የተጣራ የዕጩዎች ዝርዝር ሚያዚያ 23፣  2018 ይፋ እንደሚያደርግ ምርጫ ቦርድ አሳወቀ

የካቲት 16፣ 2018 የተጠናቀቀውን የዕጩዎች ምዝገባ ተከትሎ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጥቅል የዕጩዎችን መረጃ ይፋ ያደረገ ቢሆንም፣ ሙሉ የዕጩዎች ዝርዝር በቦርዱ ድረገጽ ይፋ አለመደረጉን በማስመልከት “ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ለቦርዱ ተደጋጋሚ ጥያቄ ስታቀርብ ነበር። ቦርዱ ትላንት፣ ሚያዝያ 15፣ የመራጮች ምዝገባ መጠናቀቅን ለማወጅ በተዘጋጀው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ፣ “ትክክለኛ እና ጥርት ያለውን የዕጩዎች ዝርዝር” በዚህ ወር፣ ሚያዝያ 23 ይፋ እንደሚያደርግ አሳውቋል።

የዕጩዎች ምዝገባ ሕዳር 30  ይፋ በተደረገው የምርጫ የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ከጥር 1 እስከ የካቲት 1 ድረስ እንዲከናወን ታቅዶ የነበረ ቢሆንም፣ በተለያዩ ምክንያቶች የዕጩዎች ምዝገባ ማጠናቀቂያ ቀኑ እስከ የካቲት 16 እንዲራዘም መደረጉ ይታወሳል።

የዕጩዎች ምዝገባ መጠናቀቅን ተከትሎ የካቲት 27፣ 2018 ቦርዱ ባዘጋጀው የጋዜጣዊ መግለጫ ላይ፣ የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ የዕጩዎች ዝርዝር በምርጫ ክልሎች ጽ/ቤት የዛኑ ዕለት ምሽት ጀምሮ እንደሚለጠፍ አሳውቀው ነበር። የትላንቱ መግለጫ ላይም ሰብሳቢዋ “የዕጩዎች  ምዝገባው ከተከናወነ በኋላ ዕጩዎች በሚወዳደሩባቸው ምርጫ ጣብያዎች ዝርዝር መውጣቱን” ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 አንቀጽ 36 መሠረት፣ ቦርዱ “የዕጩዎች ምዝገባ ከተጠናቀቀበት ጊዜ ጀምሮ የምርጫ ክልሉ ጽሕፈት ቤት የተወዳዳሪ ዕጩዎችን ስም ዝርዝር ለሕዝብ ይፋ” እንዲያደርግ ይደነግጋል። በመሆኑም፣ የምርጫ ክልል ጽሕፈት ቤቶች የዕጩዎች ምዝገባ እንደተጠናቀቀ የተወዳዳሪዎችን ስም ዝርዝር ለሕዝብ ይፋ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

ነገር ግን “ጥርት ያለውን፣ ያለቀውን እና የተጠናቀቀውን” ወደ ድምፅ መስጫ ወረቀት የሚሔደውን ዕጩዎች ዝርዝር የሚወጣው በሕጉ መሠረት “ፓርቲዎች የሚለቁ ወይንም በሞት የተለዩ ዕጩዎች ካሏቸው፣ እነሱን የማተካካት ሥራ አጠናቀው ከጨረሱ በኋላ” መሆኑን የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ ተናግረዋል። የምርጫ ሕጉ አንቀፅ 39ም ከዕጩነት ውድድር  የሚወጡ ወይም የሚተኩ ዕጩዎች ከድምፅ መስጫቸው ከአንድ ወር በፊት ማሳወቅ እንዳለባቸው ይደነግጋል።

በሕዳር ወር መጨረሻ ይፋ በሆነው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት “የድምፅ መስጫ ወረቀቶች እና ቅፆች ኅትመት” ከመጋቢት 12 እስከ ሚያዝያ 27 እንደሚከናወን ተገልጿል።  በዚሁ የጊዜ ሰሌዳ የድምፅ መስጫው ቀን ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም በመሆኑ፣ አሁን የዕጩዎችን ዝርዝር የማጥራት ሥራው እየተሠራ መሆኑን የቦርዱ ሰብሳቢ ገልጸው፣ ይኸውም እስከ ሚያዚያ 23 እንደሚጠናቀቅ ገልጸዋል።

“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከዲጂታል የዕጩዎች ምዝገባ ስርዓት ጋር በተያያዘ እና በተለይም መመዝገቢያ ሲስተሙ የብሔራዊ መታወቂያ የሚጠይቅ በመሆኑ ሳቢያ ሊያስመዘግቡ ካቀዷቸው ዕጩዎች ያነሰ ቁጥር ያላቸው ብቻ ማስመዝገብ እንደቻሉ እና ይህንንም ለምርጫ ቦርድ አቅርበው እየታየላቸው መሆኑን ገልጸዋል።

ለአብነትም፣ ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት 1,700 ለማስመዝገብ አቅዶ፣ 1,223፤ ነፃነት እና እኩልነት ፓርቲ 1,500 ለማስመዝገብ አቅዶ 884፤ እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ፓርቲ 1,100 ለማስመዝገብ አቅዶ 167 ብቻ እንደተመዘገቡላቸው፣ በዚህም ቅሬታቸውን ለቦርዱ አቅርበው እየታየላቸው መሆኑን መዘገባችን ይታወሳል።

ምርጫ ቦርድ የካቲት 27 ይፋ ባደረገው መረጃ፣ በድምሩ 10ሺ 934 ዕጩዎችን መመዝገቡን  መግለጹ የገለጸ ሲሆን፣ ሚያዚያ 23 ይፋ የሚያርገው ቁጥር ለውጥ ሊኖረው እንደሚችልም ይጠበቃል።  ሁለት ጥምረቶችን እና አንድ ግንባርን ጨምሮ 47 ያህል የፖለቲካ ፓርቲዎች ዕጩዎቻቸውን ማስመዝገባቸውን እንዲሁም 73 የግል ዕጩዎች መመዝገባቸውን በመግለጫው ተገልጾ ነበር።

ከነዚህ ውስጥ 2,198 ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲመዘገቡ፣ ለክልል ምክር ቤቶች 8,736 ዕጩዎች መመዝገባቸው ተጠቅሷል። 2,760 (25%) ዕጩዎቹ ሴቶች ሲሆኑ፣ 8,174  (75%) ደግሞ ወንዶች ናቸው ተብሏል። [ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር]