ምርጫ ቦርድ በአማራ ክልል በ8 የምርጫ ክልሎች ምርጫ እንደማይደረግ ሲገልጽ፣ በኦሮሚያ ግን በሁሉም የምርጫ ክልሎች እንደሚካሄድ አሳወቀ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ በአማራ ክልል በሚገኙ ስምንት የምርጫ ክልሎች ውስጥ በመጪው ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም. የታቀደው ጠቅላላ ምርጫ እንደማይካሄድ በይፋ አሳወቁ። ሰብሳቢዋ ይህንን የገለጹት ቦርዱ ዛሬ፣ ግንቦት 18 ቀን የቅድመ ምርጫ ሂደቱ ማገባደጃ ሥራዎችን አስመልክቶ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው።

ቦርዱ በአማራ ክልል በ8 የምርጫ ክልሎች ምርጫ እንደማይካሄድ ቢገልጽም፣ በኦሮሚያ ክልል እስካሁን ባለው ሁኔታ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስቸግር ምንም ዓይነት መዋቅራዊ ችግር አለመኖሩን የጠቆሙት ሰብሳቢዋ፣ በክልሉ ካሉት 178 የምርጫ ክልሎች ውስጥ ከአረንጓዴ እና ቢጫ ውጪ በከፍተኛ ስጋትነት “በቀይ” ቀለም የተፈረጀ የምርጫ ክልል አለመኖሩን አረጋግጠዋል።

ቦርዱ ቀደም ሲል የምርጫ ክልሎችን የጸጥታ ሁኔታ መሠረት በማድረግ በአረንጓዴ፣ በብጫ እና በቀይ ቀለማት ከፍሎ መከታተሉ ይታወሳል።

በአማራ ክልል ምርጫ የማይደረግባቸው ተብለው የተለዩት ስምንት የምርጫ ክልሎች በደቡብ ጎንደር፣ በምዕራብ ጎንደር፣ በደጋ ዳሞት እና በአምባሰል አካባቢዎች የሚገኙ መሆናቸው ተገልጿል።

ቦርዱ ቀደም ሲል የጸጥታ ሁኔታን የሚያጠኑ ዘጠኝ ቡድኖችን ወደ ተለያዩ አካባቢዎች የላከ ሲሆን፣ በአማራ ክልል የተሰማራው ቡድን በባሕር ዳር፣ በጎንደር እና በጎጃም የተለያዩ የምርጫ ክልሎች ተንቀሳቅሶ ያጠናቀቀውን ሪፖርት መሠረት በማድረግ ይህ ውሳኔ መተላለፉን ሰብሳቢዋ ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ ቦርዱ ግንቦት 6 ቀን 2018 ዓ.ም. ባካሄደው የጸጥታ ሁኔታ ውይይት ላይ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች “97 በመቶ ምርጫ ለማድረግ አስቻይ ሁኔታ አለ” በሚል የቀረበው ይፋዊ ሪፖርት፣ በትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት (ትብብር) ጥምረት በኩል “ሪፖርቱን አንቀበለውም” በሚል ጽኑ ተቃውሞና በፓርቲዎች መካከል ከፍተኛ ጭቅጭቅ ማስነሳቱ ይታወሳል።

ሰብሳቢዋ ሜላትወርቅ ኃይሉ ለዚሁ ቅሬታ በሰጡት ማብራሪያ፣ በወቅቱ የቀረበው ሪፖርት ቀጣይነት ባለው መልኩ ክትትል የሚደረግበት መሆኑን ጠቅሰው፣ ለምሳሌ በቤኒሻንጉል-ጉሙዝ ክልል በመራጮች ምዝገባ ላይ በደረሰ ጥቆማ መሠረት የተወሰኑ የምርጫ ጣቢያዎችን በጊዜያዊነት መዝጋታቸውን እንደ ማሳያ አንስተዋል።

የጸጥታ ሁኔታ እስከ ድምፅ መስጫው ዕለት ድረስ ተለዋዋጭ ሊሆን ስለሚችል፣ ቦርዱ ሂደቱን እስከ መጨረሻው ሰዓት እየተከታተለ ውሳኔዎችን ያስተላልፋል ብለዋል። ከዚህ ባለፈ፣ በመራጮች ምዝገባ ወቅት ሕጋዊ አሠራርን ሳይከተሉ ሲሠሩ የነበሩ ጣቢያዎችን የመዝጋት ሥራ መከናወኑን ቦርዱ አስታውቋል።

በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በቤኒሻንጉል-ጉሙዝ እና በሶማሊ ክልሎች ውስጥ የተወሰኑ የምርጫ ጣቢያዎች የተዘጉ ቢሆንም፣ በእነዚህ ጣቢያዎች የተመዘገቡ መራጮች መብታቸው ተጠብቆ በድምፅ መስጫው ዕለት ምዝገባቸው ተረጋግጦ እንዲመርጡ ይደረጋል ተብሏል።

በዕጩዎች ምዝገባ ረገድ፣ ከዘጠኝ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተወጣጡ 80 ዕጩዎች ማሟላት የሚገባቸውን መስፈርት ባለማሟላታቸው ምዝገባቸው በዲጂታል ሥርዓቱ ውድቅ መደረጉ ተገልጿል። ለ“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጥያቄ ምላሽ የሰጡት ሰብሳቢዋ፣ ይህ የ80 ዕጩዎች ስረዛ በሲስተም ስህተት እና በፎርማሊቲ ችግር ብቻ የሆነ እንጂ፣ በፓርቲ አመራሮች አለመግባባት ምክንያት የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) ፍርድ ቤት ተከራክሮ ከ309 በላይ ዕጩዎቹ ከተሰረዙበት ይዘት ጋር ፍጹም የተለያየ መሆኑን አስረድተዋል።

በተመሳሳይ የትብብር ጥምረት “ከ200 በላይ ዕጩዎቼን መመዝገብ አልቻልኩም” በሚል ላቀረበው ቅሬታ ቦርዱ ባደረገው ማጣራት፣ በተጨባጭ ሳይመዘገቡ የቀሩት አምስት ዕጩዎች ብቻ መሆናቸውን ሰብሳቢዋ ጠቁመዋል።

በመጨረሻም፣ የምርጫ ቁሳቁሶችን የማሸግ ሥራ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ በአብዛኞቹ የምርጫ ክልሎች የድምፅ መስጫ ወረቀቶች መሰራጨት መጀመራቸውን ቦርዱ አረጋግጧል። በቀጣዮቹ አራት ቀናት ውስጥ ሁሉም የድምፅ መስጫ ቁሳቁሶች ወደየምርጫ ጣቢያዎቹ ይደርሳሉ ተብሎ ይጠበቃል። ይሁን እንጂ በአማራ ክልል ካሉት የምርጫ ክልሎች ውስጥ በ10ሩ የምርጫ ክልሎች ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ምክንያት በታቀደው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት የምርጫ ቁሳቁስ ማድረስ እንዳልተቻለ ሰብሳቢዋ አልሸሸጉም።

በፋይናንስ ረገድ ቦርዱ ከሰባት የተለያዩ አገራት የ7 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ማግኘቱን የገለጸ ሲሆን፣ በተጨማሪም የአውሮፓ ኅብረት የምርጫውን ሂደት ለማገዝ የገንዘብ እና የቴክኒክ ድጋፍ እያደረገ መሆኑ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ተመልክቷል። [ምርጫ 2018 -ኢትዮጵያ ኢንሳይደር]