በባልደራስ ይፋዊ ማኅበራዊ ሚዲያ ገጽ የወጣውን መግለጫ፣ ፕሬዚዳንቱ አላውቀውም አሉ

የባልደራስ ፓርቲ “የሥራ አስፈፃሚ እና የምክር ቤት አባላት” ባወጡት መግለጫ፣ በፓርቲው ፕሬዚዳንት እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች የፓርቲውን መዋቅርና መተዳደሪያ ደንብ የጣሱ ናቸው ሲሉ ወቀሱ፤ የፓርቲው ፕሬዚዳንት በበኩላቸው መግለጫው የወጣበት የማኅበራዊ ሚዲያ ገጽ ከፓርቲው ቁጥጥር ውጪ ሆኗል በማለት፣ መግለጫዎቹ “እኛን አይወክሉንም” ብለዋል።

ዛሬ፣ ሚያዝያ 12፣ 2018 በባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ (ባልደራስ) ይፋዊ የማኅበራዊ ሚዲያ ገፅ፣ የፓርቲው “የሥራ አስፈፃሚ እና የምክር ቤት አባላት” እንደጻፉት የሚገልፀው መግለጫ፣ ፕሬዝዳንቱ ሁለት ግለሰቦችን በመያዝ ተቋማዊ አሠራርን ወደ ጎን በመተው ፓርቲውን በሕገ-ወጥ መንገድ እየመሩት ነው ብለዋል።

​መግለጫው አክሎም፣ ባለፉት ጥቂት ወራት በፓርቲው ስም የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት የሥራ አስፈፃሚውንና የምክር ቤቱን ዕውቅና ያላገኙ መሆናቸውን ዘርዝሯል። ከነዚህም መካከል ያለ ውይይት በምርጫ ለመሳተፍ መወሰን፣ ዕጩዎችን ማስመዝገብ፣ ማኒፌስቶ ማውጣትና የፓርቲውን ዋና ጽሕፈት ቤት አድራሻ መቀየር የሚሉት ይገኙበታል።

​መግለጫው አክሎም፣ ግለሰባዊ ውሳኔዎች በአስቸኳይ እንዲቆሙና ፓርቲው ወደ መዋቅራዊ አሠራር እንዲመለስ አሳስበዋል። ጉዳዩ በውስጥ ውይይት የማይፈታ ከሆነም ማስረጃዎችን ይፋ እንደሚያደርጉ አስጠንቅቀዋል። “የፓርቲው ፕሬዝዳንት ሁለት ግለሰቦችን በመያዝ ፓርቲውን ሕገ-ወጥ በሆነ መንገድ ለመምራት፤ የፓርቲውን የሥራ አስፈፃሚ፣ ምክር ቤት እና ሌሎች መዋቅሮችን ከጨዋታ ውጪ በማድረግ ውሳኔዎችን ከሕግ ውጪ በራሳቸው እየወሰኑ ይገኛሉ። እነዚህ የሥራ አስፈፃሚን እና ምክር ቤትን ያገለሉ ውሳኔዎች እና ተግባራት ተቀባይነት የላቸውም” ይላል።

በዚህ ጉዳይ ላይ ምላሻቸውን እንዲሰጡ “ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የጠየቀቻቸው የፓርቲው ፕሬዚዳንት አቶ አመሃ ዳኘው “በየትኛውም ማኅበራዊ ሚዲያ የሚወጡ መግለጫዎች እኛን አይወክሉንም። ፓርቲው ሲጠቀምባቸው የነበሩ ሦስት የፌስቡክ ገፆች እና አንድ ዌብሳይት ከእኛ ቁጥጥር ወጥተዋል።” ብለዋል። እርሳቸው የሚመሩት ባልደራስ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ለመውሰድ በዝግጅት ላይ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

ባልደራስ ከዚህ ቀደም ያካሔደው የብሔራዊ ምክር ቤት ስብሰባ ምልዓተ ጉባዔ አላሟላም በሚል፣ የተወሰኑ አባላት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያቀረቡትን አቤቱታ ተከትሎ ፓርቲው የመከፋፈል አደጋ እንደተጋረጠበት “ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” መዘገቧ ይታወሳል። ምርጫ ቦርድም አቤቱታውን ተቀብሎ ስብሳባው በድጋሚ እንዲካሔድ መወሰኑን ፓርቲው ስላልተቀበለው፣ ክርክሩ እስከ ፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት መድረሱን እና ፍርድ ቤቱም የቦርዱን ውሳኔ ማፅናቱ ታውቋል። [ ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር]