የነእፓ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ በተወዳደሩበት የሃላባ 1 የምርጫ ክልል “የምርጫውን ተአማኒነት ሙሉ ለሙሉ የሚያጠራጥሩ የሕግና የዲሲፕሊን ጥሰቶች” ተፈፅመውብኛል አሉ

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከፍተኛ አመራሮች በሃላባ ቁጥር 1 ምርጫ ክልል ለክልል ምክር ቤት በተካሄደው ውድድር ላይ ሕገወጥ የውጤት ማጭበርበር እና መዋቅራዊ ጥሰት ፈጽመዋል ሲሉ የነፃነት እና እኩልነት ፓርቲ (ነእፓ) የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ እና የዚሁ ምርጫ ክልል ዕጩ የነበሩት ወይዘሮ ነቢሃ መሐመድ ከሰሱ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በበኩሉ አቤቱታ በቀረበበት የሀላባ 1 ምርጫ ክልል ውጤት ላይ ዳግም የድምፅ ቆጠራ እንዲካሄድ መወሰኑን ሰኔ 10 ቀን 2018 ዓ.ም. በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል።

ይሁንና ነእፓ ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰኔ 3 ቀን 2018 ዓ.ም. የተጻፈውን፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሃላባ ቁጥር 1 ምርጫ ክልል (የሃላባ እና የስልጤ አካባቢዎች የጋራ ምርጫ ክልል) ለክልል ምክር ቤት ተወዳዳሪ ሆነው የቀረቡት ወይዘሮ ነቢሃ መሐመድ አቤቱታ “ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” በርካታ ቅሬታዎችን መያዙን ተመልክታለች።

ወይዘሮ ነቢሃ ለ“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” በሰጡት ቃል፣ የክልሉ መስተዳድር የእሳቸውን ስም በመጠቀም በስልጤ በኩል የቀረቡትንና በስም የሚመሳሰሏቸውን ሌላኛዋን ዕጩ ወይዘሮ ነቢያት ሁሴንን ለማሳለፍ ሲሉ ምርጫው ላይ ከፍተኛ መዋቅራዊ ጫና አሳድረዋል ብለዋል።

ተመሳሳይ ይዘት ያለው የድምፅ ቅጂ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ እየተዘዋወረ “ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የድምፁን እውነተኝነት ማረጋገጥ አልቻለችም።

ወይዘሮ ነቢሃ መሐመድ ቅሬታቸውን ይበልጥ ሲያብራሩ፣ ድጋፍ እየተደረገላቸው ያሉት ወይዘሮ ነቢያት ሁሴን የነፃነት እና እኩልነት ፓርቲ አባል ተደርገው ቢቀርቡም የአባልነት መታወቂያ እንኳን የሌላቸው እና በዕጩዎች ምዝገባ ወቅት በተበተነው መመዝገቢያ ቅጽ ላይ ብቻ የተመዘገቡ ናቸው የሚል ቅሬታቸውንም ለዝግጅት ክፍላችን ገልጸዋል።

ለቦርዱ በቀረበው ይፋዊ አቤቱታ ላይ ዕጩዋ፣ “ያገኘሁት ሕጋዊ ድምፅ፣ ስሟ በተመሳሳይ ሁኔታ «ነቢያት ሁሴን» ለተባለች ሌላ ዕጩ ተወዳዳሪ ተዛውሮ እንዲደመርላት ተደርጓል። ይህ ሕዝብ ያልሰጣትን ድምፅ እንድታገኝ ለማድረግ ሆን ተብሎ የተፈጸመ ግልጽ የውጤት ማጭበርበር ድርጊት ሲሆን፣ ለዚህም የሚያስረዳ ጠንካራ የሰነድና የፎቶግራፍ ማስረጃ አያይዘን አቅርበናል” ብለዋል።

በተለይም በየምርጫ ጣቢያው እሳቸው ያገኟቸውን 1,400 ድምፆች ሙሉ በሙሉ ወደ ‘ዜሮ’ በመቀየር፣ ድምፁ ወደ ሌላኛዋ ዕጩ እንዲዛወር መደረጉን ማረጋገጣቸውን ገልጸዋል።

ከዚህም በተጨማሪ በሳንኩራ ምርጫ ጣቢያ ላይ የአካባቢው አመራሮች ሁከት በመፍጠራቸው የምርጫ አስፈጻሚ ኃፊው ጣቢያውን ጥሎ መውጣቱንና ምርጫ ጣቢያው ለሁለት ቀናት ባዶውን ማደሩን ወይዘሮ ነቢሃ ጠቅሰዋል።

በኋላም የክልሉ ልዩ ኃይል ጣልቃ በመግባት የምርጫ ሳጥኖቹን ወደ ሆሳዕና ከተማ በማምጣት ድጋሚ ቆጠራ እንዲደረግ ቢደረግም፣ በሆሳዕናው ማዕከልም የባለሥልጣናት “ረጃጅም እጆች” ገብተውበታል ሲሉ ወይዘሮ ነቢሃ ጥርጣሪያቸውን ገልጸዋል።

በጥቅሉ በሳንኩራ፣ በዌራ እና በዌራ ዲጆ ወረዳዎች የተመዘገበው የመራጭ ሕዝብ ቁጥር ከተጨባጩ የሕዝብ ብዛትና ከዞኖቹ ነባራዊ ሁኔታ ጋር የማይገናኝ በመሆኑ አጠቃላይ ሂደቱን እንደማይቀበሉ አስታውቀዋል።

በሃላባ 1 እና 2 ምርጫ ክልሎች ለክልል ምክር ቤት በጥቅሉ 5 መቀመጫዎች (ወንበሮች) ያሉ ሲሆን፣ ነፃነት እና እኩልነት ፓርቲም ለነዚህ ወንበሮች 5 ዕጩዎችን አቅርቦ ነበር። ቦርዱ ሁለቱም ዕጩዎች የአንድ ፓርቲ አባላት በመሆናቸው ፓርቲው በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጥበት ደብዳቤ ጽፎ የነበረ ሲሆን፣ ፓርቲውም “ሁለቱም ዕጩዎቻችን ቢሆኑም፣ የሕዝብ እውነተኛ ድምፅ ሊከበር ይገባል” የሚል አቋም በመያዝ የይፋዊ አቤቱታውን መውጣት አምኖበት መፈረሙን ወይዘሮ ነቢሃ ለ“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል።

የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ ሰኔ 10 ቀን 2018 ዓ.ም. ምሽት ላይ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ በአሁኑ ወቅት ቅሬታ ከቀረበባቸው 129 የምርጫ ክልሎች መካከል 75ቱ ውድቅ መደረጋቸውንና 10ሩ ደግሞ በንግግር መነሳታቸውን ጠቅሰው፤ በሀላባ 1 ምርጫ ክልል ላይ ግን ድጋሚ ቆጠራ እንዲደረግ መወሰኑን ይፋ አድርገዋል።

ሰብሳቢዋ ጉዳዩ በአንድ ፓርቲ ውስጥ ባሉ ሁለት ዕጩዎች መካከል የተፈጠረ የውጤት ውዝግብ መሆኑን ገልጸው፤ ቦርዱ በቀረበው አቤቱታ ላይ መዋቅራዊ ጥሰት መኖሩን በማመኑ በአሁኑ ወቅት ድጋሚ የድምፅ ቆጠራ በይፋ እየተካሄደ መሆኑን አስታውቀዋል። ዋና ሰብሳቢዋ አክለውም፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች እውነተኛነቱን ያረጋግጡ ዘንድ በቆጠራው ወቅት እንዲገኙ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን፣ ተፎካካሪዎቹ በአካል ካልተገኙ ግን ቦርዱ በሕጉ መሠረት ቆጠራውን ብቻውን አከናውኖ ማጠቃለያውን ይፋ እንደሚያደርግ አስገንዝበዋል። (ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)