የአውሮፓ ኅብረት አገራት 7ተኛው ጠቅላላ ምርጫ “መካሄዱን” እንቀበለዋለን አሉ፤ ምርጫ ያልተካሄደባቸው የምርጫ ክልሎችም “ይህን ዕድል እንዲያገኙ” ተስፋቸውን ገልጸዋል

​ተቀማጭነታቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉ የአውሮፓ ኅብረት አባል አገራት እና ሌሎች የምዕራባውያን ዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላት፣ በትላንትናው ዕለት የተጠናቀቀውን 7ኛውን ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ አስመልክቶ የጋራ መግለጫ አውጥተዋል። አገራቱ በጋራ ባወጡት መግለጫ ኢትዮጵያ 7ተኛውን ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ ማካሄዷን “እንቀበለዋለን” ብለዋል።

መግለጫው በተጨማሪም፣ ግንቦት 24 ምርጫ ያልተካሄደባቸው. የምርጫ ክልሎችም ይህን “ዕድል እንዲያገኙ” ተስፋቸውን ገልጸዋል።

​ይህንን የጋራ መግለጫ ያወጡት የአውሮፓ ኅብረት አባል የሆኑት ኦስትሪያ፣ ቤልጂየም፣ ቡልጋሪያ፣ ቼክ ሪፐብሊክ፣ ዴንማርክ፣ ፊንላንድ፣ ጀርመን፣ ፈረንሳይ፣ ግሪክ፣ ሐንጋሪ፣ አየርላንድ፣ ጣሊያን፣ ሉክሰምበርግ፣ ማልታ፣ ኔዘርላንድስ፣ ፖላንድ፣ ፖርቱጋል፣ ሮማኒያ፣ ስሎቫኪያ፣ ስሎቬንያ፣ ስፔን እና ስዊድን ሲሆኑ፤ ከካናዳ፣ ስዊዘርላንድ እና ኖርዌይ ኤምባሲዎች ጋር በጋራ በመሆን ነው።

​አገራቱ በመግለጫቸው፣ በጸጥታና በተለያዩ ምክንያቶች ምርጫ ባልተካሄደባቸው የምርጫ ክልሎች ላይ በቀጣይ የድምፅ መስጠት ዕድል ይኖራቸዋል ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ አመልክተዋል።

በተጨማሪም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን ጨምሮ የምርጫ አስፈጻሚዎች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ዕጩዎች እና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምርጫው ስኬታማ እንዲሆን ላደረጉት ጥረት ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል።

ዲፕሎማቶቹ አክለውም፣ የአፍሪካ ኅብረት እና የምሥራቅ አፍሪካ በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) የምርጫ ታዛቢ ቡድኖች ምርጫውን በመታዘብ ለተጫወቱት ወሳኝ ሚና ዕውቅና እንደሚሰጡ እና ሪፖርታቸውን በጉጉት እንደሚጠብቁ አስታውቀዋል።

​በተመሳሳይ ዜና፣ በአዲስ አበባ የሚገኘው የእንግሊዝ ኤምባሲ በበኩሉ ባወጣው መግለጫ፤ ምርጫ ማድረግ በተቻለባቸው የሀገሪቱ አካባቢዎች 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ድምፅ የምስጠት ሂደቱ በመጠናቀቁ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፏል።

​ምርጫው በተሳካ ሁኔታ እንዲከናወን የበኩላቸውን አስተዋጽዖ ላበረከቱ አካላት እና ለተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲ ዕጩዎች አድናቆቱን የገለጸው የእንግሊዝ ኤምባሲ፣ ሂደቱን ለታዘቡት የአፍሪካ ኅብረት እና የኢጋድ የታዛቢዎች ቡድንም የላቀ ምስጋናውን አቅርቧል። (ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር) 


ማስታወሻ፤ ይህ ዜና ከቆይታ በኋላ የአውሮፓ ኅብረት የመግለጫውን የአማርኛ ቅጂ ይፋ ስላደረገ ተቀይሯል። የዘግጅት ክፍላችን “welcomes holding elections” የሚለውን በግርድፉ “ምርጫ መካሄዱን አደነቀ” ብለን የተረጎምነው ቢሆንም፣ ኅብረቱ በአማርኛ ባወጣው ትርጉም ላይ “ምርጫ መካሄዱን እንቀበላለን” በሚል ገልጾታል። በተጨማሪም “will be given the opportunity” የሚለውን “ይህ ዕድል እንደሚሰጣቸው” ብለን የተረጎምነው ቢሆንም፣ የኅብረቱ ትርጉም “እድል እንዲያገኙ” ብሎ ስላረመው ዜናውን በዚህ መሠረት አርመነዋል።