የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰኔ 10 ቀን 2018 ዓ.ም. ምሽቱን ይፋ ካደረጋቸው የምርጫ ክልል ውጤቶች መካከል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የምርጫ ክልል 11 ውጤት አንዱ ሲሆን፣ ገዢው ብልፅግና ፓርቲ ዕጩ ባላቀረበበት በዚህ ምርጫ ክልል የትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት ቅንጅት ዕጩ የነበሩት እና የፓርላማ አባሉ ዶ/ር አበባው ደሳለው ድል ሳይቀናቸው ቀርቷል።
በዚህ የምርጫ ክልል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት (ፓርላማ) አብላጫ ድምፅ በማግኘት ያሸነፉት በግል የተወዳደሩት የሪፍት ቫሊ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አበበ ገመቹ መሆናቸውን ቦርዱ አስታውቋል።
ምርጫ ቦርድ ትናንት ይፋ ካደረጋቸው 723 ውጤቶች መካከል 5ቱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውጤቶች ሲሆኑ፤ ከእነዚህም ውስጥ 2ቱ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲሁም 3ቱ ለክልል (የከተማ አስተዳደር) ምክር ቤት የቀረቡ ናቸው። ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውጤታቸው ይፋ ከተደረገባቸው መካከል አንዱ የሆነው የምርጫ ክልል 11 እጅግ በርካታ ፓርቲዎችና ዕጩዎች የተፎካከሩበት ነበር።
በዚህ የምርጫ ክልል ስር አንድ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አኢዴፓ)፣ የወላይታ ሕዝቦች ነፃነት ንቅናቄ፣ ራያ ራዩማ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ ሕዳሴ ፓርቲ፣ ሰላም ለኢትዮጵያ ጥምረት፣ አዲስ ትውልድ ፓርቲ፣ ኢዜማ፣ ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት፣ የወሎ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ እና የግል ተወዳዳሪዎች ቀርበውበታል።
በጥቅሉ 59 ሺህ 159 መራጮች በተመዘገቡበት በዚህ ምርጫ ክልል፣ በግል የተወዳደሩት አቶ አበበ ገመቹ 10 ሺህ 459 (18 በመቶ) ድምፅ በማግኘት አብላጫ ድምፅ አስመዝግበው ማሸነፋቸውን ቦርዱ አረጋግጧል።
በዚህ ምርጫ ክልል ዕጩ ሆነው የቀረቡት ታዋቂው ፖለቲከኛ ዶ/ር አበባው ደሳለው፣ በ6ኛው አገራዊ ምርጫ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄን (አብን) ወክለው የፓርላማ አባል ሆነው ተመርጠው የነበረ ቢሆንም፣ በቅርቡ የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲን (ኢሕአፓ) በመቀላቀል፣ ፓርቲያቸው የሚገኝበትን የትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት ቅንጅትን በመወከል በዚህ 7ኛው ምርጫ ዕጩ ሆነው ቢቀርቡም ሳይመረጡ ቀርተዋል።
ይህ የምርጫ ክልል ገዢው ብልፅግና ፓርቲ ምንም ዓይነት ዕጩ ሳያቀርብባቸው ከተዋቸው 3 የአዲስ አበባ ምርጫ ክልሎች መካከል አንዱ ነው።
ቦርዱ ቀደም ሲል በ3ኛው ዙር የውጤት መግለጫው ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት፣ ከመጀመሪያዎቹ የብልፅግና ዕጩ ከሌለባቸው የምርጫ ክልሎች ውስጥ አንዱን የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) መሪ እና ዕጩ አቶ ኢዮብ መሳፍንት ማሸነፋቸው መገለጹ ይታወሳል።
በዚህም መሠረት ብልፅግና ፓርቲ ባልተወዳደረባቸው በእነዚህ የምርጫ ክልሎች ውስጥ እስካሁን ይፋ በተደረጉት ውጤቶች መሠረት አንዱን ወንበር ኢዜማ፣ ሁለተኛውን ወንበር ደግሞ የግል ዕጩው አቶ አበበ ገመቹ የወሰዱት ሲሆን፤ ቀሪው ሦስተኛው የንፋስ ስልክ ላፍቶ ምርጫ ክልል 23 ውጤት እስካሁን በቦርዱ ይፋ አልተደረገም።
በትናንትናው ዕለት ውጤቱ የታወጀው ሌላኛው የአዲስ አበባ የፓርላማ መቀመጫ የምርጫ ክልል 25 ሲሆን፤ በዚህ ምርጫ ክልል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተወዳደሩት የገዢው ብልፅግና ፓርቲ ዕጩ አቶ እሸቱ እሸትቤት ነጋሽ አብላጫ ድምፅ በማግኘት ማሸነፋቸው ተገልጿል።
በዚህ ምርጫ ክልል ስር ሰላም ለኢትዮጵያ ጥምረት፣ ሕዳሴ ፓርቲ፣ የወሎ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ ብልፅግና፣ ኢዜማ፣ ጎጎት ለጉራጌ አንድነት፣ ትብብር ለኢትዮጵያ እና ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲዎች በዕጩነት ተሳትፈውበት እንደነበር ተመልክቷል። (ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)




