ምርጫ ቦርድ የቁጫ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ያቀረበውን “የውጤት ይሰረዝልኝ” አቤቱታ ውድቅ አደረገ

​የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የቁጫ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቁሕዴፓ) በቁጫ ምርጫ ክልል የተካሄደው የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ውጤት እንዲሰረዝለት ያቀረበውን ይፋዊ አቤቱታ ውድቅ ማድረጉን አስታወቀ።

 ቦርዱ ሰኔ 9 ቀን 2018 ዓ.ም.  ለፓርቲው በጻፈውና የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ነዋይ እንግዳሸት በፈረሙበት ይፋዊ ደብዳቤ፤ ፓርቲው ያቀረበው ቅሬታ በቂ ማስረጃ ያልተደገፈ መሆኑን ገልጿል።

​የቁጫ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ “በቁጫ ምርጫ ክልል የምርጫ ሕግን የሚጥሱ ተግባራት ተፈጽመዋል” በሚል፣ የምርጫው ውጤት ሙሉ በሙሉ ተሰርዞ በድጋሚ እንዲካሄድ ለቦርዱ አቤቱታ አቅርቦ ነበር።

ምርጫ ቦርድ በበኩሉ አቤቱታውን ተከትሎ የተባለውን የምርጫ ሕግ ጥሰት ለማጣራት አጣሪ ኮሚቴ በማደራጀት ሂደቱን ሲያጠና፣ ሲያመራምር እና ሲመረምር መቆየቱን በደብዳቤው ላይ ጠቅሷል።

​ሆኖም ቦርዱ ባደረገው ማጣሪያ “ፓርቲው ያቀረበው ቅሬታ በበቂ ማስረጃ ያልተደገፈ ሆኖ ተገኝቷል” በሚል ጥያቄውን ውድቅ ማድረጉንና ውሳኔውን ለፓርቲው ማሳወቁን ገልጿል። ቦርዱ የዚህን ውሳኔ ግልባጭ በቁጫ ምርጫ ክልል በዋና ተፎካካሪነት ለተወዳደረውና ይኸው ውሳኔ ለሚመለከተው ለገዢው ብልፅግና ፓርቲም ልኳል።

​የቁጫ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ በዚሁ የምርጫ ክልል ከምርጫው ዋዜማ ጀምሮ የፌዴራል መንግሥቱ እና የክልሉ መዋቅር በተፎካካሪ ዕጩዎች ላይ እያደረሱት ነው ያለውን እስራት፣ ጫና እና መዋቅራዊ የአሠራር ጥሰቶች በተደጋጋሚ ሲያነሳ እንደነበር ይታወሳል።

 ፓርቲው የምርጫው ዕለት ሂደት ሙሉ በሙሉ ነፃነት የጎደለው እና በሕግ ጥሰት የተሞላ ነው በሚል ያቀረበው ይሄው የውጤት ይሰረዝልኝ ጥያቄ፤ ቦርዱ ካስተናገዳቸው 120 የምርጫ ክልል ቅሬታዎች መካከል አንዱ የነበረ ቢሆንም፣ በቦርዱ አጣሪ ቡድን ውድቅ ከተደረጉት የመጀመሪያዎቹ ይፋዊ ውሳኔዎች መካከል ሆኗል።

ጉዳዩን በተመለከተ የቁህዴፓ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ገነነ ገደቡ ለ “ምርጫ 2018-ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” እንደገለጹት ቦርዱ በዛሬው ዕለት ሰኔ 9 2018 የጻፈው ደብደቤን እንደማንኛውም ሰው በማህበራዊ ሚዲያ መመልከታቸውን ተናግረዋል፡፡

ደብበዳቤው በእጃቸው የደረሳቸው ሳይሆን በማህበራዊ መመለከታቸውንና ይህንን አስመልክቶ ፓርቲው መግለጫ ለማውጣት ውይይት ላይ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

ፕሮፌሰር ገነነ ቦርዱ ፓርቲው ያቀረበውን የትኛውን የሕግ ጥሰት ትክክል አይደለም በሚል ውድቅ ያደረገው የሚለው ግልጽነት የጎደለው ነወ በማለት ነቅፈዋል፡፡ (ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)