የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህን ጨምሮ የታዋቂ ፖለቲከኞች የምርጫ ውጤት ይፋ ተደረገ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የ7ኛውን ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ ውጤት የማረጋገጥ ሂደቱን በመቀጠል፣ የ723 የምርጫ ክልሎችን ውጤት ማፅደቁን ዛሬ ሰኔ 10 ቀን 2018 ዓ.ም. በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታወቀ።

ቦርዱ በ3 ዙር ካወጃቸው ውጤቶች በተጨማሪ ዛሬ የ40 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት (የፓርላማ) እና የ35 የክልሎች ምክር ቤቶችን ዝርዝር ውጤት ይፋ አድርጓል።

ቦርዱ ምሽቱን በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቀው፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በተወዳደሩባቸው የምርጫ ክልሎች አብላጫ ድምፅ ማግኘት ችለዋል።

በተጨማሪም በምርጫው በግል ዕጩነት የቀረቡት አንጋፋው ፖለቲከኛ ዶ/ር ዲማ ነጎ እና ያለተፎካካሪ የተወዳደሩት የአዲስ ትውልድ ፓርቲ (አትፓ) ፕሬዝዳንት አቶ ሰለሞን ታፈሠ በተወዳደሩባቸው የምርጫ ክልሎች ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መመረጣቸው ፀድቆላቸዋል።

በክልል ምክር ቤት ውድድር በኩል ደግሞ፣ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የምክር ቤት ዕጩ የነበሩት የከተማዋ የሰላምና ጸጥታ ኃላፊ ሊዲያ ግርማ አብላጫ ድምፅ ማግኘታቸው የተገለጸ ሲሆን፤ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጎፋ ዙሪያ ምርጫ ክልል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተወዳደሩት የብልፅግና ፓርቲ ዕጩ አቶ ተስፋዬ በልጅጌ ማሸነፋቸው ተረጋግጧል።

የቦርዱ የቴክኒካል አማካሪ አርማዬ አሰፋ ቦርዱ ዛሬ ካፀደቃቸው ውጤቶች ውስጥ 40 መቀመጫዎች ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲሁም 35 መቀመጫዎች ለክልል ምክር ቤቶች የጸደቁ መሆናቸውን ጠቅሰው ዝርዝሩን አቅርበዋል።

በዚህም መሠረት ከታወጁት 40 የፓርላማ ወንበሮች መካከል 23ቱን ገዢው ብልፅግና ፓርቲ ሲያሸንፍ፣ 14ቱ መቀመጫዎች ወደ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ገብተዋል፤ ቀሪዎቹን 3 ወንበሮች ደግሞ የግል ዕጩዎች ማሸነፋቸው ተገልጿል።

በአማራ ክልል ይፋ ከተደረጉት 9 መቀመጫዎች ውስጥ ገዢው ብልፅግና ፓርቲ 4ቱን ሲያሸንፍ፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ቀሪዎቹን ወንበሮች ተከፋፍለዋቸዋል፤ በዚህም መሠረት የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) 3 መቀመጫዎችን፣ ነፃነት እና እኩልነት ፓርቲ (ነእፓ) 1 መቀመጫን፣ እንዲሁም የአማራ ዴሞክራሲ ኃይል ንቅናቄ (አዴኃን) ቀሪውን 1 መቀመጫ ማሸነፍ ችለዋል።

በኦሮሚያ ክልል ደግሞ ውጤታቸው ከታወጀው 6 መቀመጫዎች መካከል ግማሹን ማለትም 3ቱን ወንበሮች ብልፅግና ፓርቲ ሲወስድ፣ 2ቱ መቀመጫዎች በግል ዕጩዎች ተይዘዋል፤ ቀሪው 1 ወንበር ደግሞ ለአዲስ ትውልድ ፓርቲ (አትፓ) ሆኗል።

በደቡብ ኢትዮጵያ እና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎችም ገዢው ፓርቲ እና ተቃዋሚዎች መቀመጫዎችን ተጋርተዋል። በደቡብ ኢትዮጵያ ከተረጋገጡት 6 መቀመጫዎች መካከል 3ቱን ብልፅግና ፓርቲ ያሸነፈ ሲሆን፣ ቀሪዎቹን ሦስት ወንበሮች የወላይታ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ወሕዴግ)፣ የጌዲዮ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ጌሕዴድር) እና የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) እያንዳንዳቸው አንድ አንድ ወንበር በመውሰድ ተከፋፍለዋቸዋል።

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል በበኩሉ ይፋ ከተደረጉት 4 መቀመጫዎች ውስጥ ብልፅግና ፓርቲ 2ቱን ማሸነፉ ሲረጋገጥ፣ ነእፓ 1 ወንበር እንዲሁም ኢዜማ 1 ወንበር አግኝተዋል።

በአፋር፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች እና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የታየው የፓርላማ ወንበሮች ክፍፍል ደግሞ፣ በአፋር ክልል ከታወጁት 3 መቀመጫዎች ውስጥ 2ቱን ብልፅግና ፓርቲ ሲወስድ፣ ቀሪውን 1 መቀመጫ የአፋር ሕዝብ ፓርቲ (አሕፓ) ማሸነፍ ችሏል። በአንጻሩ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ለውድድር የቀረቡት 2 የፓርላማ መቀመጫዎች ሙሉ በሙሉ ወደ ተቃዋሚዎች የሄዱ ሲሆን፣ አንደኛውን ወንበር ኢዜማ ሁለተኛውን ደግሞ ነእፓ አሸንፈውታል። በአዲስ አበባ ከተማ ከተረጋገጡት ሁለት መቀመጫዎች መካከል ደግሞ አንዱ ወደ ገዢው ፓርቲ ብልፅግና ሲያመራ፣ ሁለተኛውን ወንበር የግል ዕጩ ወስደውታል።

በመጨረሻም በሐረሪ፣ በሲዳማ እና በሶማሌ ክልሎች የተመዘገቡት ውጤቶች ገዢው ፓርቲ ሙሉ በሙሉ የበላይነት የወሰደባቸው ሆነዋል። የእነዚህ የሦስቱ ክልሎች ስድስት የፓርላማ መቀመጫዎች ውጤት እንደሚያሳየው፣ በእያንዳንዱ ክልል የቀረቡት ሁለት ሁለት መቀመጫዎች በድምሩ ስድስቱም ወንበሮች ያለ ምንም ተካፋይ ሙሉ በሙሉ በብልፅግና ፓርቲ ተጠቃለው ተወስደዋል።

ከምርጫው አፈጻጸም ጋር ተያይዞ በቀረቡ አቤቱታዎች ዙሪያ ማብራሪያ የሰጡት የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ፤ ከዚህ ቀደም ቅሬታ ቀርቦባቸው የነበሩ የምርጫ ውጤቶች ላይ ተጨማሪ 9 የምርጫ ክልሎችን አቤቱታ ቦርዱ በመቀበሉ፣ በጥቅሉ ቅሬታ የቀረበባቸው የምርጫ ክልሎች ቁጥር ከ120 ተነስተው 129 መድረሳቸውን ገልጸዋል።

ሰብሳቢዋ አክለውም፣ በአሁኑ ወቅት 253 የሚሆኑ የምርጫ ክልል ውጤቶችን የማረጋገጥና የኦዲት ሥራዎችን በመሥራት ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

የቦርዱ የቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ማስተባበሪያ ሥራ ክፍል ኃላፊ ቀነኒ እንሰርሙ በበኩላቸው፣ ከቀረቡት 129 አጠቃላይ ቅሬታዎች ውስጥ እስካሁን 86 የሚሆኑት ውሳኔ ማግኘታቸውን አስታውቀዋል።

በዚህም መሠረት 75 የሚሆኑት የምርጫ ክልል አቤቱታዎች የቀረቡባቸው ማስረጃዎች እና ምስክሮች ከተሰሙ በኋላ በቂ ሆነው ባለመገኘታቸው በቦርዱ ውድቅ ተደርገዋል። 10 የሚሆኑት የፖለቲካ ፓርቲዎች አቤቱታ አቅራቢዎች ከቦርዱ ጋር ከተነጋገሩ በኋላ ቅሬታቸውን በራሳቸው ፍላጎት አንስተዋል።

በሀላባ 1 ምርጫ ክልል ላይ በቀረበው የሕግ ጥሰት አቤቱታ መሠረት ድጋሚ የድምፅ ቆጠራ እንዲደረግ ተወስኖ በአሁኑ ወቅት ቆጠራው እየተካሄደ ይገኛል።

እንደ ኃላፊዎቹ ገለጻ ከሆነ፣ እስካሁን መፍትሔ ሳያገኙ የቆዩት ቀሪዎቹ 43 የምርጫ ክልል ቅሬታዎች በአሁኑ ወቅት በጥብቅ እየተመረመሩ የሚገኙ ሲሆን፣ እስከ ነገ ሰኔ 11 ቀን 2018 ዓ.ም. ድረስ የመጨረሻ ውሳኔ እንደሚሰጥባቸውና ተጨማሪ ውጤቶችም ይፋ መደረጋቸውን እንደሚቀጥሉ ተገልጿል። (ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)