በትላንትናው ዕለት በተካሄደው ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ፤ እስከ ምሽቱ ሁለት ሰዓት ድረስ 40 ሚሊዮን መራጮች ድምጽ መስጠታቸውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዋና ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ ትላንት በሰጡት መግለጫ ተናገሩ። የምርጫ ቆጠራ በትላንትናው ዕለት በማይጠናቀቅባቸው ቦታዎች፤ በዛሬው ዕለት እንደሚከናወንም ዋና ሰብሳቢዋ ገልጸዋል።
ሜላትወርቅ ይህን የገለጹት ትላንት ሰኞ ግንቦት 24፤ 2018 ሲካሄድ የዋለውን ምርጫ መጠቃለል በተመለከተ ለሊት ሰባት ሰዓት ገደማ በሰጡት መግለጫ ነው። የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ በዚሁ መግለጫቸው በጸጥታ ችግር ምክንያት ምርጫ ስላልተካሄደባቸው እና ስለተቋረጠባቸው አካባቢዎች በቅድሚያ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ዋና ሰብሳቢዋ ትላንት እኩለ ቀን ገደማ በሰጡት መግለጫ በ143 የምርጫ ጣቢያዎች፤ በጸጥታ ችግር ምክንያት የድምጽ መስጠት ሂደቱ አለመካሄዱን ገልጸው ነበር። ሜላትወርቅ በዚሁ መግለጫቸው ለማሳያነት ከጠቀሷቸው መካከል በአማራ ክልል በሚገኘው የኩታ በር ምርጫ ክልል 15 ምርጫ ጣቢያዎች ላይ ድምጽ መስጠት መቻሉን አስታውቀዋል።
በዚሁ ምርጫ ክልል በሚገኙ አራት የምርጫ ጣቢያዎች ላይ ግን ምርጫ ሳይከናወን መቅረቱን ተናግረዋል። በመኮሳቺ እና ቀርሳ ምርጫ ክልል ያለው የጸጥታ ሁኔታ ባለመሻሻሉ በተመሳሳይ ሁኔታ የድምጽ መስጠት ሂደቱ አለመካሄዱን አብራርተዋል።
ትላንት ቀን በሰጡት መግለጫ የተጠቀሰው ቢሎኖፓ የተሰኘው የምርጫ ክልል በአንጻሩ በዛሬ ዕለት ምርጫ እንደሚደረግበት የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ አመልክተዋል። በቡርጂ ምርጫ ጣቢያ ያሉ የምርጫ አስፈጻሚዎች፤ በድምጽ መስጪያ ወረቀቶች ላይ ራሳቸው ምልክታ እያደረጉ ድምጽ ሲሰጡ በመገኘታቸው፤ በቦርዱ ውሳኔ መሰረት ጣቢያው እንዲዘጋ መደረጉን ተናግረዋል።
በምርጫ አስፈጻሚዎቹ ላይ ስለሚወሰደው እርምጃ ቦርዱ ተነጋግሮ ውሳኔ እንደሚያሳልፍም ሜላትወርቅ ገልጸዋል። የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ በመግለጫቸው በቀጣይነት የተመለከቱት ጉዳይ የመራጮች ቁጥር ነበር።

የምርጫ ቦርድ የዴስክ ባለሙያዎች በስልክ እና በቴክስት እስከ ትላንት ምሽቱ ሁለት ሰዓት ድረስ በሰበሰቧቸው መረጃዎች መሰረት፤ 40 ሚሊዮን መራጮች ድምጽ መስጠታቸውን ሜላትወርቅ በለሊቱ መግለጫቸው አስታውቀዋል። በኔትወርክ እና የስልክ ግንኙነት ችግር ምክንያት በአንዳንድ አካባቢዎች ያሉ የመራጮች መረጃዎችን ማካተት አለመቻላቸውንም አስረድተዋል።
በትላንትናው ዕለት ሲከናወን የቆየው ድምጽ መስጠት ሂደት በአብዛኞቹ ቦታዎች መጠናቀቃቸውን የገለጹት የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ፤ በአዲስ አበባ ከተማ ባሉ የምርጫ ጣቢያዎች ግን ከእኩለ ለሊት በኋላም የምርጫ ሂደቱ መቀጠሉን ተናግረዋል። ምርጫ ቦርድ ትላንት ማምሻውን ባወጣው መግለጫ፤ የድምጽ መስጠት ባልተጠናቀቀባቸው የምርጫ ጣቢያዎች ሂደቱ እስከ እኩለ ለሊት ድረስ እንዲቀጥል ወስኖ ነበር።
ሆኖም የተመዘገቡ መራጮች መርጠው ያጠናቀቁባቸው ቦታዎች ላይ የምርጫ አስፈጻሚዎች የድምጽ ቆጠራ ሂደቱን እንዲያከናውኑ አሳስቦ ነበር። የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ በለሊቱ መግለጫቸው የምርጫው ቆጠራ ውጤት በትላንትናው እለት መጠቃለል በሚችልባቸው ቦታዎች ተጠቃልሎ እንደሚያድር ገልጸዋል።
ዘግይቶ የምርጫ ሂደቱ በሚጠናቀቅባቸው እና ለቆጠራ የማይመች ሁኔታ ባለባቸው፤ የቆጠራ ሂደቱ በዛሬው ዕለት እንደሚካሄድ አስታውቀዋል። ቆጠራው የሚካሄደው የምርጫ አስፈጻሚዎች፣ የፓርቲ ወኪሎች እና ታዛቢዎች በሚገኙበት እንደሆነም አመልክተዋል። (ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)




