ዶ/ር ራሔል ባፌ ኢሶዴፓ ያስመዘገባቸው 309 ዕጩዎች መሰረዛቸውን በመቃወም ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት እና ፓርላማ አቤቱታ ማስገባታቸውን ገለጹ

​የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለኢትዮጵያ ሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) በጻፈው ደብዳቤ፣ ፓርቲው ለ7ኛው ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ ያቀረባቸው ዕጩዎች ከውድድር ውጪ መደረጋቸውን አስታውቋል። ቦርዱ ይህን ውሳኔ ያስተላለፈው በፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር ዶ/ር ራሔል ባፌ አማካይነት የተመዘገቡት ዕጩዎች በእነ አቶ አጫሞ ቦቄ በቀረበበት ተቃውሞ ሳቢያ ነው። ቦርዱ በዶ/ር ራሔል አማካይነት በዲጂታል ሲስተም ተመዝግበው ይፋ የተደረጉትን ዕጩዎች በእነ አጫሞ ቦቄ ተቃውሞ ቀርቦበት ወደ ፍርድ ቤት ክርክር እንዲያመራ ማድረጉን ገልጿል። ፍርድ ቤቱም ‘ዕጩዎች የቀረቡበት አግባብ የፓርቲውን መተዳደሪያ ደንብ ተከትሎ አይደለም’ የሚል ውሳኔ በማሳለፉ፣ ምርጫ ቦርድ ሁለቱን ወገኖች ሊያሸማግል ያደረገው ሙከራ ስላልተሳካ አስቀድሞ ይፋ የተደረጉት ዕጩዎች መሰረዛቸውንና ወደ ኅትመት አለመግባታቸውን አሳውቋል።

ይህንን ውሳኔ ተከትሎ፣ “ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው የኢሶዴፓ ምክትል ሊቀመንበር ዶ/ር ራሔል ባፌ “በአመራሮች መካከል በተፈጠረ አለመግባባት የዕጩዎችን መብት ማገድ ተገቢ አይደለም። ሕገ መንግሥታዊ ጥበቃ የተደረገለትን የመመረጥ መብት ብሔራዊ ምርጫ  ቦርድ ተጋፍቷል” በማለት ቅሬታቸውን ገልጸዋል። “ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን ለመወሰን የሄደበት አካሄድ የፓርቲውን መተዳደሪያ ደንብ እና አዋጁን ጠቅሶ የጻፈበት 309ኙ ዕጩዎች እንዲወጡ ሳይሆን፣ ማስተካካያ እንዲያደርግበት ቢሆንም ቦርዱ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ አልተከተለም” ሲሉ አስረድተዋል። ይህንን ቅሬታቸውን ለማሰማትም፣ ምክትል ሊቀመንበሯ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት እና ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት (ፓርላማ) አቤቱታ ማቅረባቸውን ገልጸዋል።

የምርጫ ቦርድ ደብዳቤ እንደሚገልጸው፣ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመጋቢት ወር 2018 ዓ.ም በሰጠው ውሳኔ፣ በሁለቱም ወገኖች በኩል የቀረቡት ዕጩዎች የፓርቲውን መተዳደሪያ ደንብ ተከትለው የቀረቡ ባለመሆናቸው ውድቅ እንዲሆኑ ወስኗል። ቦርዱ ይህንን የፍርድ ቤት ውሳኔ ሚያዚያ 9 ቀን 2018 ዓ.ም ለፓርቲው ካሳወቀ በኋላ፣ ሁለቱም ወገኖች ልዩነታቸውን ፈትተው የጋራ ዕጩዎችን እንዲያቀርቡ በተደጋጋሚ የጊዜ ገደብ ሰጥቶ እንደነበር በደብዳቤው ላይ ገልጿል።

ዶ/ር ራሔል “ቦርዱ በፓርቲው የተለያዩ የተሠሩ ሥራዎችን ስናሳውቅ የመሻር፣ ያለመቀበል እንዲሁም ጣልቃ የመግባት ሁኔታዎችን ሲያሳይ ቆይቷል” ያሉ ሲሆን፣ እንደ እርሳቸው ገለጻ “እነአጫሞ በፓርቲው በዕጩነት ቀርበው የነበረ ቢሆንም፣ መስፈርቱን አሟልተው ፋይዳ [ብሔራዊ የዲጂታል] መታወቂያ አቅርበው ለመመዝገብ ፈቃደኛ አልነበሩም”።

ምርጫ ቦርድ ዶ/ር ራሔል ላነሱት ወቀሳ ለ“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” በሰጠው ምላሽ “አለመግባባት ውስጥ የገቡት የኢትዮጵያ ሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲ ምክትል ሊ/መንበር ዶ/ር ራሔል ባፌ እና እነ’አቶ አጫሞ ቦቄ በተለያየ ጊዜ ለሚጽፉለት ፓርቲውን የተመለከቱ ደብዳቤዎች ሕጉን ተከትሎ አስፈላጊውን ምላሽ ሲሰጥ ቆይቷል። ይኽውም ቦርዱ አስተዳደራዊ ሥራውን መሥራቱና በሕጉ አግባብ ከሁለቱም ለሚቀርቡለት አቤቱታዎች ሕጉ በሚፈቅደው አግባብ ምላሽ መስጠቱን እንደጣልቃ ገብነት ማየት የአንድን ሕገ-መንግሥታዊ ተቋም ሥልጣንና ኃላፊነቱን ተግባራዊ ማድረግ ላይ የተነሣ መሠረታዊ ስህተት ነው” ብሏል።

ቦርዱ አክሎም፣ አስቀድሞ በዶ/ር ራሔል በኩል የተመዘገቡትን ዕጩዎች በምርጫ ክልል ደረጃ ይፋ ያደረገ መሆኑን ገልጾ፣ ነገር ግን ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት የወሰዱት እነ አጫሞ ቦቄ በፍርድ ቤቱ “ዕጩዎች የቀረቡበት አግባብ የፓርቲውን መተዳደሪያ ደንብ ተከትሎ አይደለም” ተብሎ በመወሰኑ፣ “በሁለት የተለያየ ጊዜ እያንዳንዳቸውን በተናጥል፤ አንድ ጊዜ ደግሞ በጋራ በማወያያየት ተቋማዊና አስተዳደራዊ ኃላፊነቱን ከመወጣትም በላይ የማሸማገል ተግባራት ሲያከናወን” መቆየቱን በመጥቀስ ችግሩ የፓርቲው አመራሮች ጋር መሆኑን አመልክቷል።

ምክትል ሊቀመንበሯ በበኩላቸው ችግሩን “ቦርዱም ያውቀዋል” ያሉ ሲሆን፣ “ሚያዚያ 21 ቀን በቦርዱ ጽ/ቤት በመገኘት ምዝገባውን ፍርድ ቤቱ በወሰነው አግባብ ለማከናወን ሽማግሌ ይዘን እንድንቀርብ የተደረገ ቢሆንም [እነ አጫሞ ቦቄ] ሳይመጡ ቀርተዋል” በማለት የምርጫ ቦርድን ሚና ጠቅሰዋል። ይሁንና፣ “በአመራሮች መካከል በተፈጠረ አለመግባባት የዕጩዎችን መብት ማገድ ተገቢ አይደለም። ሕገ መንግሥታዊ ጥበቃ የተደረገለትን የመመረጥ መብት ብሔራዊ ምርጫ  ቦርድ ተጋፍቷል” ብለዋል።

ምርጫ ቦርድም ለዚህ ቅሬታቸው በሰጠው መልስ፣ “ከምርጫ ውጭ እንዲደረጉ የሆኑት ዕጩዎች የቀረቡት በፓርቲ ዕጩነት ሲሆን፤ ይኽውም በፓርቲ ዕጩነት የሚቀርቡ በዐዋጅ ቁጥር 1162/2011 እና በፓርቲያቸው መተዳደሪያ ደንብ መሠረት ተመልምለው ለዕጩነት መቅረብ ይኖርባቸዋል። ዕጬዎቹ ሲቀርቡ እንደ ግል ዕጩ ሣይሆን እንደ ፓርቲ ዕጩ የቀረቡ ስለሆነ ጉዳያቸውም የሚታየው በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ ላይ በተደነገገው አግባብ ሲቀርብ ብቻ ነው” ብሏል።

ምርጫ ቦርድ ለኢሶዴፓ በጻፈው ደብዳቤ “ቦርዱ ተቃውሞ የቀረበባቸውን ዕጩዎች የያዘ የድምፅ መስጫ ወረቀት ወደ ማተሚያ ቤት ገብቶ ለህትመት ዝግጁ ቢሆንም፣ በሁለቱ ወገኖች መካከል [የ]ተፈጠረው ችግር እልባት እስከሚያገኝ ሳያሳትም እንዲቆይ አድርጓል፤ ችግራቸውንም ፈተው ይቀርባሉ በማለት ቢጠብቅም መፍትሔ ሊገኝ አልቻለም” ብሏል።

ዶ/ር ራሔል በበኩላቸው፣ ዛሬ፣ ሚያዝያ 26፣ ጉዳዩን ወደ ጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት እና ለፓርላማ መውሰዳቸውን “ለምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። “ጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የሚሰጠንን ምላሽ ገና አላወቅንም። [ቦርዱ] ቀጥታ ተጠሪነታቸው ለፓርላማ ስለሆነ በተመሳሳይ ለፓርላማውም አመልክተናል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ያስገባነው የመንግሥትን ዘርፍ በተመለከተ መንግሥታቸው በሚሄድበት አግባብ ይሄ አካሄድ ትክክል ስላለሆነ ነው” ብለው ለ“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

በተመሳሳይ፣ ምክትል ሰብሳቢዋ ቀደም ሲል ለምርጫ ቦርድ በጻፉት ደብዳቤ፣ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ “የጉዳዩ ባለቤት የሆነው ኢሶዴፓ ባላወቀበትና ባልተሳተፈበት የክስ ሂደት” የተሰጠ መሆኑን ጠቅሰው ቅሬታቸውን አቅርበዋል። ዶ/ር ራሔል ቦርዱ ቀደም ብሎ ለሕዝብ ይፋ ያደረጋቸውን “[309 ዕጩዎች] ሕጋዊ መስፈርቱን ተከትለው የተመዘገቡ” ናቸው ብለው በመከራከር፣ የእነዚህ ዕጩዎች ስም በድምፅ መስጫ ወረቀት ላይ እንዲካተት ጠይቀው ነበር። የምርጫ ቦርድ ደብዳቤ እንደሚያሳየው፣ የፍርድ ቤቱ ክርክር የተካሔደው በቦርዱ እና በእነ አጫሞ ቦቄ መካከል ነበር።

በዶ/ር ራሔል የተፈረመው ደብዳቤ “በአዋጅ ቁጥር 1162/2011 አንቀጽ 42 መሠረት ዕጩዎች ላይ ሕጋዊ እርምጃ ሊወሰድባቸው የሚችለው የምርጫው ውጤት በቦርዱ አማካኝነት በይፋ ለሕዝብ ከተገለጸ በኋላ ብቻ መሆኑ እየታወቀ፣ ከምርጫው ሂደት የሚገታቸው ነገር የለም” በሚል ውሳኔውን ተቃውሞታል።

ይሁን እንጂ ምርጫ ቦርድ የድምፅ መስጫ ወረቀት ህትመትን ከዚህ በላይ ማዘግየት “የሌሎቹ ፓርቲዎችን የመወዳደር እና የመመረጥ መብት እንዲሁም የመራጮችን የመምረጥ መብትን ችግር ላይ የሚጥል” ሆኖ አግኝቼዋለሁ ብሏል። ቦርዱ የፍርድ ቤት ውሳኔን የማክበር ግዴታ ያለበት መሆኑን በመጥቀስ፣ በተሰጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ አዲስ ዕጩዎች ባለመቅረባቸው ፓርቲው ቀደም ብሎ አቅርቧቸው የነበሩት ዕጩዎች በምርጫው እንዳይሳተፉ መወሰኑን በቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ንዋይ የተፈረመው ደብዳቤ ያሳያል።

በዚህም ምክንያት ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም በሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ፣ ኢሶዴፓ አስቀድሞ ለሕዝብ ይፋ ያደረጋቸው 309 ዕጩዎች በውድድሩ ላይ እንደማይሳተፉ ለመረዳት ተችሏል። 

ኢሶዴፓ በነሐሴ 8፣ 2015 ባወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ እንደጠቀሰው፣ የኢሶዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ ዶ/ር ራሔል ባፌን በሞት የተለዩትን የቀድሞው የፓርቲው ሊቀ መንበር ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስን በመተካት ሊቀ መንበር አድርጎ መምረጡን አሳውቆ ነበር። በዚሁ ስብሰባው፣ ማዕከላዊ ኮሚቴውን “የመከፋፈል ሴራ አንግበው” ተንቀሳቅሰዋል፣ “አሳሳች አጀንዳ ነድፈው የተሳሳተ መረጃ በመዝራትና በማሰራጨት” ተግባር ላይ ተሳትፈዋል ያላቸውን አቶ አጫሞ ቦቄን ጨምሮ አራት የሥራ አስፈፃሚ አባላትን ከማንኛውም የሥራ ኃላፊነታቸው በማንሳት፣ በአባልነት ብቻ እንዲቀጥሉ ወስኗል። 7ኛውን አገራዊ ጠቅላላ ምርጫ ከግንዛቤ በማስገባትም ቀድሞ የነበረውን 10 የሥራ አስፈፃሚዎች ቡድን፣ 11 የሥራ አስፈፃሚ አባላትን በመምረጥ ማሳደጉን አሳውቆ ነበር።

ይሁን እንጂ ምርጫ ቦርድ ይህንን ዶ/ር ራሔል ሊቀ መንበር ሆነው የተመረጡበት የሥራ አስፈፃሚ ስብሰባ ሊቀ መንበር ለመምረጥ የማያስችል በመሆኑ እና በፓርቲው ሕገ ደንብ መሠረት ይህንን የማድረግ ሥልጣን ያለው የማዕከላዊ ኮሚቴ መሆኑን በመግለጽ ውሳኔውን ሳይቀበለው ቀርቷል። በዚህም ምክንያት ዶ/ር ራሔል ምክትል ሊቀ መንበር ሆነው ፓርቲውን የመምራት ኃላፊነት ይዘው ቀጥለዋል።

በሌላ በኩል ሰኔ 8፣ 2017 ዶ/ር ራሔል ተመረጡበት የተባለው የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ያገዳቸው አጫሞ ቦቄን ጨምሮ ስድስት የሥራ አስፈፃሚዎች ዶ/ር ራሔልን እና የፓርቲውን ማኅተም ማገዳቸውን ያሳወቁ ሲሆን፣ ጊዜያዊ ሊቀ መንበር መምረጡንም አሳውቀዋል። በዚህ መግለጫ ላይ የፓርቲው ምክትል ሊቀ መንበር ሆነው እንደተሰየሙ የተገለጹት አቶ አጫሞ ቦቄ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ የበይነመረብ ሚዲያ በወቅቱ እንደተናገሩት፣ “ዶ/ር ራሔል ከተሰጣቸው ኃላፊነት ውጭ እየተንቀሳቀሱ በመሆናቸው እና ማኅተሙን ላልተገባ ተግባር እየተጠቀሙበት ስለሆነ” ሥራ አስፈፃሚው “የእግድ ውሳኔውን አሳልፏል፤ አዲስ ማኅተምም አስቀርጿል” ማለታቸው ይታወሳል።

ዶ/ር ራሔል፣ “ፓርቲው ከዚህ ቀደም መከፋፈል ውስጥ ገብቶ ነበር፤ አሁን ከሳሽ ሆነው የቀረቡት እነ አጫሞ ቦቄ በፎርጂድ ማኅተም አግጃለው” በሚል የወሰዱት እርምጃ ትክክል አለመሆኑን የገለጹ ሲሆን፣ በዚህ ጉዳይ አሁንም ድረስ በክስ ላይ መሆናቸውን አስረድተዋል።

በጉዳዩ ላይ የአቶ አጫሞ ቦቄን አስተያየት ለማካተት በተደጋጋሚ በእጅ ስልካቸው ጥሪ ብናደርግም፣ መልስ ሳይሰጡ በመቅረታቸው አልተሳካም። [ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር]