የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የቀጠራቸው ጊዜያዊ የምርጫ አስፈጻሚዎች ቀሪው 60 በመቶ ክፍያቸው እና የመራጮች ምዝገባ በተራዘመባቸው 14 ቀናት ሊታሰብላቸው የሚገባው ሙሉ አበል እንዳልተከፈላቸው በመግለጽ ቅሬታ አቀረቡ። ምርጫ ቦርድ በበኩሉ፣ የምርጫ አስፈጻሚዎች ቀሪው ክፍያ እንዲፈጸምላቸው መጀመሪያ ከቦርዱ የተረከቧቸውን ንብረቶች ሙሉ በሙሉ ማስረከብ እንዳለባቸው አስታውቋል።
ቦርዱ ዘግይተው ምርጫ በጀመሩ አካባቢዎች ጭምር በጥቅሉ 259 ሺህ 894 አስፈጻሚዎችን በጊዜያዊ ሠራተኝነት ቀጥሮ እንዳንቀሳቀሰ የተገለጸ ሲሆን፣ ከምርጫ አስፈፃሚዎቹ ጋር በገባው ውል መሠረት የመጀመሪያው ዙር 40 በመቶ ክፍያ የመራጮች ምዝገባ በተጠናቀቀ በ15 ቀናት ውስጥ መፈጸም ነበረበት።
ይሁን እንጂ “ራሳችንን ለከፍተኛ በደልና እንግልት አሳልፈን ሰጥተናል” በሚል አስፈጻሚዎቹ ለቦርዱ የላኩትንና “ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተመለከተችውን አቤቱታ እንደሚያሳየው፣ “ከየካቲት 20 ጀምሮ ውል የወሰድን ቢሆንም፣ በየደረጃው የተፈጸሙብን የውል ጥሰቶች ዛሬም ድረስ ቀጥለዋል” ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጸዋል።
አስፈጻሚዎቹ ሥራ በጀመሩ በ15 ቀናት ውስጥ ሊሰጣቸው የሚገባው የ40 በመቶ ቅድሚያ ክፍያ ለወራት መዘግየቱን፣ እንዲሁም ያገለገሉባቸው ተጨማሪ 14 ቀናት ክፍያ እና የስልጠና አበል ታሳቢ ሳይደረግ እስካሁን መቆየቱን ጠቅሰዋል። ይህ የክፍያ መዘግየት በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው ላይ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጫና እየፈጠረባቸው መሆኑን በመግለጽ፣ ውዝፍ ክፍያዎቹ በሙሉ በአስቸኳይ እንዲሰረዙላቸው ጠይቀዋል።
የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ ትላንት ሰኔ 10 ቀን 2018 ዓ.ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ምርጫ ቦርድ የመጀመሪያውን ዙር የ40 በመቶ ክፍያ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ መክፈሉን ገልጸዋል። ሰብሳቢዋ “ይህንን ለመክፈል ትልቅ ችግር ገጥሞን የነበረው በሶማሌ እና በአፋር ክልሎች ነበር፤ የምርጫ አስፈጻሚዎቻችን የባንክ አካውንት ስላልነበራቸው የቦርዱ ሠራተኞች በቦታው ተገኝተው ገንዘብ በካሽ (በጥሬ ገንዘብ) በማውጣት ከፍለዋል” ብለዋል።
ቀሪውን 60 በመቶ ክፍያ በተመለከተ ግን፣ ክፍያው የሚፈጸመው የምርጫ አስፈጻሚዎች ከቦርዱ የተቀበሉትን ንብረት ሙሉ በሙሉ መመለስ ሲችሉ ብቻ እንደሆነ ሰብሳቢዋ በግልጽ አስታውቀዋል። በአሁኑ ወቅት የንብረት ማጣራት ሥራ እየተሠራ መሆኑንና ምንም ዓይነት የቦርዱ ንብረት የሌለባቸው መሆኑ የተረጋገጡ አስፈጻሚዎችን የመክፈል ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ አክለዋል።
ቦርዱ የመራጮች ምዝገባ ሂደትን ለ14 ቀናት ማራዘሙን መጋቢት 30 ቀን ለምርጫ አስፈጻሚዎች በጻፈው ደብዳቤ አስታውቆ የነበረ ሲሆን፣ ለተራዘሙት ቀናትም ተጨማሪ ክፍያ የሚፈጸምላቸው መሆኑን በወቅቱ ማሳወቁ ይታወሳል። ይህንን አስመልክቶ ቦርዱ ለ“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” በሰጠው ምላሽ፤ ለ14ቱ ተጨማሪ ቀናት የሚደረገው ክፍያ በአሁኑ ወቅት ከቀሪው 60 በመቶ ክፍያ ጋር አብሮ የሚፈጸም መሆኑን አረጋግጧል።
ከዚህ ቀደም ለምርጫ አስፈጻሚዎች የሥራ ጊዜው በ14 ቀናት በመጨመሩ ምክንያት፣ ቦርዱ ከ1.5 እስከ 1.6 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት እንዲጠይቅ ማስገደዱን “ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” መዘገቧ ይታወሳል። (ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)




