በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ላይ ተመራጮች ያገኙት ድምፅ መካከል እጅግ የተጋነነ ልዩነት ተስተዋለ፤ ከአንድ ሺሕ በታች እና ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ድምፅ ያገኙ ተመራጮች እኩል ወደ ፓርላማ ይገባሉ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የ7ኛውን ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ ከፊል አሃዛዊ ዝርዝር ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ መረጃዎቹ በተለያዩ የምርጫ ክልሎች አሸናፊ የሆኑ ተመራጮች ባገኟቸው ድምፆች መካከል እጅግ ከፍተኛ ልዩነት እንዳለ ያሳያሉ። በአንዳንድ የምርጫ ክልሎች ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የመራጮችን ድምፅ ያገኙ ተመራጮች ቢመዘገቡም፣ በሌላ በኩል ከአንድ ሺሕ እስከ አሥር ሺሕ በሚያንስ ድምፅ ያሸነፉ ዕጩዎች ግማሽ ሚሊዮን ድምፅ ካገኙት ጋር እኩል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት (ፓርላማ) የመግባት ዕድል ማግኘታቸው ተስተውሏል።

በዚህ ረገድ በአማራ ክልል “አዲስ ቅዳም” የምርጫ ክልል የተወዳደሩት ፈተና ባዩ ሽባባው ያገኙት አጠቃላይ ድምፅ 840 ብቻ በመሆኑ፣ በምርጫው እጅግ በጣም ዝቅተኛ ድምፅ ያገኙ ተመራጭ ሆነዋል። ፈተና ባዩ በተወዳደሩበት በዚህ የምርጫ ክልል በአጠቃላይ ድምፅ የሰጡት ሰዎች ብዛት 1,916 ብቻ መሆኑ የታወቀ ሲሆን፣ እርሳቸው ያገኙት ውጤትም የአጠቃላይ መራጮቹን 44 በመቶ ይሸፍናል። እንደ ምርጫ ቦርድ አሠራር አንድ የድምፅ መስጫ ሳጥን (ኮሮጆ) ከ1,200 እስከ 1,500 የድምፅ መስጫ ወረቀቶችን ማስተናገድ የሚችል በመሆኑ፣ ፈተና ባዩ የተወዳደሩበት የምርጫ ክልል ውስጥ በትክክል የተሰጠው አጠቃላይ ድምፅ ሁለት ኮሮጆ እንኳ የማይሞላ መሆኑን መረዳት ይቻላል።

..ክልልየምርጫ ክልልየተመራጭ ሥምያገኙት ድምፅአጠቃላይ የመረጡ ሰዎች ቁጥርተመራ ያገኙት ድምፅ ከአጠቃላይ መራጮች በመቶኛ
1አማራአዲስ ቅዳምፈተና ባዩ ሽባባው8401,91644%
2ቤኒሻንጉል ጉሙዝሺናሻ ልዩፍሬህይወት አበበ ጎበና1,8812,83066%
3ደቡብ ኢትዮጵያላስካ/ባስኬቶ መደበኛካሳሁን ደለነ ደያላ3,8695,27573%
4አዲስ አበባየምርጫ ክልል 2 እና 14ዳንኤል ክብረት ብርሃኔ4,1576,36765%
5ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያሱርማ ልዩሜሪ ገርሲ ፈጠነ4,7755,19992%
6ደቡብ ኢትዮጵያአይዳ ልዩእንድሪስ ወርቁ ጉሳ4,8068,30558%
7አዲስ አበባየምርጫ ክልል 15ደበሌ ቃቢታ ሁርሳ5,2807,89267%
8አማራአርጎባ ልዩማህሙድ መሀመድ አወል6,5068,89573%
9አማራአማኑኤልዮሃንስ ጥላሁን ጌቴ6,6136,613100%
10ደቡብ ኢትዮጵያጊዶሌ መደበኛዘነበ ሳጎያ አርካይዶ6,64412,97951%

ሰንጠረዥ 1፤ እጅግ ዝቅተኛ ድምፅ ያገኙ 10 የፓርላማ ተመራጮች

በተመሳሳይ ሁኔታ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል “ሸንጎ ልዩ” የምርጫ ክልል ፍሬሕይወት አበበ ጎርፉ በ1,881 ድምፅ (66%) እንዲሁም በማዕከላዊ ኢትዮጵያ “ሳስካ/ሳስካቶ መደበኛ” የምርጫ ክልል ካሳሁን ደለነ ደያላ በ3,869 ድምፅ (73% በትክክል የመረጡ ሰዎችን ዝቅተኛ ድምፅ በማግኘት) አሸናፊ መሆን ችለዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር “የምርጫ ክልል 2 እና 14” የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማኅበራዊ ጉዳዮች አማካሪ የሆኑት አቶ ዳንኤል ክብረት ብርሃኔ በ4,157 ድምፅ (65% መራጮችን ድምፅ በማግኘት) አሸናፊነታቸውን አረጋግጠዋል። አቶ ዳንኤል ክብረት በ6ኛው ጠቅላላ ምርጫ በግል ዕጩነት በ“ምርጫ ክልል 28” ተወዳድረው ያሸነፉ ሲሆን፣ በወቅቱ 51,760 ድምፅ ማግኘት ችለው እንደነበር ይታወሳል።

በተቃራኒው በአፋር፣ በሶማሌ እና በኦሮሚያ ክልሎች የሚገኙ የምርጫ ክልሎች እጅግ ግዙፍ የሆነ የመራጮች ቁጥር እና የአሸናፊዎች ድምፅ የተመዘገበባቸው ሆነዋል። በዚህ ረገድ በአገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛውን ድምፅ በማግኘት ቀዳሚ የሆኑት በአፋር ክልል “አብዓላ” የምርጫ ክልል የተወዳደሩት የመከላከያ ሚኒስትሯ አይሻ መሐመድ ሙሳ ናቸው። በምርጫ ክልሉ በትክክል ድምፃቸውን ከሰጡት 560,005 መራጮች መካከል ወይዘሮ አይሻ 553,458 ድምፅ (99 በመቶ) በማግኘት ተመርጠዋል።

በተመሳሳይ፣ በሶማሌ ክልል “ፊልቱ” የምርጫ ክልል የተወዳደሩት ኢክራም መሐመድ አደን 539,524 መራጮች ባሉበት ጣቢያ ሙሉውን 539,524 ድምፅ (100 በመቶ) ያገኙ ሲሆን፤ በዚሁ ክልል “ቀብሪ በያህ” ምርጫ ክልል የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር (ኦብነግ) ተመራጭ የሆኑት አቶ አብዲቃድር አብዱላሂ በያህ 505,275 ድምፅ (93%) አግኝተዋል።

..ክልልየምርጫ ክልልየተመራ ሥምያገኙት ድምፅአጠቃላይ የመረጡ ሰዎች ቁጥርተመራ ያገኙት ድምፅ ከአጠቃላይ መራጮች በመቶኛ
1አፋርአብአላአይሻ መሀምድ ሙሣ553,458560,00599%
2ሶማሌፊልቱኢክራም መሀድ አደን539,524539,524100%
3ሶማሌቀብሪ በያህአብዲዋስ አብድላህ በዴ505,275542,11293%
4ኦሮሚያሚቻታወዚራ አህመድ ሃሚድ441,053441,053100%
5ኦሮሚያፉኛን ቢራሲራጅ አብዱላሂ ሁሴን438,557438,557100%
6አፋርዱብቲሐሰን አብዱልቃድር በርከት437,860487,84290%
7ኦሮሚያሀራዋጫአብዱረማን ኑሬ አሊሾ369,567369,567100%
8አፋርአይሳይታፋጡማ አወል ዊቲካ368,735370,142100%
9አፋርዳሊፋጌበርኦ ሀሰን በርኦ360,781378,78595%
10ሶማሌፊቅፈርዶሳ አህመድ መሐሙድ358,396358,396100%

ሰንጠረዥ 2፤ እጅግ ከፍተኛ ድምፅ ያገኙ 10 የፓርላማ ተመራጮች

ተመራጮች በአማካይ ያገኟቸው ድምፆች በክልሎች መካከልም የጎላ ልዩነት የታየበት ሲሆን፣ አፋር ክልል ተመራጮች በአማካይ 300 ሺሕ ገደማ ከፍተኛ ድምፅ ያገኙበት ክልል ሆኗል። በተቃራኒው፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ተመራጮች በአማካይ 21,866 ድምፆችን በማግኘት በምርጫ ክልሎች ዝቅተኛ ድምፆች የተገኙበት ሆኖ ተመዝግቧል።

..ክልልተመራጮች ያገኙት አማካይ ድምፅ
1አፋር302,975
2ሶማሌ204,744
3ኦሮሚያ128,991
4ድሬዳዋ123,313
5ጋምቤላ90,015
6ሲዳማ88,445
7ሃረሪ78,044
8አማራ72,469
9ማዕከላዊ ኢትዮጵያ55,268
10ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ44,082
11ደቡብ ኢትዮጵያ37,895
12አዲስ አበባ35,408
13ቤኒሻንጉል ጉሙዝ21,866

ሰንጠረዥ 3፤ በክልሎች ተመራጮች ያገኟቸው አማካይ ድምፆች

የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀፅ 54(3) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት “የሕዝብ ብዛትንና በልዩ ትኩረት ውክልና የሚሰጣቸው አናሳ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን ቁጥር መሠረት በማድረግ 550 የማይበልጥ ሆኖ ከዚህ ውስጥ አናሳ ብሔረሰቦች 20 የማያንስ መቀመጫ ይኖራቸዋል” ሲል ይደነግጋል።

በዚህ መሠረት ፓርላማው 547 መቀመጫዎች ቢኖሩትም የምርጫ ክልሎች ለመጀመሪያው ምርጫ ከተካለሉ ወዲህ የሕዝቦችን አሰፋፈር ለውጥ እና የሕዝብ ዕድገትን ከግምት ውስጥ ያስገባ ማስተካከያ አልተደረገም።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በዘንድሮው የሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በ501 የምርጫ ክልሎች ያካሄደ ሲሆን፣ የ486ቱ ውጤት በይፋ ፀድቆ፣ ቀሪዎቹ ድጋሚ ምርጫ ወይም ድጋሚ ቆጠራ እንደሚያካሂዱ መነገሩ ይታወሳል። (ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)