ሰባተኛውን ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ ተከትሎ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ድጋሚ የድምፅ ቆጠራ እንዲደረግባቸው በወሰነባቸው በርካታ የምርጫ ክልሎች ላይ ሂደቶቹ ቢጠናቀቁም፣ ቦርዱ ውጤቶቹን እስካሁን ይፋ እንዳላደረገ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ገለጹ። በአንጻሩ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሚገኘው የሃላባ 1 ምርጫ ክልል የተፈጠረውን አለመግባባት ለመፍታት የተደረጉ ተከታታይ ቆጠራዎች ባለመሳካታቸው፣ የድምፅ ቆጠራው አሁን ለአራተኛ ጊዜ በድጋሜ ሊካሄድ መሆኑን አቤቱታ አቅራቢዋ ገልጸዋል።
በሃላባ 1 ምርጫ ክልል የነፃነት እና እኩልነት ፓርቲ (ነእፓ) ዕጩዎችና አባላት መካከል በተፈጠረ አለመተማመንና ቆጠራው ላይ “ስህተት ተፈጥሯል” በሚል ድጋሚ ቆጠራ እንዲካሄድ ቦርዱ መወሰኑ ይታወሳል። በዚሁ ምርጫ ክልል የነእፓ ዕጩ የሆኑት ነቢሃ ሙሐመድ ለ“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” እንደገለጹት፣ ከሲዳማ ክልል 15 የሚሆኑ የምርጫ አስፈጻሚዎች ተመድበው ሂደቱ ሦስት ጊዜ ቢካሄድም አሁንም በማጭበርበር ድርጊት ላይ ቅሬታ በመኖሩ ቆጠራው ለአራተኛ ጊዜ ሊደገም ነው።
ዕጩዋ ሂደቱን ሲያስረዱ “በመጀመሪያ በምርጫ ጣቢያዎች ላይ ተቆጠረ፣ በመቀጠል ሆሳዕና እንዲካሄድ ተወሰነ፣ ለሦስተኛ ጊዜ በዚያው በሆሳዕና በቦርዱ ውሳኔ ቆጠራ የተካሄደ ቢሆንም ማጭበርበር በመፈጠሩ ድጋሚ አቤቱታ ለቦርዱ አስገብቻለሁ” ብለዋል። ቦርዱ አቤቱታውን ተቀብሎ “እመለከተዋለሁ” ማለቱን የገለጹት ነቢሃ፣ በአሁኑ ወቅት ግን ያልተረጋገጠ ውጤት በምርጫ ጣቢያ ደረጃ እየተለጠፈ መሆኑን መታዘባቸውን ስጋታቸውን አክለዋል።
ነእፓ ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰኔ 3 ቀን 2018 ዓ.ም. የተጻፈውን፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሃላባ ቁጥር 1 ምርጫ ክልል (የሃላባ እና የስልጤ አካባቢዎች የጋራ ምርጫ ክልል) ለክልል ምክር ቤት ተወዳዳሪ ሆነው የቀረቡት ወይዘሮ ነቢሃ መሐመድ አቤቱታ “ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” በርካታ ቅሬታዎችን መያዙን መመልከቷን ከዚህ በፊት ዘግባ ነበር። ወይዘሮ ነቢሃ ለ“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” በወቅቱ በሰጡት ቃል፣ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር የእሳቸውን ስም በመጠቀም በስልጤ በኩል የቀረቡትንና በስም የሚመሳሰሏቸውን ሌላኛዋን ዕጩ ወይዘሮ ነቢያት ሁሴንን ለማሳለፍ ሲሉ ምርጫው ላይ ከፍተኛ መዋቅራዊ ጫና አሳድረዋል በሚል ቅሬታ ማቅረባቸው ይታወሳል።
የነእፓ የኦሮሚያ ክልል አስተባባሪ አቶ ዑመር ጎበና በበኩላቸው፣ ቆጠራው በስልጤ እና በሃላባ በኩል ከተከናወነ በኋላ ውጤቱ ከመጀመሪያው ጋር ተመሳሳይ መሆኑ እየተገለጸ ቢሆንም ቦርዱ ግን ውሳኔውን ይፋ አላደረገውም ብለዋል። አቶ ዑመር “በአንድ የፓርቲ አባላት መካከል የተፈጠረ በመሆኑ እንደዚህ መሆን አልነበረበትም” ካሉ በኋላ፣ ሁለቱም የሚያልፉበትን ሁኔታ ለመፍጠር ጥረት ቢደረግም እስካሁን ስምምነት ላይ መድረስ አለመቻሉን ጠቁመዋል።
ሌላው ድጋሚ ድምፅ ቆጠራ የተካሄደበት በሲዳማ ክልል የጩኮ (ጨኮ) ምርጫ ክልል ሲሆን፣ የነእፓ የሲዳማ ክልል አስተባባሪ አቶ ታደለ ታኔ ቆጠራው በሐዋሳ ሚሊኒየም አዳራሽ መከናወኑን አረጋግጠዋል። ይሁን እንጂ አራት ቀናት በወሰደው በዚህ ቆጠራ ላይ ፓርቲያቸው ታዛቢ እንዲልክ ጥሪ የቀረበለት በሦስተኛው ቀን መሆኑን የገለጹት አቶ ታደለ፣ “ቆጠራው ተጠናቋል፤ ነገር ግን የቆጠራው ውጤት በምርጫ ክልሉም ሆነ በሐዋሳ ሚሊኒየም አዳራሽ አልተለጠፈም። ሪፖርቱን እንዲያሳዩን ጥያቄ ብናቀርብም ሊያሳዩን ፈቃደኛ አይደሉም” ሲሉ ወቅሰዋል።
ነእፓ በዚህ ምርጫ ክልል የመምረጫ ወረቀት ላይ የ9 ዕጩዎቹ ስም ዝርዝርና ምልክት አለመኖሩን በማረጋገጥ አቤቱታ ማቅረቡን “ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” መዘገቧ ይታወሳል።
በተመሳሳይ በኦሮሚያ (ወልመራ)፣ በደቡብ ኢትዮጵያ (ዳሞት ወይዴ 2 እና ጨንቻ) የምርጫ ክልሎች ድጋሚ ቆጠራ እንዲካሄድ አቤቱታ ካቀረቡት መካከል የሕብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አበራ በቀለ፣ በሦስቱም ምርጫ ክልሎች ቆጠራው ቢጠናቀቅም ውጤቱ እስካሁን አለመለጠፉን ገልጸዋል።
በተለይ ወልመራ ብልፅግና ፓርቲ ያልተወዳደረበት ቢሆንም በተፎካካሪዎች አቤቱታ ቆጠራው እንዲደገም መደረጉን ጠቅሰዋል። አቶ አበራ ቦርዱ ተጨማሪ ውይይቶችና ድርድሮች እንደሚኖሩ ማሳወቁን ገልጸው፣ “ውይይቱ ውሳኔዎች ከመወሰናቸው በፊት በቦርዱ እና በፓርቲዎች መካከል ድርድሮች ይደረጋሉ፤ ቦርዱ የራሱን እውነት፣ ፓርቲዎችም የራሳቸውን እውነት ያቀርባሉ” ብለዋል። ውጤቱ ለውጥ በማያመጣባቸው ጉዳዮች ላይ ስምምነት ከተደረሰ በኋላ ቦርዱ ውጤቱን ይፋ ያደርጋል የሚል እምነት እንዳላቸውም አክለዋል።
የምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ንዋይ ሰኔ 14 ቀን 2018 ዓ.ም. ባደረጉት ይፋዊ መግለጫ፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ10 የምርጫ ክልሎች (ብርብራ፣ ገረሴ፣ ዳሞት ወይዴ 2፣ ሀገረ ሰላም፣ ጩኮ፣ ወልመራ፣ ክብረ መንግሥት፣ አሊቦ እና ቀለፎ) እንዲሁም ለክልል ምክር ቤት በ3 የምርጫ ክልሎች (ክብረ መንግሥት፣ ሐርሺሞ፣ አሚባራ እና ሃላባ 1) ላይ ድጋሚ ቆጠራ እንዲደረግ መወሰኑ ይታወሳል። በእነዚህ ክልሎች የቀረቡት አቤቱታዎች በአብዛኛው የምርጫ አስፈጻሚዎች ፍትሐዊ አለመሆንና የታችኛው የመንግሥት መዋቅር ጣልቃ ገብነት ላይ ያተኮሩ ናቸው።
የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 ክፍል አምስት ላይ ስለ ድጋሚ ድምፅ ቆጠራ በሚያትተው ድንጋጌ መሠረት፤ በቆጠራው ሂደት ላይ ግድፈት አለ በማለት ቅሬታ ሲቀርብ የምርጫ ጣቢያው ቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ ጉዳዩን መርምሮ ቢዘገይ ከ12 ሰዓት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ውሳኔ መስጠት እንዳለበት ይደነግጋል። እንደ አስፈላጊነቱም የድምፅ ቆጠራው እንዲቋረጥ ወይም ዳግም ቆጠራ እንዲካሄድ ሊደረግ እንደሚችል ቢደነግግም፣ አዋጁ ድጋሚ ድምፅ ቆጠራም ሆነ ድጋሚ ምርጫ ከተደረገ በኋላ ውጤታቸው በምን ያህል የጊዜ ገደብ ውስጥ ለሕዝብ ይፋ መደረግ እንዳለበት በግልጽ የሚያስቀምጠው ነገር የለም።
“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የድጋሚ ድምፅ ቆጠራዎቹ እና የድጋሚ ምርጫዎቹ አጠቃላይ ሂደት ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝና ውጤቱ መቼ ይፋ እንደሚደረግ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምላሽ ለማግኘት ተደጋጋሚ ሙከራ ብታደርግም እስካሁን አልተሳካላትም። (ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)




