የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የ7ኛውን ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ ውጤት የማረጋገጥ ሂደቱን በመቀጠል፣ ሰኔ 12 ቀን 2018 ዓ.ም. ምሽት በስካይላይት ሆቴል በሰጠው ዕለታዊ ጋዜጣዊ መግለጫ ተጨማሪ የጸደቁ ውጤቶችን ይፋ አደረገ ።
ዛሬ ውጤታቸው ከተነገሩ ተመራጮች መካከል ከፍተኛውን ድምጽ ያገኙት አቶ ቲያ ሚዮ አርሳዋ ናቸው። አቶ ቲያ ሚዮ በኦሮሚያ ክልል ያቤሎ የምርጫ ክልል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የብልጽግና ፓርቲን ወክለው የተወዳደሩ ሲሆን፣ 242,357 ድምጽ በማግኘት ተመርጠዋል።
በተቃራኒው እጅግ ዝቅተኛ በሆነ ድምፅ መመረጣቸው የፀደቀላቸው ዕጩ ቤዛ የማነ በርሄ ናቸው። ቤዛ የማነ በድሬዳዋ አስተዳደር፣ አዲጋ ፈለማ የክልል ምክር ቤት ምርጫ ክልል (ለ3 መቀመጫዎች በተካሄደው ምርጫ) የነጻነትና እኩልነት ፓርቲን ወክለው ተወዳድረው 43 ድምጽ በማግኘት አሸናፊ ከሆኑት ሦስት ዕጩዎች አንዱ መሆን ችለዋል። ቤዛ የማነን ብልፅግና ፓርቲ ተወዳዳሪ አላቀረበባቸውም።
በዚህ የምርጫ ጣቢያ የተመዘገቡ መራጮች ቁጥር 3,002 ሲሆን፣ በምርጫ ክልሉ የተመረጡት ሌሎቹ ሁለት የብልፅግና ዕጩዎች 2,910 እና 2,857 ድምፅ ማግኘታቸው ተገልጿል።
የቦርዱ የቴክኒክ አማካሪ አርማዬ አሠፋ ዛሬ በሰጡት ማብራሪያ ቦርዱ ካፀደቃቸው አዳዲስ ውጤቶች መካከል ይፋ የሆኑት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት (ፓርላማ) ውጤቶች ብዛት 23 ሲሆን፣ 20 ወንበሮችን ብልፅግና ማሸነፉ ተገልጿል፤ ቀሪዎቹን ሦስት ወንበሮች፣ በኦሮሚያ አንድ የግል ዕጩ፣ በአማራ አንድ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ዕጩ፣ እና በደቡብ ኢትዮጵያ አንድ የሰላም ለኢትዮጵያ ጥምረት ዕጩ ማሸነፋቸው ታውቋል።
በዛሬው የቦርዱ መግለጫ ከተደመጡት የታዋቂ ፖለቲከኞች ውጤቶች መካከል፣ የኢፌዴሪ የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስትር ዶ/ር አብርሃም በላይ በአዲስ አበባ ምርጫ ክልል 3፣ 13,530 ድምፅ በማግኘት መመረጣቸው የታወጀ ሲሆን፣ በአማራ ክልል በራያ ቆቦ ምርጫ ክልል፣ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ሊቀ መንበር እንዲሁም የኢኖቪሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶ/ር በለጠ ሞላ ጌታሁን 134 ሺህ 624 ድምፅ በማግኘት መመረጣቸው ታውቋል።
በኦሮሚያ ክልል የመንዲ ምርጫ ክልል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በግል ዕጩነት ብቻቸውን ለውድድር የቀረቡት አቶ ቀጄላ መርዳሳ 129 ሺህ 299 ድምፅ በማግኘት አሸናፊ መሆናቸው ተገልጿል።
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ በቢጣ ጌሻ ምርጫ ክልል የሰላም ለኢትዮጵያ ጥምረት ዕጩ አቶ ሰለሞን አየለ 50 ሺሕ 941 ድምፅ በማግኘት በአብላጫ ድምፅ ለፓርላማ ተመርጠዋል።
በተመሳሳይ አጠቃላይ 145 ወንበሮች ያሏቸው 30 የክልል ምክር ቤት ውጤቶች ይፋ ተደርገዋል። ከነዚህ ውስጥ 132ቱን ብልፅግና ፓርቲ ሲያሸንፍ 12ቱን መቀመጫዎች ደግሞ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንደወሰዷቸው ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ በአዲስ አበባ፣ በደቡብ ኢትዮጵያ እና በድሬዳዋ አንድ፣ አንድ ዕጩዎች ተመርጠውለታል። ነፃነት እና እኩልነት ፓርቲ (ነእፓ) በድሬዳዋ 3 ዕጩዎች ሲመረጡለት፣ በሲዳማ የሲዳማ አንድነት ፓርቲ 2 ወንበሮችን፣ ሕዳሴ ፓርቲ በአዲስ አበባ አንድ ወንበር፣ እንዲሁም ሰላም ለኢትዮጵያ ጥምረት በደቡብ ኢትዮጵያ አንድ ወንበር አሸንፈዋል።
በሶማሌ ክልል ለክልል ምክር ቤት፣ በደጋቡር ከተማ ምርጫ ክልል የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ ሙሃመድ ዑመርን ጨምሮ የብልፅግና ዕጩዎች ሲያሸንፉ፣ ከዚሁ ምርጫ ክልል ከአምስቱ መቀመጫዎች አንዱን የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር (ኦብነግ) ዕጩ አቶ መሐመድ በድሪ አብዱላሂ 30 ሺህ 997 ድምፅ በማግኘት አሸንፈዋል።
በመጨረሻም ቦርዱ በዛሬው መግለጫው በአሁኑ ወቅት በኦዲት እጅ የሚገኙ የምርጫ ክልሎች በጥቅሉ 129 መድረሳቸውን በድጋሚ ያረጋገጠ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ 43 የምርጫ ክልሎች አሁንም ድረስ እልባት አላገኙም።
የቦርዱ የቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ማስተባበሪያ ሥራ ክፍል ኃላፊ ቀነኒ እንሰርሙ በሰጡት ማብራሪያ፣ አቤቱታ በቀረበበት በሀላባ 1 ምርጫ ክልል ላይ የተወሰነው ድጋሚ የድምፅ ቆጠራ በአሁኑ ወቅት በይፋ እየተካሄደ ይገኛል።
በዚህ የምርጫ ክልል ተወዳዳሪ የነበሩት የነፃነት እና እኩልነት ፓርቲ (ነእፓ) የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ወይዘሮ ነቢሃ መሐመድ በምርጫው ሂደት ላይ መዋቅራዊ የሕግ ጥሰት መፈጸሙን በመጥቀስ ይፋዊ አቤቱታ ማቅረባቸውን “ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” መዘገቧ ይታወሳል። (ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)



