ከ54 ሚሊዮን በላይ መራጮች ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ መመዝገባቸውን ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ፤ በአማራ እና በጋምቤላ 9 የምርጫ ክልሎች የቁሳቁስ መዘግየት አጋጥሟል

ለመጪው ሰኞ ሰኔ 1 ቀን 2018 ዓ.ም. ለተቀጠረው 7ኛው ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ በአጠቃላይ 54 ሚሊዮን 57 ሺህ 861 መራጮች በይፋ መመዝገባቸውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምሽቱን በሰጠው መግለጫ አስታወቀ። ከዚህ ቀደም የተመዘገቡ መራጮች ቁጥር 50.5 ሚሊዮን መሆኑ የተጠቀሰ ሲሆን፣ ይህም የመጭረሻው ቁጥር እንዳልሆነ ተገልጾ ነበር። ምርጫው ሊካሄድ ሦስት ቀናት ብቻ በቀሩበት በአሁኑ ወቅት፣ የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ የምርጫ ሎጂስቲክስ ስርጭትን እና አጠቃላይ የቦርዱን የመጨረሻ ዝግጅት በተመለከተ ለመገናኛ ብዙኃን ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ዋና ሰብሳቢዋ በአማራ ክልል በነበረው የጸጥታ ሁኔታ ምክንያት በ48 የምርጫ ክልሎች የመራጮች ምዝገባ ዘግይቶ እንደነበር አስታውሰዋል። ይሁን እንጂ ክልሉ ካቀረበው ተጨባጭ የጸጥታ ሪፖርት እና ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ከተደረገ ውይይት በኋላ በ40ዎቹ የምርጫ ክልሎች ምዝገባው በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁን ገልጸዋል። ቦርዱ ቀደም ሲል ግንቦት 18 ቀን 2018 ዓ.ም. በሰጠው መግለጫ፣ ከአማራ ክልል 8 የምርጫ ክልሎች ላይ ግን ዘንድሮ ምርጫ እንደማይካሄድ በይፋ ማስታወቁ ይታወሳል።

ቦርዱ በልዩ ሁኔታ ምዝገባ ባካሄደባቸው ወገኖች በኩል የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች 20 ሺህ 122 መራጮች፣ በተፈናቃይ ካምፖች የሚገኙ ዜጎች 28 ሺህ 632 መራጮች፣ የመከላከያ ሠራዊት አባላት 100 ሺህ 498 መራጮች በይፋ መመዝገባቸው በመግለጫው ጠቅሷል።

በዚህም መሠረት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ካሉት 547 አጠቃላይ መቀመጫዎች መካከል፣ ዘንድሮ ምርጫ የሚካሄደው በ501 ወንበሮች ላይ ብቻ መሆኑ ተረጋግጧል።

የዓለም አቀፍ እና የአገር ውስጥ ታዛቢዎችን ዝግጅት በተመለከተም፣ የዓለም አቀፍ ታዛቢ ቡድኖቹ እና ፈቃድ የወሰዱ 55 የአገር ውስጥ ሲቪክ ማኅበራት ሥራ መጀመራቸውን ሰብሳቢዋ አብራርተዋል። በዚህም መሠረት ዎች 55ቱ የአገር ውስጥ ታዛቢ የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች በአጠቃላይ 1 ሺህ 562 ታዛቢዎችን እንደሚያሰማሩ ተነግሯል።

በቀድሞው የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ የሚመራ 59 አባላት ያሉት የታዛቢዎች ቡድን ወደ ሥራ እንደገባ የገለጹት ሰብሳቢዋ፣ ኢጋድ (IGAD) 26 አባላት ያሉት የምርጫ ታዛቢ ቡድን ማሰማራቱም አክለው ገልጸዋል። በአዲስ አበባ ለሚገኙ ዲፕሎማቶችም ሂደቱን ተዘዋውረው እንዲመለከቱ የእንግድነት ማለፊያ (Guest Pass) እንደተሰጣቸውም ታውቋል።

ቦርዱ ከታዛቢዎች በተጨማሪ ለመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎችም ምርጫውን እንዲዘግቡ የዕውቅና ባጅ መስጠቱን አስታውቋል።

​በዚህ መሠረት በአጠቃላይ 68 የሚሆኑ መገናኛ ብዙኃን ፈቃድ መውሰዳቸው የተገለጸ ሲሆን፣ ቦርዱ ለ56 የአገር ውስጥ እንዲሁም ለ12 የውጭ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ምርጫውን እንዲዘግቡ ባጅ መስጠቱን አሳውቋል።

​የፖለቲካ ፓርቲዎችም የምርጫውን ሂደት የሚከታተሉበት ከ250 ሺህ በላይ የወኪል መግቢያ ባጆችን ማከፋፈሉን የገለጸው ቦርዱ፤ ፍላጎቱ አሁንም በመኖሩ ተጨማሪ ባጆችን የማከፋፈል ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝ በመግለጫው ላይ ተነስቷል።

​ቦርዱ ከ359 ሺህ በላይ ከሚሆኑ ምርጫ አስፈጻሚዎች ጋር በመሆን እየሠራ መሆኑን የገለጹት ዋና ሰብሳቢዋ፣ ድምፅ አሰጣጡ በአጠቃላይ በ52 ሺህ ምርጫ ጣቢያዎች እንደሚከናወንም አብራርተዋል።

ይህ በእንዲህ እያለ፣ የምርጫ ቁሳቁስ ስርጭቱ ቀድሞ በተያዘው መርሃ ግብር መሠረት በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ መሆኑን የገለጹት ሰብሳቢዋ፣ እስካሁን በአማራ ለ130፣ በኦሮሚያ ለ179፣ በደቡብ ኢትዮጵያ ለ56፣ በድሬዳዋ ለ48፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ለ35፣ በአዲስ አበባ ለ33፣ በአፋር ለ32፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ለ22፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ለ22፣ ለጋምቤላ 14 እንዲሁም ለሐረሪ ክልል ለ3 የምርጫ ማዕከላት ቁሳቁሶች በሙሉ መሰራጨታቸውን አስታውቀዋል።

​ይሁን እንጂ በአማራ ክልል ካለው ወቅታዊ ሁኔታ ጋር በተያያዘ በ5 የምርጫ ክልሎች፣ እንዲሁም በጋምቤላ ክልል በ4 የምርጫ ክልሎች (በአጠቃላይ በ9 የምርጫ ክልሎች) ላይ የድምፅ መስጫ ቁሳቁስ እስካሁን ማድረስ አለመቻሉንና የመዘግየት ችግር ማጋጠሙን ቦርዱ ገልጿል።

ከተጠቀሱት 9 የምርጫ ክልሎች ውጪ በሁሉም ቦታዎች ቁሳቁሶቹ የደረሱ ሲሆን፣ ከዋና ዋና ማዕከላት ወደየምርጫ ጣቢያዎቹ የማሰራጨት ሥራ ከዛሬ ጀምሮ እየተከናወነ ይገኛል። ይህ ስርጭት እስከ መጪው እሁድ (የምርጫው ዋዜማ) ድረስ ሙሉ በሙሉ እንደሚጠናቀቅ ተገልጿል።

​ዋና ሰብሳቢዋ በመጓጓዣ ሂደት ላይ ያጋጠሙትን ችግሮች ሲያብራሩ፦ “ቁሳቁሶቹ ሲጓጓዙ ዝናብ በመጣሉ ምክንያት የምርጫ ቁሳቁስ ችግር የገጠመበት ሁኔታ አለ፤ በአንዳንድ የምርጫ ክልሎች ደግሞ ከርቀት ጋር ተያይዞ የሚጓጓዙበት መኪኖች ጎማ መበላሸት እና መኪናዎች በተጠበቀው ፍጥነት አለመሄድ አጋጥሟል” ብለዋል። (ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

[ይህ ዘገባ ከቆይታ በኋላ መረጃ ታክሎበታል]