የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የመራጮች ድምፅ ቁጥር ምን ይነግረናል?

ሰባተኛው ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ ግንቦት 24 ቀን 2018 በ501 የምርጫ ክልሎች ተካሂዷል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰኔ 14 ቀን 2018 የ486 የምርጫ ክልሎችን ውጤት ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ በቀሪዎቹ ላይ ድጋሚ ምርጫ ወይም ድጋሚ ቆጠራ እንደሚካሄድ አስታውቋል። በማስከተልም ቦርዱ በሰኔ ወር መጨረሻ የምርጫውን ዝርዝር ውጤት በድረ-ገጹ ይፋ አድርጓል፤ “ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የዚህን ምርጫ ዝርዝር ውጤት በጥልቀት በመመርመር ከመራጮች ድምፅ ብዛትና ስርጭት ጀርባ ያሉ እውነታዎችን እና የፖሊሲ እርምጃ የሚሹ ጉዳዮችን አውጥታለች።

“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የ7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ ከቅድመ ምርጫ ዝግጅት ጀምሮ እስከ ምርጫው ዕለትና የድኅረ ምርጫው ሙሉ ሂደት ድረስ በዝርዝር ስትዘግብ ቆይታለች። መረጃዎቿንም ከዕለት ተዕለት ዜናዎች ባለፈ፣ በገላጭ ምስሎች (Infographics) እና በጥቅል የዳታ ትንታኔዎች በማስደገፍ ዘላቂ የምርጫ ፖሊሲ ግብዓት ሊሆን በሚችል መልኩ አቅርባለች። ለአብነትም የምርጫው ሙሉ የዕጩዎች ዝርዝር ይፋ መደረጉን ተከትሎ ያዘጋጀችው የዕጩዎች ዝርዝር ጥልቅ ትንታኔ የምርጫውን ውጤት ቀድሞ ለመተንበይ ያስቻለ ነበር። በተመሳሳይ፣ በቅርቡ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋ የሆነውን ዝርዝር መረጃ መሠረት በማድረግ፣ ይህንን የ7ኛው ምርጫ ውጤት ጥልቅ ትንታኔ ከ6ኛው ጠቅላላ ምርጫ ጋር በማነጻጸር በጽሑፍ፣ በቁጥርና በገላጭ ምስሎች አሰናድታዋለች።

በምርጫው ዋዜማ የነበረው ሂደት የገዢው ብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ የሆነ የዕጩዎች እና የሀብት የበላይነት የታየበት ሲሆን፣ ፓርቲው በመላ አገሪቱ በሚገኙ አብዛኞቹ የምርጫ ክልሎች 461 ዕጩዎችን አሰማርቶ ተወዳድሯል። በአንጻሩ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በፋይናንስ እጥረት፣ በጸጥታ ስጋት፣ በአባላት እስር እና በአደረጃጀት ውስንነት ሳቢያ በሁሉም አካባቢዎች እኩል ዕጩዎችን ማቅረብ ባለመቻላቸው ገዢው ፓርቲ ብቻውን የተወዳደረባቸው 65 የምርጫ ክልሎች ነበሩ፤ የተቃዋሚ ፓርቲ ተወዳዳሪዎች እና የግል ዕጩዎችም በ10 የምርጫ ክልሎች ውስጥ ያለምንም ተፎካካሪ ለውድድር ቀርበዋል። ከዚህ በተጨማሪም፣ አንዳንድ ተቃዋሚዎች የዲሞክራሲ ምኅዳሩን ከማስፋት ይልቅ ለተቃዋሚዎች የተሰጠ ችሮታ ነው ሲሉ ቢተቹትም፣ ገዢው ፓርቲ ለተቃዋሚ ወኪሎች እና ጥቂት የግል ተወዳዳሪዎች የፓርላማ ወንበሮችን ለማጋራት በሚል በ48 የምርጫ ክልሎች ውስጥ ዕጩ ሳያቀርብ ቀርቷል።

ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምርጫ ከተካሄደባቸው 501 የምርጫ ክልሎች መካከል ውጤታቸው በይፋ የጸደቀውን የ486 የምርጫ ክልሎች አጠቃላይ የድምፅ ስርጭት ይፋ ሲያደርግ፣ ገዢው ብልፅግና ፓርቲ 438 መቀመጫዎችን ጠቅልሎ በመውሰድ ፍጹም አብላጫ ድምፅ ማግኘቱ ታውቋል። ቀሪዎቹ 48 ወንበሮች በተለያዩ ተቃዋሚ ፓርቲዎችና በግል ተወዳዳሪዎች መካከል የተከፋፈሉ ሲሆን፣ ገዢው ፓርቲ ውጤት ከታወጀባቸው የፓርላማ ወንበሮች መካከል 90 በመቶውን በማሸነፍ የምርጫውን ፍጹም የበላይነት አረጋግጧል። በቀሪዎቹ የምርጫ ክልሎች ላይ ደግሞ በድምፅ ቆጠራና በሂደት ግድፈቶች ሳቢያ ድጋሚ ቆጠራና ድጋሚ ምርጫ እንደሚካሄድ መገለጹ ይታወሳል።

አርባ የተቃዋሚ ፓርቲ ወኪሎች እና ስምንት የግል ተወዳዳሪዎች የፓርላማ ወንበሮችን ቢያሸንፉም፣ በ43ቱ ላይ ግን ብልፅግና ፓርቲ ተወዳዳሪ ዕጩዎችን አላቀረበም ነበር። ስለሆነም ተቃዋሚዎች ገዢውን ፓርቲ ተወዳድረው ያሸነፉት በአምስት የፓርላማ ወንበሮች ላይ ብቻ ነው። ብልፅግና ፓርቲ ተወዳድሮ ከተሸነፈባቸው አምስት ወንበሮች መካከል አራቱን ኢዜማ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሲያሸንፍ፣ አንዱን ደግሞ በኦሮሚያ ክልል አንድ የግል ተወዳዳሪ አሸንፈዋል። በዚህም ሳቢያ፣ ድጋሚ ምርጫ ወይም ቆጠራ የሚካሄድባቸው የምርጫ ክልሎች ውጤት ሲጠናቀቅ፣ ተቃዋሚዎች የሚያገኙት ወንበር ብዛት ቢያንስ በአምስት ሊጨምር ይችላል።

በምርጫው ሂደት ተቃዋሚ ፓርቲዎችና የግል ዕጩዎች ያገኟቸው ውስን 48 የፓርላማ ወንበሮች እንዲሁም ጥቂት የክልል ምክር ቤት መቀመጫዎች፣ በአብዛኛው የተመዘገቡት ገዢው ብልፅግና ፓርቲ ዕጩ ባላቀረበባቸውና ፉክክሩ በተቃዋሚዎችና በግል ተወዳዳሪዎች መካከል ብቻ በተካሄደባቸው አካባቢዎች ነው። በእነዚህ አካባቢዎች የተገኙት ውጤቶች እውነተኛውን የሕዝብ ውሳኔና የነፃ ውድድር አቅም ከማሳየት ይልቅ፣ ገዢው ፓርቲ በቅድሚያ ዕጩ ባለማቅረብ ባመቻቸው ክፍተት የተገኙ በመሆናቸው፣ ተቃዋሚዎች ከገዢው ፓርቲ ጋር በቀጥታ ተፎካክረው ያሸነፉባቸው ወንበሮች እጅግ አናሳ መሆናቸውን ያሳያል።

የብልፅግና ፓርቲ ፍጹም የበላይነት

በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ብልፅግና ፓርቲ ከ13ቱ ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች መካከል በስምንቱ ከ80 በመቶ በላይ የመራጮችን ድምፅ አግኝቷል። ፓርቲው በኦሮሚያ 96.6 በመቶ፣ በድሬዳዋ 94.3 በመቶ እና በአፋር 91.6 በመቶ የሚሆነውን እጅግ ከፍተኛ የመራጮች ድምፅ ማግኘት ችሏል። በአንጻሩ ዝቅተኛ ድምፅ ያገኘው በአዲስ አበባ ሲሆን፣ ይኸውም 60.1 በመቶ ነው። ከአዲስ አበባ ቀጥሎ በደቡብ ኢትዮጵያ (72.1%) እና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ (74%) በአንጻራዊነት ዝቅተኛ ድምፅ አግኝቷል። ገዢው ፓርቲ ይህንን ያህል ከፍተኛ ድምፅ ያገኘው ባልተወዳደረባቸው የምርጫ ክልሎች ምንም ዓይነት ድምፅ ባላገኘበት ሁኔታ ነው።

ግራፍ 1፤ ብልፅግና ፓርቲ ያገኘው ድምፅ በመቶኛ (ቁጥሮቹን ለመመልከት የመረጡትን ባር ቻርት ይጫኑ።)

የዘንድሮው ምርጫ ምንም እንኳን ከ6ኛው ጠቅላላ ምርጫ አንጻር ያነሰ ፉክክር የተስተዋለበት ቢሆንም፣ ብልፅግና ፓርቲ ካለፈው ምርጫ ያነሰ ድምፅ ያገኘባቸው ክልሎችም አሉ። ከእነዚህም ውስጥ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ (17.3%)፣ ሲዳማ (16.4%) እና ሶማሌ (12.5%) ክልሎችን ጨምሮ በስምንት ክልሎች ውስጥ ካለፈው ምርጫ ያነሰ የመራጮች ድምፅ አግኝቷል። በተቃራኒው በአማራ (17.2%)፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ (12.9%)፣ በአዲስ አበባ (6.4%) እና በድሬዳዋ (3.8%) ካለፈው ምርጫ የተሻለ ድምፅ ሲያገኝ፣ በኦሮሚያ ክልል ግን ተመሳሳይ መጠን ያለው ድምፅ ማግኘቱ ተመዝግቧል። (ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያን ጨምሮ 6ኛው ምርጫ ወቅት ራሳቸውን ችለው ባልነበሩ ክልሎች ውስጥ ያለው ንጽጽር የተሰላው በወቅቱ በነበሩት የምርጫ ክልሎች ውጤት መሠረት ነው።)

የካርታ ማሳያ፤ ብልፅግና ፓርቲ በየክልሉ ያገኘው የድምፅ ምጥጥን (የመራጮች ድምፅ ድርሻ እና ከ6ተኛው ምርጫ አንፃር ያለውን የመራጮች ድምፅ ለውጥ ለመመልከት ከላይ ያሉትን አማራጮ ይምረጡ። ካርታው ላይ የመረጡት ክልል ላይ ክሊክ በማድረግ ውጤቱን ይመልከቱ)

ተቃዋሚዎች የት አተረፉ? የት አጎደሉ?

ከ6ኛው ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ ጋር ሲነጻጸር፣ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ላይ የተሳተፉ መራጮች ቁጥር እንደሚበልጥ የምርጫ ቦርድ መረጃዎች ያሳያሉ። በ6ኛው ምርጫ 40,525,964 መራጮች ተመዝግበው 37,035,067 ያህሉ ድምፅ የሰጡ ሲሆን፤ በዘንድሮው ምርጫ ደግሞ የ33 በመቶ ብልጫ ያላቸው 54,057,861 መራጮች ተመዝግበው፣ 52,003,662 መራጮች ድምፅ እንደሰጡ ምርጫ ቦርድ አሳውቋል። ዘንድሮ ምርጫ የተካሄደባቸው የምክር ቤት ወንበሮች ብዛትም ከ6ኛው ምርጫ አንጻር ጭማሪ አሳይቷል፤ በ6ኛው ምርጫ 482 ወንበሮች ላይ በሦስት ዙር ምርጫ የተካሄደ ሲሆን፣ በዘንድሮው ምርጫ 501 ወንበሮች ላይ ምርጫ ተካሂዷል። ለዘንድሮው ምርጫ መራጮች ተመዝግበው የነበሩት ለ509 የምርጫ ክልሎች ቢሆንም፣ በጸጥታ ስጋት ምክንያት በአማራ ክልል ስምንት የምርጫ ክልሎች ላይ ምርጫ ሳይካሄድ መቅረቱ ይታወሳል።

ይሁን እንጂ የተሻለ ነፃ ፉክክር በሚታይባት በአዲስ አበባ ከተማ በ6ኛው ጠቅላላ ምርጫ ከገዢው ፓርቲ ቀጥሎ ከፍ ያለ ድምፅ አግኝተው የነበሩት ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ (ባልደራስ) እና የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ)፣ በ7ኛው ምርጫ ያገኙት ድምፅ ማሽቆልቆሉ ተስተውሏል። ባልደራስ በ6ኛው ምርጫ ካገኘው ድምፅ አንጻር በ7ኛው ምርጫ የ13.9 በመቶ ቅናሽ ሲያሳይ፣ ኢዜማ ደግሞ የ4.4 በመቶ ድምፅ በማጣት ተከታይ ሆኗል።

በግራፍ 2 የቀረበው አራት ትልልቅ ድምፅ ያገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች በየክልሉ ያሳዩት የድምፅ ጭማሪ ወይም ቅናሽ እንደሚያሳየው፣ ብልፅግና ፓርቲ በስምንት ክልሎች ድምፅ አጥቷል። ከፍተኛ ድምፅ ያጣው በ6ኛው ምርጫ በደቡብ ክልል ሥር በነበረውና በአሁኑ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ (17.3%) ሲሆን፣ በመቀጠልም በሲዳማ ክልል የ16.4 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል። በተቃራኒው ተቃዋሚ ፓርቲዎች በቀድሞው የደቡብ ክልል ሥር በነበሩት አራቱ ክልሎች ውስጥ የተሻለ ድምፅ አግኝተዋል።

ኢዜማ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የ6.5 በመቶ ድምፅ ጭማሪ ማግኘት ቢችልም፣ በዘጠኝ ክልሎች ግን ካለፈው ምርጫ ያነሰ ድምፅ አስመዝግቧል። በተለይ ኢዜማ “ዕጩዬ ያለ አግባብ ተሰርዞብኛል” በማለት ቅሬታ ሲያቀርብበት በነበረው በሐረሪ ክልል ያገኘው ድምፅ በ5.8 በመቶ ዝቅ ብሏል። ነፃነት እና እኩልነት ፓርቲ (ነእፓ) ከስድስተኛው ምርጫ አንጻር በሰባተኛው ምርጫ በሰባት ክልሎች የተሻለ ድምፅ ማግኘት የቻለ ሲሆን፣ በተለይም በማዕከላዊ ኢትዮጵያ (3%) እና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ (2.5%) ከፍ ያለ ድምፅ አስመዝግቧል። በ7ኛው ምርጫ ለመጀመሪያ ጊዜ ለውድድር የቀረበው ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት (ትብብር) ከፍተኛ ድምፅ ያገኘው በአዲስ አበባ ውስጥ ነው። ትብብር በአዲስ አበባ 8.5% የመራጮችን ድምፅ አግኝቷል።

ግራፍ 2፤ ከፍተኛ ድምፅ ያገኙ አራት ፓርቲዎች ከስድስተኛው ምርጫ አንፃር ያገኙት እና ያጎደሉት ድምፅ (የመረጡትን ግራፍ ላይ ክሊክ በማድረግ ውጤቱን ይመልከቱ)

በአገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ድምፅ ያጡት ኢዜማ እና የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ናቸው። በ6ኛው ጠቅላላ ምርጫ ካገኙት የመራጮች ድምፅ አንጻር ኢዜማ የ1.2 በመቶ፣ አብን ደግሞ የ1.1 በመቶ ቅናሽ አሳይተዋል። አብን ለዚህ የድምፅ ማጣት የተዳረገው በአማራ ክልል ያገኘው ድምፅ በ10 በመቶ በመቀነሱ ሳቢያ ነው።

ግራፍ 3፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያገኙት እና ያጡት ድምፅ በክልል፣ በመቶኛ (ክልል ከላይ በመምረጥ የሚፈልጉት የባር ቻርት ላይ ክሊክ በማድረግ ለውጡን ይመልከቱ)

ፉክክሩ በምርጫ ክልሎች ምን ይመስላል?

የ7ኛው እና የ6ኛው ጠቅላላ ምርጫዎች የድምፅ ውጤት በምርጫ ክልሎች ደረጃ ሲፈተሽ፣ 6ኛው ምርጫ የተሻለ ፉክክር እንደነበረበት መረዳት ይቻላል። የምርጫ ውጤት ከተረጋገጠባቸው 486 የምርጫ ክልሎች ውስጥ በ394ቱ (81%) ያሸነፉ ዕጩዎች ተከታይ ተፎካካሪያቸውን ከ75 በመቶ በላይ በሆነ እጅግ የተጋነነ የድምፅ ልዩነት (Landslide) አሸንፈዋል። በአንጻሩ በ6ኛው ምርጫ ውጤት በታወቀባቸው 482 የምርጫ ክልሎች ውስጥ በአሸናፊው እና በተከታዩ መካከል እንዲህ ዓይነቱ የተጋነነ የድምፅ ልዩነት የተመዘገበው በ301ዱ (62%) የምርጫ ክልሎች ብቻ ነበር።

አብዛኛዎቹ የተጋነኑ የድምፅ ልዩነቶች የሚስተዋሉት ብልፅግና ፓርቲ ባሸነፈባቸው የምርጫ ክልሎች ሲሆን፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በሁለቱም ምርጫዎች ያገኟቸው ድምፆች ከተፎካካሪዎቻቸው ጋር የተቀራረቡ ነበሩ። የገዢው ፓርቲ ዕጩዎች በአንዳንድ አካባቢዎች 100 በመቶ የመራጮችን ድምፅ ያገኙ ሲሆን፣ በእነዚህ የምርጫ ክልሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች ዕጩ አላቀረቡም ወይም ደግሞ አንድም ድምፅ አላገኙም።

ግራፍ 4፤ ተመራጮች ተከታይ ድምፅ ካገኘው ተወዳዳሪ አንፃር ያገኙት ድምፅ ልዩነት በመቶኛ (ከስድስተኛው ምርጫ ጋር ለማወዳደር ከላይ ይምረጡ፤ የእያንዳንዱን የምርጫ ክልሎች የድምፅ ልዩነት ለማየት ከፈለጉ ነጥቦቹን ክሊክ ያድርጉ)

ንጽጽሩ በክልሎች ሲታይ፣ በሁለቱም ምርጫዎች ኦሮሚያ እጅግ ዝቅተኛ ፉክክር የተስተዋለበት ክልል ሲሆን፣ አዲስ አበባ ደግሞ በአንጻራዊነት የተሻለ ፉክክር የታየባት ሆናለች። በአዲስ አበባ በሁለቱም ምርጫዎች አንድም ከ75 በመቶ በላይ በሆነ የተጋነነ የድምፅ ልዩነት ያሸነፈ ዕጩ አልተመዘገበም። በስድስተኛው ምርጫ ከሦስቱ በስተቀር ቀሪዎቹ 20 ዕጩዎች ተፎካካሪዎቻቸውን ከ50 በመቶ ባነሰ የድምፅ ልዩነት አሸንፈዋል። በወቅቱ ከ25 በመቶ ባነሰ የድምፅ ልዩነት ተፎካካሪያቸውን ያሸነፉት ብቸኛ የግል ተወዳዳሪ እና ብልፅግና ፓርቲ ያልተወዳደራቸው የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ ዳንኤል ክብረት ብቻ ነበሩ።

በ2018ቱ ምርጫ ግን የአዲስ አበባ የፉክክር ደረጃም በመጠኑ ቀንሷል። አብዛኞቹ (16ቱ ዕጩዎች) ተፎካካሪዎቻቸውን ከ50 በመቶ በላይ በሆነ የድምፅ ልዩነት አሸንፈዋል። ብልፅግና ፓርቲ ወንበር የለቀቀላቸው ሁለት ተቃዋሚዎች ደግሞ ከ25 በመቶ ባነሰ ጠባብ የድምፅ ልዩነት ተፎካካሪዎቻቸውን ማሸነፋቸው ታውቋል።

ከዚህ በተቃራኒ የቆመው የኦሮሚያ ክልል ነው። በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በኦሮሚያ ብልፅግና ፓርቲ የፓርላማ ወንበር ከለቀቀላቸው አንድ ዕጩ በስተቀር፣ ሁሉም ተመራጮች ተፎካካሪዎቻቸውን ከ75 በመቶ በላይ በሆነ የተጋነነ የድምፅ ልዩነት አሸንፈዋል። አንዳንድ ዕጩዎች 100 በመቶ ድምፅ ማግኘታቸውም ተመዝግቧል። በተመሳሳይ በ6ኛውም ጠቅላላ ምርጫ ከሁለት ተቃዋሚዎች እና ከአንድ የብልፅግና ተመራጭ በስተቀር፣ ቀሪዎቹ ከ75 በመቶ በላይ በሆነ ሰፊ ልዩነት አሸንፈዋል። በኦሮሚያ በሁለቱም ምርጫዎች ከ50 በመቶ ባነሰ የድምፅ ልዩነት የተመረጠ አንድም ዕጩ አልነበረም። (በግራፍ 5 ያልተካተቱት ክልሎች ያላቸው የፓርላማ መቀመጫዎች ብዛት ዝቅተኛ በመሆኑ ለንጽጽራዊ ማሳያ ምቹ ባለመሆናቸው ነው።)

ግራፍ 5፤ ተመራጮች ከተከታይ ተፎካካሪዎቻቸው አንፃር ያገኙት ድምፅ ልዩነት በመቶኛ፣ በክልል (ክላይ ክልል ይምረጡ፣ ነጥቦቹ ላይ ክሊክ በማድረግ የድምፅ ልዩነቱን ይመልከቱ)

የምርጫ ሥርዓቱ ችግር አለበት?

በኢትዮጵያ በተግባር ላይ ያለው የአብላጫ ድምፅ (First-Past-the-Post – FPTP) የምርጫ ሥርዓት በተደጋጋሚ ከተመጣጣኝ ውክልና (Proportional Representation – PR) ሥርዓት ጋር ለንጽጽር ይቀርባል። የአብላጫ ድምፅ ሥርዓት በአንድ የምርጫ ክልል ከተወዳደሩት መካከል ብልጫ ድምፅ ያገኘውን ዕጩ ብቻ አሸናፊ የሚያደርግ ሲሆን፣ በተለይም የመራጮችን ድምፅ በማባከን ረገድ በስፋት ይተቻል። ለአብነትም ከፍተኛ ፉክክር በታየበት የአዲስ አበባ ምርጫ ክልል 11 ውስጥ፣ 59,159 መራጮች ድምፅ በሰጡበት ሁኔታ በግል የተወዳደሩት አቶ አበበ ገመቹ 10,459 (18 በመቶ) ድምፅ በማግኘት ተፎካካሪዎቻቸውን በስምንት በመቶ ጠባብ ልዩነት አሸንፈዋል። በዚህም ሳቢያ ወደ ሌሎች ተወዳዳሪዎች የሄደው 80 በመቶ የሚሆነው የሕዝብ ድምፅ ያለ ምንም ውክልና እንዲባክን ሆኗል።

በተቃራኒው የተመጣጣኝ ውክልና ሥርዓት ፓርቲዎች ባገኟቸው አጠቃላይ ድምፆች ምጣኔ ልክ የምክር ቤት መቀመጫዎችን የሚያከፋፍል አሠራር ነው። በዚህ ሥርዓት የምክር ቤት ወንበሮች ስርጭት መራጮች ከሰጡት አጠቃላይ የድምፅ ስብጥር ጋር ተመጣጣኝ ድርሻ ይኖረዋል። ለምሳሌ በአዲስ አበባ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ለተቃዋሚ ፓርቲዎች እና ለግል ተወዳዳሪዎች የተሰጡ ድምፆች ድምር 40 በመቶ የነበረ ሲሆን፣ ይህ ድምፅ በተመጣጣኝ ውክልና ሥርዓት ቢሰላ ኖሮ ገዢው ፓርቲ ካሸነፋቸው 20 ወንበሮች መካከል ስድስቱ ወደ ተቃዋሚዎች ይሄዱ ነበር።

ግራፍ 6፤ የ7ተኛው ጠቅላላ ምርጫ ውጤት በተመጣጣኝ ውክልና የምርጫ ሥርዓት ቢከፋፈል የሚያመጣው ለውጥ

ውጤታቸው ይፋ ከተደረገው 486 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ወንበሮች ውስጥ፣ ተቃዋሚዎች ከሕዝቡ ባገኙት የድምፅ ድርሻ ሊያገኟቸው ይችሉ የነበሩ 15 ወንበሮች በአብላጫ ድምፅ ሥርዓቱ ምክንያት ወደ ገዢው ብልፅግና ፓርቲ ገብተዋል። የምርጫ ሥርዓቱ የአብላጫ ድምፅ በመሆኑ ብቻ ብልፅግና ፓርቲ በአዲስ አበባ 6፣ በደቡብ ኢትዮጵያ 3፣ በአማራ እና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ በእያንዳንዳቸው 2፣ እንዲሁም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና በጋምቤላ ክልሎች አንድ አንድ ወንበሮችን ካገኘው የድምፅ ምጣኔ በላይ አትርፏል። በአንጻሩ ሰላም ለኢትዮጵያ ጥምረት ሁለት ተጨማሪ ወንበሮችን፣ እንዲሁም ነእፓ እና ትብብር እያንዳንዳቸው ሁለት ተጨማሪ የፓርላማ ወንበሮችን ሊያገኙ ይችሉ ነበር። በጥቅሉ 14 ተቃዋሚ ፓርቲዎች በአሁኑ ሥርዓት ካገኟቸው ወንበሮች የበለጠ ተመጣጣኝ ውክልና ሊያገኙ ይችሉ የነበረ ሲሆን፣ በተቃራኒው ብልፅግና ፓርቲን ጨምሮ አምስት ፓርቲዎች አሁን ካሸነፏቸው ወንበሮች ይቀንስባቸው ነበር።

ባልተመጣጠነ ድምፅ የተመረጡ የፓርላማ አባላት

የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የመራጮች ተሳትፎ እንደሚያሳየው፣ አንድ ክልል ከሌላው እንዲሁም አንዱ የምርጫ ክልል ከሌላኛው ሲታይ እጅግ ያልተመጣጠነ (Asymmetrical) የመራጮች ብዛት ልዩነት ተመዝግቧል። አሸናፊዎችን የመረጡ መራጮች አማካይ ቁጥር በክልል ሲነጻጸር በአፋር 302,975፣ በሶማሌ 204,744 እና በኦሮሚያ 128,991 ሆኖ እጅግ ከፍተኛ የመራጮች አማካይ ብዛት ሆኖ ተመዝግቧል። በተቃራኒው በቤኒሻንጉል ጉሙዝ 21,866፣ በአዲስ አበባ 35,408 እና በደቡብ ኢትዮጵያ 37,895 ዝቅተኛ የአማካይ መራጮች ቁጥር ተመዝግበዋል።

ይህ ሰፊ ልዩነት የፓርላማ ተመራጮች በሚወክሏቸው ሰዎች ብዛት ላይ በግልጽ ይንጸባረቃል። በዚህ ረገድ በአማራ ክልል “አዲስ ቅዳም” የምርጫ ክልል ተወዳድረው ያሸነፉት ፈተና ባዩ ሽባባው ያገኙት አጠቃላይ ድምፅ 840 ብቻ በመሆኑ፣ በምርጫው እጅግ ዝቅተኛ ድምፅ ያገኙ ተመራጭ ሆነዋል። አንድ የድምፅ መስጫ ሳጥን (ኮሮጆ) ከ1,200 እስከ 1,500 የድምፅ መስጫ ወረቀቶችን ማስተናገድ የሚችል በመሆኑ፣ ፈተና ባዩ የተወዳደሩበት የምርጫ ክልል ውስጥ የተሰጠው ጠቅላላ ድምፅ አንድ ኮሮጆ እንኳ የማይሞላ እንደነበር መረዳት ይቻላል።

በተቃራኒው በአገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛውን ድምፅ በማግኘት ቀዳሚ የሆኑት በአፋር ክልል “አብዓላ” የምርጫ ክልል የተወዳደሩት የመከላከያ ሚኒስትሯ አይሻ መሐመድ ሙሳ ናቸው። ሚኒስትሯ በምርጫ ክልሉ ድምፃቸውን ከሰጡት 560,005 መራጮች መካከል 553,458 (99 በመቶ) ድምፅ በማግኘት ተመርጠዋል። በዚህም መሠረት አይሻ መሐመድ ፈተና ባዩን ከመረጧቸው መራጮች የ658 እጥፍ ያህል ድምፅ ቢያገኙም፣ ሁለቱም በፓርላማ ውስጥ እኩል የአንድ ድምፅ ውሳኔ ሰጪነት አላቸው።

ከ7ኛው ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ መራጮች ብዛት በመነሳት ሲሰላ፣ የአንድ የምርጫ ክልል አማካይ የመራጮች ብዛት 158,838 ነው። የምርጫ ክልሎችን የመራጮች ብዛት ለማመጣጠን በቬኒስ ኮሚሽን የሕዝብ ቁጥር ውክልና ምጣኔ መስፈርት መሠረት የዚህ አማካይ ቁጥር የ15 በመቶ ጭማሪ ወይም ቅናሽ እንደ ልዩነት ወሰን ተወስዶ ንጽጽር ሲደረግ በምርጫ ክልሎች መካከል እጅግ ሰፊ ልዩነት ተስተውሏል። ምርጫ ቦርድ ይፋ ያደረገው የውጤት ዝርዝር፣ በየምርጫ ክልሉ የተመዘገቡ መራጮችን ቁጥር ስለማይጨምር፣ ግራፍ 7 በስድስተኛው ምርጫ ወቅት የነበረውን የምርጫ ክልሎች መራጮች ብዛት ልዩነት እንዲያሳይ ተደርጎ ቀርቧል።

ግራፍ 7፤ የምርጫ ክልሎች የመራጮች ቁጥር ምጥጥን (በዚህ ምስላዊ መግለጫ የ6ተኛውን ምርጫ ቁጥሮች ለመጠቀም የተገደድነው ምርጫ ቦርድ ይፋ ያደረገው የ7ተኛው ምርጫ መረጃ በየምርጫ ክልሉ የተመዘገቡ መራጮች ቁጥርን የማይጨምር በመሆኑ ነው።)

በ6ኛው ጠቅላላ ምርጫ ከ40 ሺሕ እስከ 80 ሺሕ መራጮች የተመዘገቡባቸውን የምርጫ ክልሎች እንደ አማካይ በመውሰድ ሲሰላ፣ በ82 የምርጫ ክልሎች ከወሰኑ/ከአማካዩ በታች የሆኑ መራጮች የተመዘገቡ ሲሆን፣ በ170 የምርጫ ክልሎች ላይ ደግሞ ከወሰኑ/ከአማካዩ በላይ መራጮች ተመዝግበው ነበር።

የኢትዮጵያ የምርጫ ክልሎች የተካለሉት በ1987 ዓ.ም. በተደረገው የመጀመሪያው ምርጫ ወቅት ሲሆን፣ የኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 54(3) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት “የሕዝብ ብዛትንና በልዩ ትኩረት ውክልና የሚሰጣቸውን አናሳ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን ቁጥር መሠረት በማድረግ 550 የማይበልጥ ሆኖ፣ ከእነዚህ ውስጥ አናሳ ብሔረሰቦች 20 የማያንስ መቀመጫ ይኖራቸዋል” ሲል ይደነግጋል። የምርጫ አዋጅ ቁጥር 1162/2011 በአንቀጽ 13(1 እና 2) ስር የምርጫ ክልሎች “በሕዝብ ቆጠራ ውጤት መሠረት ማስተካከያ ሊደረግባቸው” እንደሚችልና “አነስተኛ የሕዝብ ብዛት ያላቸውን ብሔረሰቦች ሳይጨምር የምርጫ ክልሎቹ ተቀራራቢ የሕዝብ ቁጥር ኖሯቸው በመካከላቸው ያለው ልዩነት ከ15 በመቶ መብለጥ” እንደሌለበት ይደነግጋል።

ይህንን መሠረት በማድረግ እና የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት በ1987 ዓ.ም. የነበረውን የሕዝብ ብዛት እና የ2017 ዓ.ም. የሕዝብ ብዛት ትንበያ ግምት መሠረት በማድረግ፣ “ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ክልሎች በፓርላማ ሊኖራቸው የሚገባውን የመቀመጫ ድርሻ አስልታለች።

ግራፍ 8፤ የምርጫ ክልሎች አሁን ባለው የሕዝብ ብዛት ምጥጥን ድጋሚ ቢሰመሩ የሚያመጡት የውክልና መጠን ግምት (ዝርዝሩን መስመሮቹ ላይ ክሊክ በማድረግ ይመልከቱ)

በኢትዮጵያ ስታስቲክስ አገልግሎት የሕዝብ ብዛት ግምት መሠረት፣ ኦሮሚያ፣ አፋር፣ ትግራይ እና ድሬዳዋ ከአጠቃላይ የአገሪቱ ሕዝብ ቁጥር አንጻር ከፍ ያለ የሕዝብ ድርሻ ዕድገት አሳይተዋል። በዚህ መሠረት በሕዝብ ብዛት ዕድገታቸው ልክ የፓርላማ መቀመጫዎች (የምርጫ ክልሎች) እንደገና ቢከፋፈሉ ኖሮ ኦሮሚያ 208፣ ሶማሌ 34፣ አፋር 10.5 እና ድሬዳዋ 3 ወንበሮችን በማግኘት አሁን ካላቸው መቀመጫ ከፍ ያለ ውክልና ይኖራቸው ነበር። በተቃራኒው አማራ 118፣ ትግራይ 30፣ አዲስ አበባ 20 እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ 6 መቀመጫዎችን በማግኘት አሁን ካላቸው ዝቅ ያለ ውክልና ሊኖራቸው እንደሚችል የዳታ ትንታኔው ያሳያል። (ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

ምስጋና፤ በዚህ ልዩ ዘገባ ላይ የተካተቱት ምስላዊ መግለጫዎች (Infographics) በዳታ ፎር ቼንጅ (Data4Change) የቴክኒክ ድጋፍ የተዘጋጁ ናቸው። ለዝግጅት ክፍላችን ጥያቄ ፈጣን ምላሽ በመስጠት ለተደረገልን የነፃ ሙያዊ እገዛ፣ በተለይም የድርጅቱን የሥራ ኃላፊ ብሮንዌን ሮበርትሰን (Bronwen Robertson) እና ኢንፎግራፊክሶቹን ከኢትዮጵያ ኢንሳይደር ቡድን ጋር በመተባበር ያዘጋጁልን ኤላ ሆሎውድን (Ella Hollowood) በዝግጅት ክፍላችን እና በአንባቢዎቻችን ስም ከልብ እናመሰግናለን።