በቁጫ ምርጫ ክልል የተካሄደው 7ኛው አገራዊ ምርጫ “ተጭበርብሯል” ሲል ቁሕዴፓ አስታወቀ

ከሁለት ቀናት በፊት ግንቦት 24 ቀን በተከናወነው 7ኛው ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ ላይ በቁጫ ምርጫ ክልል የተካሄደው የድምፅ አሰጣጥ ሂደት ፍጹም ተዓማኒነት የሌለው እና “የተጭበረበረ” ነው ሲል የቁጫ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቁሕዴፓ) በጽኑ ወቀሰ።

ፓርቲው ዛሬ ረቡዕ ግንቦት 26 ቀን 2018 ዓ.ም. ረፋዱን መገናኛ አካባቢ በሚገኛው ዋና ጽሕፈት ቤቱ በሰጠው አስቸኳይ ጋዜጣዊ መግለጫ፣ በምርጫ ክልሉ መራጩ ሕዝብ የሚፈልገውን ፓርቲ በነፃነት የመምረጥ ሕገ-መንግሥታዊ መብቱ ሙሉ በሙሉ መነፈጉን አስታውቋል።

ቁሕዴፓ ለ“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” በላከው ይፋዊ መግለጫው ላይ እንዳብራራው፣ በቁጫ ምርጫ ክልል በሚገኙ ሁሉም ምርጫ ጣቢያዎች በሚባል ደረጃ የምርጫ አስፈጻሚዎች፣ የገዥው ብልፅግና ፓርቲ ታዛቢዎች፣ የቀበሌ አመራሮች እና የጸጥታ አካላት የድምፅ አሰጣጥ ሂደቱ ከተጀመረበት ሰዓት ጀምሮ ከመራጩ ሕዝብ እጅ የድምፅ መስጫ ወረቀቶችን በኃይል እየነጠቁ፣ ከሕዝብ ፍላጎት ውጭ ራሳቸው ለገዥው ፓርቲ ድምፅ ሲሰጡ ውለዋል ሲል ከሷል።

ፓርቲው በምርጫ ክልሉ ተፈጸሙ ያላቸውን ሰባት ዋና ዋና የሕግ ጥሰቶች አጠቃሎ ባቀረበበት መግለጫው፣ በድምፅ አሰጣጥ ሂደቱ ላይ ቀጥተኛ ጣልቃ በመግባት የምርጫውን ምስጢራዊነት ማደፍረስ፣ የምርጫ አስፈጻሚዎች ከመራጮች እጅ የድምፅ መስጫ ወረቀቶችን ያለፍላጎታቸው እየነጠቁ ለገዢው ብልጽግና ፓርቲ ድምፅ መስጠት፣ እንዲሁም ለቁሕዴፓ ድምፅ የሚሰጡ ዜጎችን መስደብ፣ ማንጓጠጥ እና ወረቀቱን ወደ ሳጥን እንዳይከቱ መከልከል በዋናነት ተፈጽመዋል ብሏል።

በተጨማሪም መራጮች የሰጡትን ድምፅ ገልጦ በማየት ቁሕዴፓን የመረጡ ሰዎችን ስም ዝርዝር መዝግቦ ለጸጥታ አካላት አሳልፎ መስጠት፣ በፓርቲው ደጋፊዎች ላይ አካላዊ ጥቃት እንዲፈጸም ማድረግ፣ እና በቀሪው መራጭ ላይ ቀጣይነት ያለው ዛቻና ማስፈራራት መፈጸሙን በጥፋትነት ዘርዝሯል።

ቁሕዴፓ በቁጫ አካባቢ ጠንካራ የሕዝብ መሠረት ያለው ፓርቲ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን፣ ባለፈው የ6ኛው አገራዊ ምርጫ የፓርላማ (የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት) እና የክልል ምክር ቤት ወንበሮችን በአብላጫ ድምፅ ማሸነፍ መቻሉ ይታወሳል። ይሁን እንጂ በዘንድሮው የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ዋዜማ ላይ በአካባቢው ባለሥልጣናትና የጸጥታ መዋቅሮች አማካኝነት የፓርቲው የቅስቀሳ ሂደት ከፍተኛ ዕንቅፋትና መስተጓጎል ገጥሞት እንደነበር “ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ቀደም ሲል መዘገቧ አይዘነጋም።

ቁሕዴፓ ይህ በሕገ-ወጥ መንገድ የተሰጠው የምርጫ ድምፅ “የሕዝብ እውነተኛ የምርጫ ድምፅ” ተደርጎ ሊወሰድ የሚችልበት ምንም ዓይነት ሕጋዊ አመክንዮ የለውም ብሏል። ፓርቲው የተፈጸሙት የምርጫ ሥነ-ምግባር አዋጅ ጥሰቶች ረቂቅነት ያላቸው መሆኑን ጠቅሶ, በቁጫ ምርጫ ክልል የተመዘገበው ድምፅ ፍትሐዊነትና የሕዝብ ሉዓላዊነት ይረጋገጥ ዘንድ “በጣት አሻራ ወይም በፎረንሲክ ምርመራ መረጋገጥ አለበት” ሲል በጥብቅ ጠይቋል። በመሆኑም ካርድ እና የድምፅ መስጫ ወረቀት በመንጠቅ በሕገ-ወጥ መንገድ ድምፅ የሰጡ የምርጫ አስፈጻሚዎች በሕግ እንዲጠየቁ እና የተጭበረበረው የሕዝብ ድምፅ እንዲሰረዝ የጠየቀው ፓርቲው፤ የተፈጸሙትን የአዋጅ ጥሰቶች በዝርዝር በመጥቀስ ትላንት ግንቦት 25 ቀን 2018 ዓ.ም. ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የክስ አቤቱታውን በጽሑፍ ማስገባቱን አረጋግጧል። (ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)