የዎላይታ ሕዝቦች ነፃነት ንቅናቄ (ዎሕነን) ፕሬዝዳንት ዶክተር ወልደማርያም ልሳኑ ከ“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ “በመንግሥት አካላት ምክንያት ፓርቲው የምርጫ ምልክቱን መለጠፍ እና ቅስቀሳ ማካሄድ አልቻለም” ብለዋል። “45 ሺህ የምርጫ ምልክቶችን ለጥፈን የአካባቢው የመንግሥት አካላት ወዲያውኑ አንስተውብናል” በማለት፣ “ጣልቃ ገብነቱ የማይቆም ከሆነ ከ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ፉክክር እንወጣለን” ሲሉ ቅሬታቸውን አሰምተዋል።
“የመንግሥት አካላት ናቸው” ያሏቸው ሰዎች የፓርቲውን ዕጩዎች ከሥራ የማባረር እና አስሮ የማዋል ነገር እየፈጸሙ እንደሆነ የገለጹት ዶ/ር ወልደማርያም፣ “በተለይም የምርጫ ምልክታችንን መለጠፍ አልቻልንም” ብለዋል። እንዲህ ዓይነት ድርጊቶች በዋናነት የሚፈጸሙት ደግሞ የፓርቲው ፕሬዝዳንት በሚወዳደሩበት ዳሞት ጋሌ ወረዳ ዋንዳራ ቦሎሶ ቀበሌ እንደሆነም አስታውቀዋል።

“መጋቢት 24/ 2018 ዓ.ም 2 መቶ 70 የምርጫ ምልክቶችን ለጥፈን ወዲያውኑ ከሥር ከሥር የመንግሥት አካላት የተለጠፉትን ምልክቶች በማንሳት በተከለከሉ ቦታዎች ላይ ማለትም ቤተ ክርስቲያንና ትምህርት ቤቶች ላይ በመለጠፍ ስማችንን የማጥፋት ሙከራ አድርገዋል” ሲሉ አክለዋል። በዚህም ምክንያት የምርጫ ምልክቱን መለጠፍ እንዳልቻለ የገለጹት የፓርቲው ፕሬዝዳንት፣ ይኼ ዓይነቱ ተግባር በዋናነት በቀበሌዎች ላይ እንደሚስተዋልና በተለይም ሙንደጃ ሳክሬ ቀበሌ፣ ምርጫ ክልል 02 ላይ “ምልክት ሊለጥፉ የሄዱ ሁለት ሰዎችን የቀበሌው አመራሮች አስረዋቸው ከብዙ ጥረት በኋላ አስፈትተናል” ብለዋል።
በተመሳሳይ ሰኞ መጋቢት 28/2018 ዓ.ም ዎሕነን በዎላይታ ዞን ዳሞት ጋሌ ወረዳ ዋንዳራ ቦሎሶ ቀበሌ 45 ሺህ የምርጫ ምልክቶችን ለጥፎ በቀበሌ አመራሮች ትዕዛዝ የምርጫ ምልክቶቹ እንደተነሱበት አስታውቋል። ጉዳዩን ለምርጫ ቦርድ ደቡብ ኢትዮጵያ ቅርንጫፍ ማሳወቃቸውን የተናገሩት ዶክተር ወልደማርያም፣ መሰል ድርጊቶች ግን መቀጠላቸውን በመጥቀስ ከምርጫው ሙሉ በሙሉ ሊወጡ እንደሚችሉ ፍንጭ ሰጥተዋል።
“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጉዳዩን ለማጣራት የምርጫ ቦርድ የደቡብ ኢትዮጵያ ቅርንጫፍ ኃላፊ አቶ አብርሃም አንጄሎን ጠይቃለች። አቶ አብርሃም ቅሬታው ከፓርቲው እንደደረሳቸው ገልጸው “ድርጊቱ እውነት ሆኖ ከተገኘ” ቦርዱ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ ተናግረዋል።

“በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አዋጅ ቁጥር 1162/2011 መሠረት ማንኛውም ከቦርዱ ዕውቅና የተሰጠው ፓርቲ በተፈቀዱ ቦታዎች ላይ [የቅስቀሳ መልዕክቶችን] መለጠፍ ይችላል” ያሉት ኃላፊው፣ ይሁን እንጂ በተከለከሉ ቦታዎች ላይ የምርጫ ምልክት መለጠፍ እንደማይቻል አስረድተዋል። ቦርዱ ከፓርቲው የደረሰውን ቅሬታ እየተመለከተው እንደሆነ እና በሰው እንዲሁም በቪዲዮ ማስረጃዎች አማካኝነት ከፍትሕ አካላት ጋር በመሆን አጣርቶ ድርጊቱን የፈጸመው አካል ላይ ተገቢውን ቅጣት እንደሚጥልበት፣ “ድርጊቱን ሌላ የፖለቲካ ፓርቲ ፈጽሞት ከተገኘም ከምርጫው እስከ ማገድ የሚደርስ ቅጣት ቦርዱ ያስተላልፋል” ብለዋል።
ዎሕነን ምስረታውን በ2015 ዓ.ም ያደረገ ሲሆን በዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ ላይ በአገር አቀፍ ደረጃ እንደሚወዳደር አስታውቋል። በዚህም በ8 ክልሎች እና ሁለት ከተማ መስተዳድሮች 292 ዕጩዎችን አስመዝግቧል። ከዚህም ውስጥ 63 ዕጩዎችን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረበ ሲሆን፣ ቀሪዎቹ ለክልል ምክር ቤቶች የቀረቡ ናቸው። ዎሕነን የሚወዳደርባቸው ክልሎች ደቡብ ኢትዮጵያ፣ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ ምዕራብ፣ ሲዳማ፣ ኦሮሚያ፣ አማራ፣ አፋር፣ እና ሶማሌ ክልሎች እና የአዲስ አበባ እና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች ናቸው።
ዶ/ር ወልደማርያም፣ ዎሕነን የሚከተለው ርዕዮተ ዓለም “አብዮታዊ ዴሞክራሲ” እና “ልማታዊ መንግሥት” መሆኑን በመግለጽ፣ “በአገር ደረጃ ያለው የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ፣ የውጭ ግንኙነት፣ የማኅበራዊ ልማትና ደኅንነት ስጋት ላይ በመውደቁ ዜጎች እየተሰቃዩ ይገኛሉ” በማለት ፓርቲያቸው እነዚህን ችግሮች የመፍታት ዓላማ እንዳነገበ ገልጸዋል። ከኢኮኖሚ አኳያ “ሰው ተኮር ፍትሐዊ ልማት ለኢትዮጵያ ነፃነት” በሚል መርሕ እንሠራለን ብለዋል።
“የሕዝቦች ደኅንነት እና የሰላም ተስፋ እየተሟጠጠ በመገኘቱ እና 60 በመቶ በሚሆነው የአገሪቱ ክፍል የሚገኘው ዜጋ ተረጋግቶ መሥራት እየቻለ ባለመሆኑ፣ ዜጎች ከሥራ ወደ ጦርነት እንዲያዞሩ አድርጓል” ያሉት ፕሬዝዳንቱ፣ ተገንብተው የነበሩ ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪ አልባ የሆኑበትን ሁኔታ እንደሚታገሉም ገልጸዋል። በሌላ በኩል የከተማን የኑሮ ውድነት ማሻሻል እና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ወገኖች መታደግ የዎሕነን ትኩረት መሆኑን ፕሬዝዳንቱ አመልክተዋል። “ተሠርተው የነበሩ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንዱስትሪዎች በኮሪደር ልማት ሰበብ ፈርሰው ወደ ከተማ ዳር እንዲወጡ ተደርገው የኑሮ ውድነቱ እንዲባባስ ሆኗል” ሲሉ የኮሪደር ልማቱን ሂደት ተችተዋል።
“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ፓርቲው በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ምን ለማሳካት አቅዷል ስትል ላነሳችላቸው ጥያቄ፣ ዶ/ር ወልደማርያም ልሳኑ “ፍትሐዊ እና አካታች የሆነ ሰው ተኮር ልማትን እንተገብራለን” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። ዎሕነን በአምስት ዓመት ውስጥ አሥር ሚሊዮን የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ገልጾ፣ ይህንንም ለማሳካት የአገሪቱን እምቅ አቅም መለየት፣ ወጣቶችን በኢንተርፕሪነርሺፕ አማካኝነት በሥነ ልቦና ግንባታ በማገዝ አመለካከታቸውን በመቀየር ሥራ መራጭ እንዳይሆኑ እና የተገኘውን ሥራ የሚሠሩባቸውን ከ50 በላይ የሥራ አማራጮችን እንደሚያቀርብ ቃል ገብቷል።

ዶክተር ወልደማርያም “በአሁኑ ሰዓት የሚታየው ኃላፊነት የጎደለው እና ምንጩ የማይታወቀውን ቅንጡ ግንባታ (የቤተ መንግሥት ግንባታን) ጨምሮ በየቦታው የሚሠሩ ሰው አልባ ቤቶች፣ ሰው እየሞተ፣ እየጠፉ ያሉ ሀብቶችን ሰብስበን በሰው ተኮር ልማት ላይ በማዋል የኑሮ ውድነትን በተመረጠ መንግሥታዊ ጣልቃ ገብነት የገበያ ጉድለትን እንሞላለን” ብለዋል።
ዎሕነን አሁን ያለውን የግብር እና የታክስ ሥርዓት በመከለስ ሙስናን እና ኪራይ ሰብሳቢነትን እንደሚዋጋ ገልጾ፣ በከተማ ደረጃ ከሚስተዋሉ ችግሮች መካከል አንዱ የከተማ ቤቶች እጥረት መሆኑን እንደሚረዳ እና “ለኪራይ ሰብሳቢዎች ብዝበዛ የተጋለጠውን የከተማ መሬት በፍትሐዊነት በመነሻ ሊዝ ዋጋ በቴክኖሎጂ ታግዞ ‘አንድ የቤት መሥሪያ ቦታ ለአንድ ዜጋ’ በሚል ከቤቶች ልማት ጋር በማቀናጀት” እንደሚሠራም አክሏል። የክልልነት ጥያቄን በተመለከተም ዎሕነን “ባሸንፍ የመጀመሪያው እርምጃዬ የሚሆነው የዎላይታን የክልልነት ጥያቄ መመለስ ነው” ብሏል። የዎላይታን ብቻ ሳይሆን፣ የቁጫን ሕዝብ ጨምሮ የሌሎች ሕዝቦችን ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ እንደሚመልስም ፓርቲው አመልክቷል።
ዶ/ር ወልደማርያም፣ ክልልነት ለዎላይታ ሕዝብ የሚያመጣውን ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ፋይዳ ሲያስረዱ፣ በዎላይታ ዞን 272 ሺህ ዜጎች ሥራ አጥ ሆነው እንደተቀመጡ በመግለጽ “ከዞኑ ውጭ የሚኖረውን እስከ 70 በመቶ የሚሆነውን ሕዝብ እንመልሳለን” ብለዋል። የክልልነት ጥያቄ የሚነሳው ከመልካም አስተዳደር ጋር ተያይዞ እኩል የመልማት ዕድልና ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል ባለመኖሩ ምክንያት እንደሆነ ያነሱት ዶክተር ወልደማርያም “ዜጎች ራሳቸውን በራሳቸው ለማስተዳደር የሚሄዱበት መንገድ መገንጠል ተብሎ ሊጠራ አይገባም” ብለዋል። [ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር]




