ትላንት በታወጁ የምርጫ ውጤቶች፣ ብልፅግና የተሸነፈባቸው የመጀመሪያዎቹ ውጤቶች ይፋ ሆኑ፤ ሁሉንም ኢዜማ ወስዷቸዋል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከፊል ይፋዊ ውጤቶችን ማሳወቁን የቀጠለ ሲሆን፣ ትላንት ሰኔ 10 ቀን 2018 ዓ.ም. በርካታ ቁጥር ያላቸውን ውጤቶች ይፋ አድርጓል። በዚህም ለመጀመሪያ ጊዜ ገዢው ብልፅግና ፓርቲ ተወዳዳሪ ዕጩ ባቀረበባቸው አንዳንድ የፓርላማ እና የክልሎች ምክር ቤቶች ወንበሮች በኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ዕጩዎች መሸነፋቸው ታውቋል።

በደቡብ ኢትዮጵያ በሚገኘው አማሮ ኬሌ የምርጫ ክልል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት (ፓርላማ) ብልፅግና ፓርቲ፣ ኢዜማ እና ትብብር ተወዳድረው የኢዜማ ዕጩ ማሸነፍ መቻሉን ቦርዱ በመግለጫው ገልጿል።

በዕለቱ ይፋ ከሆኑት 40 የፓርላማ መቀመጫዎች ውጤቶች መካከል 23ቱን የብልፅግና ፓርቲ ዕጩዎች ሲያሸንፉ፣ 14ቱን ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ 3ቱን ደግሞ የግል ተወዳዳሪ ዕጩዎች ወስደውታል።

ሆኖም ከአንዱ የምርጫ ክልል በስተቀር፣ በሁሉም ተቃዋሚዎች እና የግል ተወዳዳሪዎች ባሸነፉባቸው የምርጫ ክልሎች ውስጥ ብልፅግና ዕጩ አላቀረበም ነበር።

ብልፅግና ዕጩ አቅርቦ እንደተሸነፈበት የተገለፀው ብቸኛው የአማሮ ኬሌ የፓርላማ ምርጫ ክልል በጥቅሉ 87,521 መራጮች የተመዘገቡበት ሲሆን፣ አሸናፊው የኢዜማ ዕጩ 35,545 (41% ገደማ) ድምጽ ማግኘት ችለዋል።

በ6ኛው ጠቅላላ አገራዊ ምርጫም በአማሮ ኬሌ ምርጫ ክልል ኢዜማ ማሸነፉ ይታወሳል።

በተመሳሳይ ሁኔታ ትላንት ውጤታቸው ከተገለጸው 35 የክልል ምክር ቤት የምርጫ ክልሎች አጠቃላይ የወንበር ብዛት 174 ሲሆን፣ ከነዚህ ውስጥ 41ዱን የተቃዋሚ ፓርቲ ዕጩዎች ማሸነፋቸው ታውቋል።

ከእነዚህ 41 መቀመጫዎች መካከል 35ቱ ብልጽግና ፓርቲ ተወዳዳሪ ዕጩ ያላቀረበባቸው ወንበሮች ሲሆኑ፣ ቀሪዎቹን 6 ወንበሮች ግን ኢዜማ ከብልጽግና እና ከሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ተወዳድሮ ያሸነፈባቸው ናቸው።

ኢዜማ እነዚህን 6 የክልል ምክር ቤት ወንበሮች ሊያገኝ የቻለው በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በሚገኙ ሁለት አካባቢዎች ሲሆን፣ እነሱም በባስኬቶ ልዩ ምርጫ ክልል ያሉትን 2 ወንበሮች (ሁሉንም) እና በጊዶሌ መደበኛ ምርጫ ክልል የተገኙ 4 ወንበሮችን ነው።

በጊዶሌ መደበኛ ምርጫ ክልል ያለው አጠቃላይ የወንበር ብዛት 5 ሲሆን፣ የቀረውን 1 ወንበር ብልጽግና ማሸነፍ ችሏል።

በዚህ የምርጫ ክልል ኢዜማም ሆነ ብልጽግና እያንዳንዳቸው አምስት አምስት ዕጩዎችን አቅርበው የነበረ ሲሆን፣ በ6ኛው ጠቅላላ ምርጫ ወቅት ግን በባስኬቶ ልዩ እና በጊዶሌ መደበኛ ምርጫ ክልሎች ሁሉንም ወንበሮች አጠቃሎ አሸንፎ የነበረው ብልጽግና ፓርቲ ነበር።

ምርጫ ቦርድ እስካሁን ይፋ ያደረጋቸው ጥቅል ውጤቶች 75 የፓርላማ ወንበሮች እና 325 የክልሎች ምክር ቤቶች ወንበሮች ሲሆኑ፣ ከእነዚህ ውስጥ ለፓርላማ 20ዎቹ እንዲሁም ለክልሎች ምክር ቤቶች 46ቱ ወንበሮች ተቃዋሚ ፓርቲዎች ወይም የግል ዕጩዎች የተመረጡባቸው መሆናቸው ታውቋል። (ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)