116 የምርጫ ጣቢያዎች ክልከላ በተደረገባቸው ወታደራዊ፣ ፖሊስ፣ ሃይማኖት ተቋማት እና መጠጥ ቤቶች ተቋቁመው መገኘታቸውን ኅብረት ለምርጫ አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ኅብረት ለምርጫ ትናንት ይፋ ባደረገው ሪፖርቱ በመራጮች ምዝገባ ላይ የታዩ አዎንታዊ እና አሉታዊ ኹነቶችን ገልጿል።

በዚህም ኅብረቱ ታዛቢዎችን ካሠማራባቸው 4,396 የምርጫ ጣቢያዎች ውስጥ በ102 የማኑዋል ምዝገባ ጣቢያዎች እና 14 የዲጂታል ምዝገባ ጣቢያዎች፣ በሕግ ክልከላ በተደረገባቸው ቦታዎች (ወታደራዊ፣ ፖሊስ፣ ሃይማኖታዊ፣ ጤና ጣቢያ፣ መጠጥ ቤት ወይም ሆቴል፣ የፖለቲካ ፓርቲ ጽሕፈት ቤት እና የግል መኖሪያ ቤት) ተቋቁመው መገኘታቸውን የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ኅብረት ለምርጫ ገልጿል። በተጨማሪም በተለይ በአማራ ክልል አንድ የምርጫ አስፈፃሚ መገደሉን የጠቀሰው ኅብረቱ፣ በሌሎችም የምርጫ አስፈፃሚዎች ላይ የግድያ ሙከራ እና አፈና መፈጸሙን ሪፖርቱ አሳውቋል።

ኅብረቱ ያከናወነውን የትዝብት ግኝቶች የያዘ ሪፖርት ትላንት ሚያዝያ 26 ቀን 2018 ዓ.ም. ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ 522 የረጅም ጊዜ ታዛቢዎችን በማሰማራት 3,953 ቋሚ እና 443 ተንቀሳቃሽ በድምሩ 4,396 የምዝገባ ጣቢያዎችን መታዘቡን ገልጿል። ሪፖርቱ የሚሸፍነው ጊዜ ከመጋቢት 12 ቀን 2018 ዓ.ም. ጀምሮ የመራጮች ምዝገባ እስከ ተጠናቀቀበት ሚያዝያ 14 ቀን 2018 ዓ.ም. ድረስ ያለውን የመራጮች ምዝገባ ሂደት የሚሸፍን መሆኑም ተገልጿል።

የምርጫ አስፈፃሚዎች መሟላትን በተመለከተ፣ ሕጉ በምዝገባ ጣቢያዎች ቢያንስ ሦስት (3) የምርጫ አስፈፃሚዎች መገኘት እንዳለባቸው ይደነግጋል። የኅብረቱ ታዛቢዎች በታዘቧቸው በሁለቱም የምዝገባ አማራጮች በአማካይ አራት አስፈፃሚዎች መኖራቸው ተረጋግጧል። የምዝገባ ሂደት መቋረጥን በተመለከተ፣ ኅብረቱ ከታዘባቸው የምዝገባ ጣቢያዎች ውስጥ 2,666 የማኑዋል እና 320 የዲጂታል ምዝገባ ጣቢያዎች የምዝገባው ሂደት በማናቸውም ጊዜ አለመቋረጡን ሪፖርቱ ያመለክታል። በተቃራኒው በ1,287 የማኑዋል እና በ123 የዲጂታል ምዝገባ ጣቢያዎች ምዝገባ ቢያንስ አንድ ጊዜ ተቋርጧል።

የጸጥታ አስከባሪዎችን በተመለከተ፣ ኅብረቱ በታዘባቸው 2,999 የማኑዋል እና በ320 የዲጂታል ምዝገባ ጣቢያዎች ውስጥ የጸጥታ አካላት ከምዝገባ ጣቢያው ውጭ (በሕጉ መሠረት) መገኘታቸውን መታዘቡን ገልጿል።

በምዝገባ ጣቢያዎች ውስጥ እና አካባቢ በተመዝጋቢዎች፣ በአስፈፃሚዎች እና በታዛቢዎች ላይ የደረሰ ጥቃት፣ ማስፈራራት እና ወከባ መኖሩን ኅብረቱ አረጋግጧል። በዚህም አንድ የምርጫ አስፈፃሚ በአማራ ክልል ምስራቅ ጎጃም ዞን መገደሉን ገልጿል።

በተጨማሪም በአማራ ክልል አዊ እና ዋግ ሕምራ ዞኖች ሁለት የግድያ ሙከራዎች፣ በምስራቅ ጎጃም ዞን ሰባት የአፈና ድርጊቶች፣ በዋግ ሕምራ ዞን ሁለት አፈናዎች፣ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ሁለት አፈናዎች እንዲሁም በሲዳማ ክልል ሁለት የድብደባ ድርጊቶች መፈጸማቸውን ሪፖርቱ አመልክቷል።

ኅብረቱ በአንዳንድ ጣቢያዎች በአካል ያልቀረቡ ሰዎችን መመዝገብ፣ መታወቂያ ሳይኖር መመዝገብ እና ሕግ በሚከለክላቸው ቦታዎች (እንደ ወታደራዊ ካምፕ ያሉ) ምዝገባ ማካሄድን እንደ ተግዳሮት ተመልክቷል። የምዝገባ ጣቢያዎች ለአካል ጉዳተኞች እና ለአረጋውያን ምቹ እንዳልነበሩም ገልጿል። በመሆኑም በምርጫ ጣቢያዎች፣ በአስፈፃሚዎች እና በመራጮች ላይ ጥቃት እንዳይደርስ ተገቢውን ጥበቃ ማድረግ እንደሚገባ አሳስቧል። የፖለቲካ ፓርቲዎችም የምዝገባ ሂደቱ ግልጽነት እና ተጠያቂነት እንዲኖረው ወኪሎቻቸውን በማሰማራት የድርሻቸውን እንዲወጡ ተጨማሪ ማሳሰቢያ ሰጥቷል። [ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር]