የምርጫ 2018 ዕጩዎች ስብጥር፤ በቁጥር እና በምስላዊ መግለጫ

ግንቦት 19፣ 2018 (ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)፤ የ7ኛው ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ በመጪው ሰኞ፣ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም. ለማካሄድ የሚያስችሉ የመጨረሻ ምዕራፍ ዝግጅቶች እየተደረጉ ነው። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋዊ ሰነዶች እንደሚያመላክቱት፣ ምርጫው ከትግራይ ክልል በስተቀር በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ይከናወናል ተብሎ ይጠበቃል። ለዚሁ አገር ዐቀፍ ምርጫ በድምሩ 50.5 ሚሊዮን መራጮች የተመዘገቡ ሲሆን፣ በተወዳዳሪነት ረገድ ደግሞ በአጠቃላይ 10,432 ዕጩዎች በቦርዱ ይፋዊ የምዝገባ ሰርተፍኬት አግኝተዋል። ከእነዚህ የዕጩ ተወዳዳሪዎች መካከል 2,080ዎቹ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት (የፌዴራል ፓርላማ) መቀመጫዎች የሚፎካከሩ ሲሆን፣ ቀሪዎቹ 8,352 ዕጩዎች ደግሞ ለክልል እና ለከተማ መስተዳድር ምክር ቤቶች የቀረቡ ናቸው።

ይህ ልዩ ምስላዊ ዘገባ የዕጩዎችን ቁጥር እና ስርጭት መሠረት በማድረግ፣ በምርጫ 2018 የሚታየውን አጠቃላይ የውድድር ሁኔታ በጥልቀት ይተነትናል።

ከላይ ያለው የካርታ ምስላዊ መግለጫ እያንዳንዱ ክልል ውስጥ ያሉትን የፌዴራል ፓርላማ እና የክልል/ከተማ ምክር ቤት የምርጫ ክልሎችን ብዛት፣ በየክልሎቹ የተመዘገቡ የገዢው ፓርቲ ዕጩዎችን ቁጥር በድምሩ ያሳያል። የመረጡት ክልል ላይ በመጫን (ክሊክ በማድረግ) ዝርዝሩን ይመልከቱ።

የሥልጣን መንገድ
ብልፅግና ፓርቲ እና ኢዜማ ብቻ ለፌዴራል መንግሥትነት ይፎካከራሉ

በኢትዮጵያ የምርጫ ታሪክ ውስጥ በተከታታይ የተካሄዱ ውድድሮች በአብዛኛው በተወዳዳሪዎች መካከል ባለው ያልተመጣጠነ አቅም የተቃኙ ናቸው። ገዢው ፓርቲ ለፌዴራል ፓርላማም ሆነ ለክልል ምክር ቤቶች ሰፊ የዕጩዎች ስብስብ የሚያቀርብ ሲሆን፣ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ግን በቁጥር ውሱን ዕጩዎችን ይዘው ለመወዳደር ይገደዳሉ። የፖለቲካ ምኅዳሩ ፍትሓዊ ውድድርን ካለመፍቀዱ ባሻገር፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሰፊ መዋቅራዊ አቅም ገንብተው ለሥልጣን በሚያበቃ ቁመት መወዳደር አለመቻላቸው ለዚህ ያልተመጣጠነ የምርጫ ውድድር ዋና አስተዋፅዖ አድርጓል።

በዚህም ሳቢያ ገዢው ፓርቲ በምርጫ 2002፣ 99.6 በመቶ፣ በምርጫ 2007፣ 100 በመቶ፣ እንዲሁም በ6ኛው ጠቅላላ ምርጫ (ምርጫ 2013) 97 በመቶ የሚሆኑትን ውድድር የተደረገባቸው የፓርላማ ወንበሮች ሙሉ በሙሉ በማሸነፍ መንግሥት መመሥረቱ ይታወሳል።

ይህንን ለማካካስ ይመስላል በዘንድሮ ምርጫ ብልፅግና ፓርቲ ለፓርላማ ብቻ በ48 የምርጫ ክልሎች ውስጥ ዕጩዎችን አላቀረበም። ባለፈው ምርጫ ዘንድሮ ብልፅግና ፓርቲን ወክለው የሚወዳደሩት የጠቅላይ ሚኒስትር የማኅበራዊ ጉዳዮች አማካሪ አቶ ዳንኤል ክብረትን ጨምሮ ሌሎችም የግል ተወዳዳሪዎች ብልፅግና ፓርቲ በማይወዳደርባቸው ቦታዎች ተወዳደረው ፓርላማ ገብተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጥር ወር 2018 ለፓርላማ እንደተናገሩት፣ የተቃዋሚዎች ቁጥር በፓርላማው “ከአምስት እስከ አስር እጥፍ” ይጨምራል ብለው ነበር፤ ለዚህም ፓርቲያቸው “ይሁነኝ ብሎ ይሠራበታል” ብለዋል። በተመሳሳይ ብልፅግና ፓርቲ በድምሩ ለ284 የክልል ምክር ቤት ወንበሮችም አይወዳደርም። ብልፅግና ዕጩ ያላቀረበባቸው የክልል ምክር ቤት ወንበሮች በአብዛኛው ከ8 በመቶ እስከ 15 በመቶ የሚደርሱትን ሲሆን፣ ለኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት ግን 1 በመቶ (5 ወንበሮችን) ብቻ ለሚሆነው የክልል ምክር ቤት መቀመጫዎች ዕጩ እንዳላቀረበ ታውቋል። በተቃራኒው ለአዲስ አበባ፣ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ ድሬዳዋ፣ እና ሶማሊ ምክር ቤቶች 15 በመቶ የሚሆኑ መቀመጫዎችን ለቋል።

ይሁን እንጂ ብልፅግና ፓርቲ ለተቃዋሚዎች የፓርላማ እና ምክር ቤቶችን መልቀቁ የምርጫውን ፍትሓዊነት አያረጋግጥም የሚል ትችት ቀርቦበታል። በተቃራኒው ብልፅግና ፓርቲ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያለ ተፎካካሪ የቀረበባቸው የፓርላማ ወንበሮች ብዛት 65 መሆኑ ታውቋል። ከነዚህ ውስጥ አብዛኛዎቹ (46ቱ) በኦሮሚያ እና (11ዱ) በአማራ ክልል መሆናቸው ታውቋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በዘንድሮም መንግሥት ለመመሥረት የሚያስችለውን አነስተኛውን የፓርላማ ወንበር (ከ274 በላይ ዕጩዎችን) ማስመዝገብ የቻሉት ገዢው ብልፅግና ፓርቲ እና የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ብቻ ናቸው። ይሁን እንጂ የኢዜማ መሪ አቶ ኢዮብ መሳፍንት እንደተናገሩት፣ ኢዜማ የፌዴራል መንግሥት ለመመሥረት የሚያስችል የዕጩዎች ቁጥር ያቀረበ ብቸኛው ተቃዋሚ ፓርቲ ቢሆንም፣ በዘንድሮው ውድድር ፓርላማ የሚገቡ ዕጩዎቹን ቁጥር ከማሳደግ ባለፈ፣ አሸናፊ ሆኖ መንግሥት እመሠርታለሁ የሚል ግምት እንዳልያዘ አስታውቀዋል።

ከላይ የቀረበው ምስላዊ መግለጫ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ዕጩዎች ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያሰማሩ 20 ቀዳሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ዝርዝር ያሳያል። በግራፉ ላይ በሐምራዊ ቀለም የተመለከቱት ክፍሎች የየፓርቲዎቹ ዕጩዎች በሚወዳደሩባቸው የምርጫ ክልሎች ውስጥ ሌሎች ተቀናቃኝ ዕጩዎች ባለመመዝገባቸው፣ ያለምንም የፖለቲካ ውድድር ከወዲሁ ማሸነፋቸው የተረጋገጠባቸውን ወንበሮች የሚያመለክት ነው። በብርቱካናማ ቀለም የተገለጹት ደግሞ ዕጩዎች እርስ በርስ የሚፎካከሩባቸውን የውድድር ምኅዳሮች ሲያሳዩ፣ በአመድማ ቀለም የተለዩት ፓርቲዎቹ ዕጩ ሳያቀርቡባቸው የቀሩትን የፓርላማ መቀመጫዎችን ብዛት ይወክላሉ። በመጨረሻም በነጭ ቀለም የተመደቡት ክፍሎች በተለያዩ ምክንያቶች ምርጫ የማይካሄድባቸውን አካባቢዎች የሚያሳዩ ናቸው። (የእያንዳንዱን የምርጫ ክልል ዝርዝር ቁጥር ለመመርመር ቀለማቱን ይጫኑ!)

ከላይ ያለው ምስላዊ መግለጫ እንደሚያሳየው ከብልፅግና ኢዜማ በስተቀር በሁሉም ምርጫ የሚካሄድባቸው ክልሎች እና ከተሞች ውስጥ ለክልል/ከተማ ምክር ቤቶች ዕጩዎችን ያቀረበ ፓርቲ የለም። በዕጩዎች ብዛት ሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት በአፋር፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና ጋምቤላ ክልሎች ለክልላዊ ምክር ቤቶቹ ዕጩ አላቀረበም።

ልክ እንደ 6ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሁሉ፣ የ7ኛው ጠቅላላ አገራዊ ምርጫም በትግራይ ክልል ዘንድሮ እንደማይካሄድ ተረጋግጧል። ቀደም ሲል በነበረው የምርጫ 2013 ሂደት ላይ በተለያዩ ምክንያቶች ምርጫ ሳይካሄድባቸው ቀርተው የነበሩ አካባቢዎች በትግራይ ክልል ሁሉም 38 የምርጫ ክልሎች፣ በአማራ ክልል 19 የምርጫ ክልሎች፣ እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል 8 የምርጫ ክልሎች ሲሆኑ፣ በጥቅሉ 65 የምርጫ ክልሎች በፓርላማ ተወካዮች እንዳልነበራቸው ይታወሳል።

በዘንድሮው የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ምንም እንኳን ግጭቶች እና አለመረጋጋቶች በሚስተዋሉባቸው የኦሮሚያ እና የአማራ ክልሎች በሚገኙ ሁሉም የምርጫ ክልሎች (Constituencies) ውስጥ የዕጩዎች ምዝገባ የተከናወነ ቢሆንም፣ አስተማማኝ ምርጫ ለማካሄድ አስቻይ ያልሆኑ አካባቢዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ በሰፊው ይገመታል። ይህንን ሁኔታ ከግምት በማስገባት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መላ የአገሪቱን የምርጫ ክልሎች በሦስት መደቦች መከፋፈሉን ገልጿል። በዚህም መሠረት ምርጫ ለማካሄድ ሙሉ አስቻይ ሁኔታ ያለባቸውን በአረንጓዴ፣ የጸጥታ ሁኔታቸው ተለዋዋጭ የሆኑትን በቢጫ፣ እንዲሁም ምርጫ ለማካሄድ ፍጹም አስቻይ ያልሆኑትን አካባቢዎች በቀይ ቀለም ለይቶ መያዙን በተደጋጋሚ ሲገልጽ ቆይቷል። ይሁን እንጂ ቦርዱ የትኞቹ የምርጫ ክልሎች በየትኛው ቀለም ሥር እንደተመደቡ ይህ ዘገባ እስከወጣበት ዕለት ድረስ ይፋዊ መግለጫ አልተሰጠም።

ምርጫ ቦርድ በዘጠኝ ቡድኖች አዋቅሮ ወደ ተለያዩ አካባቢዎች የላካቸው አጣሪ ኮሚቴዎች የመስክ ምልከታ ሪፖርታቸውን ግንቦት 10 ቀን 2018 ዓ.ም. ለቦርዱ ዋና መሥሪያ ቤት ማስገባታቸው የታወቀ ሲሆን፣ ቦርዱ ከብሔራዊ የጸጥታ አካላት ጋር የመጨረሻ ውይይት ካደረገ በኋላ የትኞቹ የምርጫ ክልሎች ምርጫ ለማስኬድ “አስቻይ” እንደሆኑ ወይም እንዳልሆኑ በይፋ ያሳውቃል ተብሎ ይጠበቃል። ቦርዱ ትላንት፣ ግንቦት 18 በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ በአማራ ክልል 8 የምርጫ ክልሎች ውስጥ ምርጫ እንደማይካሄድ ቢገልጽም፣ የትኞቹ የምርጫ ክልሎች እንደሆኑ በዝርዝር አልገለጸም።

በሌላ በኩል፣ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ሚያዝያ 21 ቀን 2018 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረበው እና “ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ለመመልከት የቻለችው የስጋት ትንተና እንደሚያመላክተው፣ በአማራ ክልል ከሚገኙት ጠቅላላ የምርጫ ጣቢያዎች መካከል 24.9 በመቶ የሚሆኑት ከፍተኛ ስጋት ያለባቸው በመሆኑ በቀይ ቀለም ተለይተው ነበር። በተመሳሳይ መልኩ 24.4 በመቶ የሚሆኑት ጣቢያዎች የጸጥታ ሁኔታቸው አስተማማኝ ባለመሆኑ “ቢጫ” ቀለም የተቀለሙ ሲሆን፣ ምንም ዓይነት የጸጥታ ስጋት የሌለባቸው እና በአረንጓዴ ቀለም የተለዩት የምርጫ ጣቢያዎች ግን 50.6 በመቶ መሆናቸውን ሰነዱ በግልጽ ያሳያል። በጥቅሉ ስምንት ክልሎች ስጋት የሌለባቸው (“አስቻይ” ወይም አረንጓዴ) ተብለው ሲለዩ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ 96.7%፣ በኦሮሚያ 98.5%፣ በጋምቤላ 51.5% እና በማዕከላዊ ኢትዮጵያ 99.6% በመቶ የሚሆኑት የምርጫ ጣቢያዎች ስጋት የሌለባቸው ናቸው ተብሎ ነበር። ፌዴራል ፖሊስ ከዚያ በኋላ የተለወጠ የስጋት ትንታኔ ስለማዘጋጀቱ “ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” መረጃ ማግኘት አልቻለችም።

ከላይ የቀረበው ምስላዊ መግለጫ በየክልሉ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና ለክልል/ከተማ ምክር ቤቶች የቀረቡ ዕጩዎችን ድርሻ በመቶኛ ያሳያል። ከላይ በስተግራ ያለውን ክልል መምረጫ በመጠቀም፣ የየክልሉን ዝርዝር የፖለቲካ ፓርቲዎች ዕጩ መረጃ መመልከት ይችላሉ። በሐምራዊ ቀለም የተመለከቱት ተፎካካሪ የሌለባቸው ዕጩዎች ብዛት ሲሆን፣ ከላይ ወደታች የተሰመሩት መሥመሮች ደግሞ ፓርቲዎቹ ያቀረቧቸው ዕጩዎች ብዛት ከምክር ቤቶቹ መቀመጫዎች ብዛት አንፃር ያላቸውን ድርሻ ያመለክታል። በመግለጫው ላይ እንደሚስተዋለው፣ በጋምቤላ ለክልል ምክር ቤቶች 5 እና ለፓርላማ 4 የፖለቲካ ፓርቲዎች ብቻ ዕጩዎች ያስመዘገቡበት ክልል በመሆን ጥቂት የፖለቲካ ፓርቲዎች ብቻ የሚሳተፉበት ክልል ሆኗል።

የክልል ምክር ቤቶች ውድድር
ብልፅግና ፓርቲ በአምስት ክልሎች ያለ ጠንካራ ፉክክር ይወዳደራል

መጪው የክልል ምክር ቤቶች ምርጫ ገዢው ብልፅግና ፓርቲ በአምስት ክልሎች እና በአንድ የከተማ መስተዳድር ውስጥ ያለ ምንም ጠንካራ የፖለቲካ ፉክክር ብቻውን የሚወዳደርበት ሆኗል። በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በጋምቤላ፣ በሐረሪ ክልሎች እና በድሬዳዋ ከተማ መስተዳድር ምክር ቤቶች ካሏቸው ጠቅላላ መቀመጫዎች መካከል ከግማሽ በላይ ዕጩዎችን በማቅረብ መንግሥት የመመሥረት የቁጥር አቅም ይዞ የቀረበው ገዢው ብልፅግና ፓርቲ ብቻ ነው።

በአንጻሩ ሲዳማ እና አፋር ክልሎች እንዲሁም የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ምክር ቤቶች ከፍተኛ የፓርቲዎች ፉክክር እና ልዩ የአሰላለፍ ገጽታ የሚጠበቅባቸው መድረኮች ሆነዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ደግሞ ገዢው ብልፅግና ፓርቲ በተወዳዳሪ ዕጩዎች ቁጥር በሁለት የፖለቲካ ፓርቲዎች የተበለጠበት ብቸኛው ምክር ቤት ሆኗል። ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት ለ143 መቀመጫዎች ዕጩዎችን በማስመዝገብ ቀዳሚ ሲሆን፣ ሕዳሴ ፓርቲ በ142፣ ብልፅግና በ134 እና ኢዜማ በ106 ዕጩዎች ይከተላሉ። በአጠቃላይ 20 የፖለቲካ ፓርቲዎች ዕጩዎቻቸውን ያቀረቡበት የአዲስ አበባ ምክር ቤት በፓርቲዎች ብዛት ሰፊ ውድድር ያስተናግዳል። በአፋር ክልል ከ142 መቀመጫዎች ውስጥ ብልፅግና 129፣ የአፋር ሕዝብ ፓርቲ 96፣ የአፋር ነፃ አውጪ ግንባር 78 እና አርጎባ አንድነት 72 ዕጩዎችን አቅርበዋል።

በተቀሩት አራት ክልሎች ደግሞ ውድድሩ ገዢውን ፓርቲ ጨምሮ በሁለት እና በሦስት የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ብቻ የተገደበ ሆኖ ተመዝግቧል። በጥቅሉ፣ ገዢው ብልፅግና ፓርቲ ምርጫ ከማይካሄድበት ከትግራይ ክልል ውጪ በሁሉም ምክር ቤቶች መንግሥት የመመሥረት አቅም ይዞ ብቻውን ሲንቀሳቀስ፣ ከእርሱ ውጪ ይህንን የቁጥር አቅም ያገኙት ኢዜማ በአምስት ክልሎች፣ ትብብር ደግሞ በሦስት ክልል ምክር ቤቶች ላይ ብቻ ነው።

ከላይ የቀረበው ምስላዊ መግለጫ የየክልሎቹን እና የከተማ መስተዳድሮቹን የፓርላማ እንዲሁም የክልል/ከተማ ምክር ቤት የምርጫ ክልሎችን የፉክክር ደረጃ በግልጽ ያሳያል። በምስላዊ መግለጫው ላይ በብርቱካናማ ቀለም የተመለከቱት ክፍሎች ከአንድ በላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዕጩዎችን ያቀረቡባቸውን እና ፉክክር የሚካሄድባቸውን የምርጫ ክልሎች የሚያሳዩ ናቸው። በአንጻሩ በአመድማ ቀለም የተለዩት ክፍሎች የሌሎች ፓርቲዎች ተቀናቃኝ ዕጩዎች ባለመመዝገባቸው ምክንያት፣ የአንድ ፓርቲ ዕጩዎች ብቻ ያለ ምንም ተፎካካሪ የሚወዳደሩባቸውን እና ከወዲሁ ማሸነፋቸው የተረጋገጠባቸውን የምርጫ ክልሎች ብዛት በጉልህ ያመለክታሉ። (ማስታወሻ፤ አንድ የፓርላማ የምርጫ ክልል አንድ የፓርላማ መቀመጫ ብቻ ያለው ሲሆን፣ አንድ የክልል ምክር ቤቶች የምርጫ ክልል ግን ከአንድ በላይ የምክር ቤት መቀመጫዎች ይኖሩታል።)

የቀድሞው ደቡብ ክልል
በርካታ ፓርቲዎች በርካታ ዕጩ የወከሉበት ቀጠና

ቀድሞ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት (ደቡብ ክልል) ተብሎ ይጠራ የነበረው እና አሁን ወደ አራት ራሳቸውን የቻሉ ክልሎች (ሲዳማ፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ ኢትዮጵያ እና ማዕከላዊ ኢትዮጵያ) የተከፋፈለው ሰፊ አካባቢ፣ ከሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች በተለየ ሁኔታ በርከት ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሰፊ የዕጩዎች ስብስብ ያስመዘገቡበት ልዩ ቀጠና ሆኗል። በአንፃሩ እጅግ በርካታ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎች ያሏቸው የኦሮሚያ እና የአማራ ክልሎች፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በሙሉ አቅማቸው መሳተፍ ባለመቻላቸው ሳቢያ ገዢው ብልፅግና ፓርቲ ብቻውን ያለምንም የጎላ ስጋት የሚወዳደርባቸው ሆነዋል።

በአዲሱ አሰላለፍ መሠረት በሲዳማ ክልል ካሉት 190 የክልል ምክር ቤት መቀመጫዎች መካከል ቢያንስ ግማሹን (95 ወንበሮችን) መሙላት የሚችሉ ዕጩዎችን በሙሉ አቅም ማቅረብ የቻሉ ሰባት የፖለቲካ ፓርቲዎች በመመዝገባቸው፣ ክልሉ በአገር አቀፍ ደረጃ በከፍተኛ ውድድር ቀዳሚነቱን ይዟል። በዚህም ብልፅግና ፓርቲ በ175 ዕጩዎች ሲመራ፣ መድረክ በ162፣ ትብብር በ148፣ ኢዜማ በ146፣ የሲዳማ ሕዝብ አንድነት ዴሞክራሲያዊ ድርጅት በ141፣ ሲዳማ አንድነት ፓርቲ በ106 እና ነእፓ በ96 ዕጩዎች ይከተላሉ። በተመሳሳይ መልኩ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ብልፅግና እና ኢዜማ እኩል 144 ዕጩዎችን ሲያስመዘግቡ፣ ነእፓ በ91 ዕጩዎች ይፎካከራቸዋል። በደቡብ ኢትዮጵያ ደግሞ ብልፅግና 201፣ ኢዜማ 169 እና ትብብር 141 ዕጩዎችን በውድድር ምኅዳሩ አሰልፈዋል። በማዕከላዊ ኢትዮጵያም ብልፅግና 148 እና ኢዜማ 104 ዕጩዎችን ማቅረብ ችለዋል።

ይህ የደቡብ አዲሶቹ ክልሎች የፉክክር ትኩሳት ከሌሎች አካባቢዎች ጋር ሲነጻጸር በእጅጉ የተለየ ነው፤ ለምሳሌ በሶማሊ ክልል ውድድሩ በብልፅግና (232 ዕጩዎች) እና በኦብነግ (161 ዕጩዎች) መካከል ብቻ የተገደበ ሲሆን፣ በድሬዳዋ ከተማ መስተዳድር ምክር ቤት ደግሞ ካሉት 47 የምርጫ ክልሎች በ37ቱ እንዲሁም ከ189 ጠቅላላ መቀመጫዎች ውስጥ ለ92ቱ ገዢው ብልፅግና ፓርቲ ብቻውን ያለ ምንም ተፎካካሪ ቀርቧል።

ከላይ የሚታየው የካርታ ምስላዊ መግለጫ የፌዴራል ፓርላማ እና የክልል/ከተማ ምክር ቤቶች ፖለቲካ ፓርቲዎች መንግሥት ለመመሥረት በሚያስችል አቅም፣ ማለትም ከግማሽ በላይ ለሚሆኑ መቀመጫዎች ዕጩዎችን በማቅረብ የሚወዳደሩባቸውን እና የቁጥር አቅም አጥተው የማይወዳደሩባቸውን ክልሎች በግልጽ ያሳያል። አንባቢዎች በምስላዊ መግለጫው ከላይ በስተግራ በኩል ያለውን አማራጭ በመጫን የፌዴራል ፓርላማ ወይም የክልል ምክር ቤቶችን መደብ መምረጥ የሚችሉ ሲሆን፣ የየክልሎቹን የካርታ አካል በመጫን ዝርዝር መረጃዎቹን እና የፓርቲዎቹን የዕጩዎች ስርጭት መመርመር ይችላሉ።

የዕጩዎች ምዝገባ
ከዲጂታል ምዝገባ ስርዓት እስከ ራስን ማግለል

7ኛው ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ፣ የዲጂታል የምዝገባ ስርዓትን በማስተዋወቅ የመጀመሪያው ነበር። የዕጩዎች ምዝገባ ሙሉ ለሙሉ በዲጂታል ስርዓት ሲከናወን፣ የመራጮች ምዝገባ ደግሞ አዲስ አበባን ጨምሮ በተመረጡ አካባቢዎች በዲጂታል ስርዓት ሲካሄድ፣ በሌሎቹ ደግሞ በቀድሞው አሠራር በማኑዋል ተዘጋጅቷል።

የዲጂታል ምዝገባ ማነቆዎች እና የዕጩዎች ምዝገባ ሁኔታ

የዘንድሮው የዕጩዎች ምዝገባ ሂደት በዲጂታል አማራጭ መከናወኑ እና የብሔራዊ መታወቂያ (National ID) እንደ አስገዳጅ ቅድመ ሁኔታ መቀመጡ፣ ለፓርቲዎች ከአቅም በላይ የሆነ ፈተና መፍጠሩን አመራሮቹ ለ“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” በተደጋጋሚ ገልጸዋል። በትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት በኩል መስፈርት ያሟሉ ከ255 እስከ 300 የሚደርሱ ዕጩዎች በዲጂታል ምዝገባው ሥርዓት መስተጓጎል ሳቢያ ሳይመዘገቡ ከውድድር ውጪ ሆነዋል። በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ፓርቲ (ኢብአፓ) አባላቱ የብሔራዊ መታወቂያ ባለማውጣታቸው ምክንያት ያቀረባቸው ዕጩዎች ቁጥር ከ1,100 ወደ 167 ማሸቆልቆሉን ሲያሳውቅ፣ የነፃነት እና እኩልነት ፓርቲ (ነእፓ) በበኩሉ 250 የሚሆኑ ዕጩዎቹ በተመሳሳይ ምክንያት ሳይመዘገቡለት መቅረታቸውንና መጀመሪያ ላይ ለመመዝገብ የብሔራዊ መታወቂያ ግዴታ መሆኑን አለማወቃቸውን ገልጿል።

የፀጥታ ጉዳይ በዕጩዎች ላይ ያሳደረው ተፅዕኖ

የፀጥታው መበላሸት ፓርቲዎች በሙሉ አቅማቸው ዕጩ እንዳያቀርቡ እና የምርጫ ዝግጅት እንዳያደርጉ ትልቅ ሥነ-ልቦናዊ ጫና ፈጥሯል። ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በአዘዞ ክፍለ ከተማ የምርጫ ምዝገባ ሲያስተባብሩ የነበሩ ሚሊሺያዎች መገደላቸውን ተከትሎ ድርጊቱ ከፍተኛ ፍርሃት እንደፈጠረበትና አማራ፣ ትግራይ፣ ከፊል ኦሮሚያ እና የመተከል ዞን ለምርጫ አስቸጋሪ መሆናቸውን አስታውቋል። በሌላ በኩል፣ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ፕሬዝዳንት አቶ ዳውድ ኢብሳ የሚወዳደሩበት የሆሮ ጉድሩ አካባቢ ባለው የጸጥታ ስጋት ምክንያት ከዘንድሮው ውድድር ውጭ መሆናቸውን ፓርቲው የገለጸ ሲሆን፣ ድርጅቱ ከነበሩት 230 ቢሮዎች ውስጥ በአሁኑ ወቅት ክፍት የሆነው የአዲስ አበባው ቢሮ ብቻ መሆኑም የዕጩዎች ቁጥሩን በእጅጉ እንደገደበው አረጋግጧል።

አስተዳደራዊ እና ፖለቲካዊ ጫናዎች

በተወዳዳሪ ዕጩዎች ላይ የሚደርሱ እስራቶች፣ ቅስቀሳ ማስተጓጎል እና ሌሎችም አስተዳደራዊ ክልከላዎች በተለይ በደቡብ ክልል አካባቢዎች በስፋት ተስተውለዋል። የሰላም ለኢትዮጵያ ጥምረት የመንግሥት የፀጥታ አካላት በጋሞ ዞን ዕጩዎችን በማሰር፣ ከሥራ በመባረርና ደመወዝ በመከልከል ወከባ እያደረሱባቸው መሆኑን ሲገልጽ፣ የዎሕነን ፓርቲ ደግሞ 45 ሺህ የምርጫ ምልክቶቹ በመንግሥት አካላት መነሳታቸውንና የቅስቀሳ እንቅፋት እንደተፈጠረበት ተናግሯል። በተጨማሪም የቁጫ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቁሕዴፓ) አመራሮች ወደ ቁጫ ወረዳ ለቅስቀሳ ሲያቀኑ “በሕገ-መንግሥቱ ዕውቅና የሌለው የብሔር አልባሳት ለብሳችኋል” በሚል በፀጥታ ኃይሎች መከልከላቸው ሲታወስ፣ በሐረሪ ክልል ደግሞ የኢዜማ እና የትብብሩ የክልል ምክር ቤት ዕጩዎች “የብሔረሰቡ ተወላጅ አይደሉም” በሚል በፍርድ ቤት ውሳኔ መሰረዛቸው የታወቀ የጫና ማሳያ ነው።

የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጣዊ ክፍፍሎች

የፓርቲዎች ውስጣዊ መከፋፈልና ተከታታይ የፍርድ ቤት ክርክሮች በርካታ ዕጩዎች ከምርጫው ሂደት ውጪ እንዲሆኑ አድርጓል። ለኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) በዶ/ር ራሔል ባፌ አማካይነት በዲጂታል ሲስተም ተመዝግበው የነበሩት 309 ዕጩዎች በሙሉ፣ በእነ አቶ አጫሞ ቦቄ በቀረበባቸው ክስ እና የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሁለቱንም ወገን ዕጩዎች ውድቅ በማድረጉ ምክንያት ፓርቲው ሙሉ በሙሉ ከዘንድሮው ምርጫ ውጪ ሆኗል። በተመሳሳይ የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ያደረገውን ብሔራዊ ጉባኤ ምርጫ ቦርድና ፍርድ ቤት ውድቅ ማድረጋቸውን ተከትሎ የዕጩዎቹ መፅደቅ ጥያቄ ውስጥ ሲወድቅ፣ የሲዳማ አርነት ንቅናቄ (ሲአን) ደግሞ በሰበር ችሎት ውሳኔ መሠረት ዕጩ ያስመዘገበው የፓርቲው አመራር ቡድን የተመረጠበት ጠቅላላ ጉባዔ ሕጋዊ ቅቡልነት እንደሌለው ተናግሮ በድጋሚ እንዲካሄድ ወስኗል። ይሁንና ምርጫ ቦርድ ለኅትመት የላካቸው የድምፅ መስጫ ወረቀቶች ክርክር የተነሳባቸውን የባልደራስንም ይሁን የሲአንን ዕጩዎች እንደሚጨምር ታውቋል።

የዕጩዎች ራስን ማግለል

የምርጫው ዕለት እየተቃረበ በመጣበት በአሁኑ ወቅት፣ ዕጩዎች በተናጥል ራሳቸውን ከውድድር ማግለላቸው በሂደቱ ላይ ሌላ መልክ አሳይቷል። ሰሞኑን የትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት ዕጩዎች የሆኑት አቶ ይሳቅ ወልዳይ እና አቶ ኤፍሬም ካሳ ራሳቸውን ማግለላቸው የተሰማ ሲሆን፣ ምርጫ ቦርድ ግን የድምፅ መስጫ ወረቀቶች ታትመው በመግባታቸው ከሚያዝያ 23 በኋላ የሚመጡ ማግለሎችን በሕግ እንደማይቀበል አስታውቋል። ይሁን እንጂ ይህ ዓይነቱ ራስን የማግለል ሂደት በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በጉራጌ ዞን እዣ 01 የምርጫ ክልል በከፍተኛ ቁጥር የተደገመ ሲሆን፣ የኢዜማ ሁለት ዕጩዎች (ቤዛዓለም ድንቁ እና ጌቱ ግርማ) እንዲሁም የጎጎት ሦስት ዕጩዎች (ደምስስ ገብሬ፣ በፍቃዱ ደግሰው እና ትዕግስቱ ደሣለኝ) በገዢው ፓርቲ “በሚደርስባቸው ወከባና ማስፈራሪያ” ሳቢያ ራሳቸውን ማግለላቸው ታውቋል። [ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር]


ማስታወሻ፤ ሁሉም የዕጩዎች ቁጥር መረጃዎች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሚያዝያ 29፣ 2018 በድረገጹ ይፋ ባደረገው የዕጩዎች ዝርዝር ላይ የተመሠረቱ ናቸው። ከዚያ በኋላ በተለያዩ ምክንያቶች የተቀየሩ መረጃዎች ቢኖሩ፣ እንዳልተካተቱ ግንዛቤ እንዲወሰድ እናሳስባለን።

ምስጋና፤ በዚህ ልዩ ዘገባ ላይ የተካተቱት ምስላዊ መግለጫዎች (Infographics) በዳታ ፎር ቼንጅ (Data4Change) የቴክኒክ ድጋፍ የተዘጋጁ ናቸው። ለዝግጅት ክፍላችን ጥያቄ ፈጣን ምላሽ በመስጠት ለተደረገልን የነፃ ሙያዊ እገዛ፣ በተለይም የድርጅቱን የሥራ ኃላፊዎች ብሮንዌን ሮበርትሰን (Bronwen Robertson) እና ኤላ ሆሎውድን (Ella Hollowood) በዝግጅት ክፍላችን እና በአንባቢዎቻችን ስም ከልብ እናመሰግናለን።