ኢሰመጉ እና ኅብረት ለምርጫ አጠቃላይ የምርጫ ትዝብት ሪፖርታቸውን ይፋ አደረጉ

ግንቦት 24 ቀን 2018 የተካሄደውን 7ኛ ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ ሙሉ ሂደት የታዘቡ ሁለት አገር በቀል የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አጠቃላይ የትዝብት ሪፖርታቸውን ይፋ አድርገዋል። የኢትዮጵያ የሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች ኅብረት ለምርጫ (ምርጫ ለኅብረት) ጳጉሜን 3 ቀን 2018 እንዲሁም የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) በማግስቱ ጳጉሜን 4 ቀን 2018 ይፋ ያደረጓቸው አጠቃላይ የምርጫ ትዝብት ሪፖርቶች በምርጫው ሂደት የተስተዋሉ ግድፈቶች እና ጥንካሬዎች የተዘረዘሩባቸው ናቸው።

ሁለቱም ተቋማት በሪፖርቶቻቸው እንዳስገነዘቡት፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባደረጋቸው አስተዳደራዊ እና ቴክኖሎጂያዊ ማሻሻያዎች ረገድ የተመዘገቡ ጥንካሬዎች ቢኖሩም፤ ሂደቱ በመላ አገሪቱ በተንሰራፋው የፀጥታ ቀውስ እና ከድምፅ መስጫ ምሥጥራዊነት በተያያዘ በተፈፀሙ ከባድ የሕግ ጥሰቶች ጥላ ሥር የወደቀ ነበር።

ሁለቱም የትዝብት ሪፖርቶች የተቀሱት የመራጮችን ነፃ ውሳኔ እና የሂደቱን ተዓማኒነት ያጠለሸው ዋነኛው ተግዳሮት በድምፅ መስጫ ምሥጢራዊ ሥፍራዎች የተፈፀሙ ጣልቃ ገብነቶች ናቸው።

ኢሰመጉ ባወጣው ሪፖርት፣ “በድምፅ አሰጣጥ ሂደቱ ሚስጢራዊነቱ የተጠበቀ መሆን የነበረበት ቢሆንም የምርጫ አስፈፃሚዎች ወደ ድምፅ መስጫ ሳጥኖች በመግባት ሕዝቡ በነፃነት እንዳይመርጡ ማድረጋቸውን” ገልጾ፣ ድርጊቱ መራጮች በነፃ ፍላጎታቸው የመምረጥ ሕገ-መንግሥታዊ መብታቸውን የጣሰ መሆኑን ገልጿል።

በተመሳሳይ መልኩ ምርጫ ለኅብረት በምርጫ ጣቢያዎች የተስተዋሉ ከባድ የአሠራር ግድፈቶችን ሲተነትን፣ “ታዛቢዎች በተገኙባቸው 87 (3 በመቶ) የምርጫ ጣቢያዎች ውስጥ ከሰብሳቢዎቹ ውጭ የሆኑ ግለሰቦች ለመራጮች እገዛ ሲያደርጉ ከአንድ ጊዜ በላይ ተስተውሏል” በማለት ሪፖርት አድርጓል። በተጨማሪም፣ “በ3 በመቶ ጣቢያዎች የምርጫ አስፈፃሚዎች በድምፅ መስጫ ወረቀቶች ላይ ምልክት ሲያደርጉ ተስተውለዋል” ሲል አስፈጻሚዎችና ያልተፈቀደላቸው አካላት የመራጮችን ምሥጢር መጣሳቸውን አረጋግጧል።

የፀጥታ ሁኔታ መደፍረስና የግጭቶች መስፋፋትም ሌላው በሁለቱም ሪፖርቶች የተነሳው ዋነኛ የመብት ጥሰት ነው። ኢሰመጉ በትግራይ፣ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች ምርጫው ሳይካሄድ መቅረቱን አስታውሶ፣ “ምርጫው በትግራይ ክልላዊ መንግሥት ሙሉ በሙሉ፣ በተወሰኑ አማራ እና ኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥታት የሚገኙ ውስን ስፍራዎች የሚገኙ ዜጎች ድምፅ የመስጠት ዕድል አለማግኘታቸውን እና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና በክልል መንግሥታት ምክር ቤቶች ውስጥ አለመወከላቸው አሳሳቢ ነው” ሲል አስፍሯል።

በሌላ በኩል ምርጫ ለኅብረት ይኼው የፀጥታ ችግር በርካታ ዜጎችን ከምርጫ ውጪ ማድረጉን ጠቅሶ፣ “የምርጫ ክንውኖች በ46 የምርጫ ክልሎች ውስጥ ጨርሶ አልተካሄዱም፤ ይህም 38ቱን የትግራይ ክልል የምርጫ ክልሎች እና 8ቱን የአማራ ክልል የምርጫ ክልሎች ያካትታል” በማለት የዜጎች የመምረጥ መብት ያልተሟላ መሆኑን ገልጿል።

በተጨማሪም በመራጮች ምዝገባ ወቅት በተፈፀመው ተገቢ ያልሆነ ጫና ዙሪያ ኢሰመጉ፣ “ሴፊቲኔት ተጠቃሚ የሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች የተወሰኑ ሰዎችን በመራጭነት የማስመዝገብ ግዴታ ተጥሎባቸው የነበረ መሆኑን፣ ተማሪዎችን መታወቂያ በመውሰድ መመዝገብ፣ እንዲሁም የምርጫ ካርድ ካልወሰዱ ማዳበሪያ ማግኘት እንደማይችሉ በመንግሥት አካላት በቀጥታ እና በተዘዋዋሪ ቅስቀሳ የተደረገ መሆኑን” ይፋ አድርጓል።

ምርጫ ለኅብረትም በበኩሉ ይኼው ተግባር የነበረ መሆኑን በራሱ ሪፖርት በማረጋገጥ፣ “የመራጮች ተሳትፎ የጎላ ቢሆንም፣ በአካባቢ ባለሥልጣናት በኩል የመመዝገብ ግዴታ የመጣል እና የማስገደድ ድርጊቶች ተፈፅመዋል” ሲል የአካባቢ አስተዳደር አካላት ያሳደሩትን ያልተገባ ተጽዕኖ መዝግቧል።

የውድድሩን ምኅዳር አስመልክቶ ተፎካካሪዎች ፍትሐዊ የውድድር ዕድል ያልነበራቸው መሆኑን ኢሰመጉ ሲያብራራ፣ “በገዢው ፓርቲ በተደጋጋሚ ሲጠሩ ከነበሩ የድጋፍ ሰልፎች ውጭ በተፎካካሪ ፓርቲዎች የነበረው እንቅስቃሴ ውስን የነበረ መሆኑን” ጠቁሟል። ምርጫ ለኅብረት በበኩሉ ይህንን አሃዛዊ በሆነ መረጃ በማስደገፍ፣ “በውድድሩ ምኅዳር ውስጥ ገዢው ብልፅግና ፓርቲ በ64 የምርጫ ክልሎች ውስጥ ያለምንም ተፎካካሪ ብቻውን ተወዳድሯል” ሲል ገዢው ፓርቲ በተቃዋሚዎች ማፈግፈግና በፀጥታ ስጋት ሳቢያ ያገኘውን ብልጫ አሳይቷል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሂደት 55 አገር በቀል የሲቪል ማኅበራት ድርጅቶችን የታዛቢነት ዕውቅና የሰጠ መሆኑን የገለጸ ሲሆን፣ እነዚህ ድርጅቶች በድምሩ ከ65 ሺሕ በላይ የአገር ውስጥ ታዛቢዎችን አስመዝግበው ነበር።

ምርጫ ለኅብረት ብቻውን ከ101 አባል ድርጅቶቹ የተውጣጡ 522 የረጅም ጊዜ ታዛቢዎችን በቅድመ-ምርጫ፣ በድምፅ መስጫ ዕለትና በድኅረ-ምርጫ ምዕራፎች ማሰማራቱን የገለጸ ሲሆን፣ በምርጫው ዕለት ደግሞ 3,477 ቋሚና ተንቀሳቃሽ ታዛቢዎችን በማሰማራት 7,723 የምርጫ ጣቢያዎችን (ማለትም በቦርዱ ከተቋቋሙት ጣቢያዎች 15 በመቶ የሚሆኑትን) መታዘብ ችሏል።

በሌላ በኩል ኢሰመጉ በስድስት ክልሎች እና በሁለት ከተማ መስተዳድሮች ውስጥ 433 ቋሚና ተንቀሳቃሽ ታዛቢዎችን እንዲሁም 25 የኹነቶች መከታተያ ባለሙያዎችን በማሰማራት ከ830 በላይ የምርጫ ጣቢያዎችን በቀጥታ ታዝቧል።

ከአጠቃላይ ታዛቢዎች በተጨማሪ በምርጫው የሴቶችን ተሳትፎ እና ፆታዊ ጥቃቶችን ለመከታተል የተለየ የትዝብት ሥራ መከናወኑን መዘገባችን ይታወሳል። የኢትዮጵያ ሴት የሕግ ባለሙያዎች ማኅበር 136 ጣቢያዎችን፣ እንዲሁም ትምራን 150 ታዛቢዎችን በማሰማራት በምርጫ ውስጥ በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶችን የመከታተል ሥራ መሥራታቸው ተገልጿል። በዓለም አቀፍ ደረጃም የአፍሪካ ኅብረት የቀድሞው የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ የመሩትን 73 አባላት ያሉት የትዝብት ልዑክ በስምንት ክልሎች በሚገኙ 495 ጣቢያዎች ያሰማራ ሲሆን፤ የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን (ኢጋድ/IGAD) በበኩሉ በዶ/ር ስፔሲዮዛ ዋንዲራ ካዚብዌ የሚመራ ልዑክ መድቦ 208 ጣቢያዎችን በመታዘብ የምርጫውን ሒደት ታዝቧል።

ሆኖም፣ ኢሰመጉ እና ምርጫ ለኅብረት ይፋዊ የትዝብታቸውን አጠቃላይ ሪፖርታቸውን ያወጡ የመጀመሪያዎቹ ታዛቢዎች ሆነዋል። (ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)