠቅልሎ የሚወስድበት” ዜሮ ድምር (Zero-sum) ሥርዓት ዳግም ቅሬታና ግጭት ሊቀሰቅስ ስለሚችል፣ ሁሉም አካላት በፓርላማ ውክልና እንዲኖራቸው የተመጣጣኝ ውክልና ሥርዓት አካታችነት ወሳኝ እንደሆነ ያስረዳል።
በአንጻሩ የአገሪቱ ማኅበረሰቦች ባሕላዊ ወጥነት ካላቸው እና የተረጋጋ የፖለቲካ ሁኔታ ውስጥ ከሆኑ፣ የአብላጫ ድምፅ ሥርዓት መራጩ ከአካባቢው ተመራጭ ጋር ቀጥተኛ ተጠያቂነት እንዲፈጥር እና የተረጋጋ መንግሥት በቀላሉ እንዲመሠረት እንደሚያስችል ይገልጻል።
መልክዓ-ምድራዊ ውክልናን እና የድምፅ ፍትሐዊነትን በአንድ ላይ ለሚፈልጉ አገራት ደግሞ በጀርመን እና በኒውዚላንድ እንደታየው ዓይነት ቅይጥ ሥርዓት አዋጭ መሆኑን አይዲኢኤ ይጠቁማል። አይዲኢኤ እንደ አፍሪካ ባሉ ብዝኃነት ባላቸው ታዳጊ አገራት ውስጥ የአብላጫ ድምፅ ሥርዓት አምባገነንነትን እና የአንድ ፓርቲ ፍጹም የበላይነትን ስለሚያጠናክር፣ ወደ ተመጣጣኝ ውክልና ወይም ቅይጥ ሥርዓቶች እንዲያዘነብሉ ይመክራል።
ሌሎችም የፖለቲካ ሳይንስ ምሁራንም ከአይዲኢኤ ጋር ተመሳሳይ ምክረ-ሐሳብ አላቸው። በካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ፕሮፌሰር ኤሜሪተስ የሆኑት ሆላንዳዊ-አሜሪካዊው ምሁር አሬንድ ላይፍሃርት (Arend Lijphart) “Patterns of Democracy” በተሰኘው ታዋቂ መጽሐፋቸው፤ የተመጣጣኝ ውክልና ሥርዓት አናሳዎችን አካታች በማድረግ፣ የሴቶች ውክልናን በማሳደግና የተለያዩ ድምፆች እንዲሰሙ በማስቻል ከአብላጫ ድምፅ ሥርዓት የተሻለ ዲሞክራሲያዊ ጥራትና ፍትሐዊነት እንዳለው ይከራከራሉ።
በተመሳሳይ የሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲዋ ፕሮፌሰር ፒፓ ኖሪስ (Pippa Norris) “Electoral Engineering” በሚለው መጽሐፋቸው፤ ዓላማው “ውክልና፣ አካታችነትና ፍትሐዊነት” ከሆነ የተመጣጣኝ ውክልና ሥርዓት እንደሚበልጥ፣ ነገር ግን “ጠንካራና ኃላፊነት የሚወስድ መንግሥት በፍጥነት መፍጠር” ከሆነ ደግሞ የአብላጫ ድምፅ ሥርዓት እንደሚመረጥ ያስረዳሉ።
የተመጣጣኝ ውክልና ሥርዓት ለአፈጻጸም ውስብስብ መሆኑና አልፎ አልፎ የመንግሥት አለመረጋጋት መፍጠሩ እንደ ድክመት የሚነሳበት ሲሆን፤ የአብላጫ ድምፅ ሥርዓት ደግሞ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የመራጮችን ድምፅ ማባከኑ ዋነኛ ጉድለቱ ነው።
በኢትዮጵያ በ2010 ዓ.ም. መባቻ ገዢው ኢሕአዴግን ጨምሮ 16 የፖለቲካ ፓርቲዎች ባደረጉት “ድርድር”፣ የምርጫ ሕጉ ቅይጥ ሆኖ 80 በመቶ በአብላጫ ድምፅ እና 20 በመቶ በተመጣጣኝ ውክልና እንዲሆን ተስማምተው እንደነበር ይታወሳል። ይሁን እንጂ በሌሎች ተዛማጅ ነጥቦች ላይ ሙሉ ስምምነት ሳይደረስና ሕጉ ሳይሻሻል የመንግሥት ለውጥ መደረጉ አይዘነጋም። (ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)




