ግንቦት 24፣ 2018 ቀን 2018 ዓ.ም. በተካሄደው 7ኛው ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ በአማራ ክልል በሚገኙ አንዳንድ ዞኖችና ወረዳዎች ውስጥ የምርጫ ሂደቱ በጸጥታ ችግር ምክንያት ተቋርጦ የነበረ ቢሆንም፣ የመንግሥት የአካባቢ መዋቅሮች “ሂደቱ በስኬት ተጠናቋል” የሚል የግምገማ ውጤት ማውጣታቸው መታዘባቸውን ነዋሪዎች ገለጹ።
በምዕራብ ጎጃም ዞን ደንበጫ ወረዳ በምርጫው ዕለት የነበረውን ሁኔታ ያስረዱት አቶ በቃሉ ጊዜነው የተባሉ ነዋሪ፣ “በወረዳው ደንበጫ ከተማ የምርጫ ሂደቱ ጠዋት 12፡00 ሰዓት ላይ ቢጀመርም፣ ብዙም ሳይቆይ በተከፈተ ተኩስ ምክንያት ሙሉ በሙሉ ተቋርጧል። ተኩሱ እስከ ቀን 10፡00 ሰዓት ድረስ ይሰማ ስለነበር ምርጫው በትክክል አልተካሄደም” ሲሉ አስረድተዋል።
ይሁን እንጂ ይህ ሁኔታ በግልጽ እየታወቀ የወረዳው ኮሙኒኬሽን ቢሮ “በዞኑ በሁሉም የምርጫ ክልሎች የተካሔደው 7ኛው ሃገራዊ ምርጫ በሰላም መጠናቀቁንም [የዞኑ ፀጥታ] መምሪያው ገልጿል” የሚል መግለጫ ማውጣቱ እጅግ እንዳስገረማቸው የዓይን እማኙ ገልጸዋል።

በተመሳሳይ ሁኔታ በፍኖተ-ሰላም፣ በቲሊሊ እና በቋሪት ወረዳዎችም እንዲሁ ሂደቱ በተኩስ ምክንያት የተቋረጠባቸው ክስተቶች እንደነበሩ የዓይን እማኞች ለ“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” በስልክ አረጋግጠዋል።
በቋሪት ወረዳ ገበዘ ማርያም ቀበሌ ነዋሪ የሆኑ አንድ እማኝ እንደገለጹት፣ የምርጫ ሂደቱ ጠዋት ቢጀመርም በአካባቢው በነበረው የተኩስ ልውውጥ ምክንያት ተቋርጧል። የዓይን እማኙ ይህንን ይበሉ እንጂ፣ የቋሪት ወረዳ ኮሙኒኬሽን ቢሮ በይፋዊ የፌስቡክ ገጹ ባወጣው የግምገማ ውጤት፤ በአካባቢው ግጭት ተከስቶ የነበረ መሆኑን በከፊል አምኖ፣ የምርጫ ሂደቱን ግን “በስኬት ማጠናቀቁን” መግለጹን “ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ከማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ ላይ መመልከት ችላለች።
በደቡብ ጎንደር ዞን በደብረ ታቦር ከተማ፣ በስማዳ ወረዳ እና በእስቴ ወረዳ በሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች በተመሳሳይ ሁኔታ የምርጫው ሂደት በተኩስ መቋረጡን ደኅንነታቸው ስጋት ላይ እንዳይወድቅ ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የዓይን እማኝ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል። እማኙ “እውነታው ይሄ ቢሆንም የገዢው ፓርቲ አባላትና ኃላፊዎች ግን ‘ሂደቱ በስኬት ተጠናቋል’ የሚል መግለጫ እየሰጡ መሆኑ ተገቢ አይደለም” ብለዋል።
በሰሜን ጎጃም ዞን በሚገኙ ወረዳዎችም ተመሳሳይ የተኩስ ልውውጦች የነበሩ ሲሆን፣ አቶ ላቀው ዘለቀ እና አቶ ታለማ ይበይን የተባሉ የአካባቢው ነዋሪዎች በስልክ በሰጡት መረጃ መሠረት በይልማና ዴንሳ እና በሜጫ ወረዳዎች በነበሩ የምርጫ ጣቢያዎች ላይ በተፈጠሩ የጸጥታ ችግሮች ምክንያት የድምፅ መስጠት ሂደቱ በይፋ ተቋርጦ ውሏል።
ይሁንና የሰሜን ጎጃም ዞን ኮሙኒኬሽን ቢሮ በበኩሉ፣ በዞኑ እና በየወረዳው የነበረው ምርጫ “ሰላማዊ በሆነ መንገድ ስኬታማ ሆኖ ተጠናቀቀ” የሚል የግምገማ ውጤቱን በማኅበራዊ ትስስር ገጹ በኩል አጋርቷል።
ጉዳዩን በተመለከተ በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያላቸውን ምልከታ ለማካተት “ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ወደ አማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)፣ ወደ ኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ)፣ እና የክልሉ አመራሮች ተደጋጋሚ የስልክ ጥሪዎችን ብታደርግም ምላሽ ማግኘት አልተቻለም።
እስከ አሁን ባለው መረጃ፣ በየአካባቢዎቹ የምርጫ ሂደቱ የተቋረጠባቸውን ቦታዎች ዝርዝርና ቀጣይ ውሳኔዎችን በተመለከተ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያወጣው የተለየ ዝርዝር መግለጫ ባይኖርም፣ በገዢው ፓርቲ አስተዳደሮች ሪፖርት እና በነዋሪው ምስክርነት መካከል ያለው ግልጽ መቃረን ግን በሂደቱ ላይ ከፍተኛ ጥያቄ እያስነሳ ይገኛል።
ይህንን የዓይን እማኞች እና የአካባቢ ባለሥልጣናት ሪፖርት መቃረን አስመልክቶ የ“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ባልደረቦች፣ ምርጫ ቦርድ ሰኔ 5 ቀን 2018 ዓ.ም. ለጋዜጠኞች መግለጫ በሰጠበት ወቅት በጥያቄ መልክ አንስተውት ነበር። ቦርዱ በሰጠው ምላሽ፤ “ምርጫን በተመለከተ ይፋዊ ውጤት የሚታወቀውም ሆነ የምርጫው አጠቃላይ አፈጻጸም ሂደት የሚገለጸው በምርጫ ቦርድ በኩል ብቻ መሆኑን በተደጋጋሚ ተናግረናል” በማለት የአካባቢ ባለሥልጣናት የሚሰጧቸው መግለጫዎች ኦፊሴላዊ አለመሆናቸውን ምላሽ ሰጥቷል።
ቦርዱ አክሎም፣ ከዚህ ውጭ የምርጫውን አፈጻጸምም ሆነ ውጤትን በተመለከተ በማንኛውም ሌላ አካል (በመንግሥት መዋቅርም ሆነ በፓርቲዎች) የሚሰጡ መግለጫዎች በሕግ ፊት ምንም ዓይነት ተቀባይነትና ሕጋዊነት የሌላቸው መሆኑን በይፋ አብራርቷል። (ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)




