ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም. የተከናወነውን 7ኛውን ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ አስመልክቶ፣ የኢትዮጵያ የሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች ኅብረት ለምርጫ (ኅብረት ለምርጫ) ዛሬ ረቡዕ ግንቦት 26 ቀን 2018 ዓ.ም. ባወጣው የመጀመሪያ ደረጃ የትዝብት ሪፖርት፤ በድምፅ አሰጣጥ እና በቆጠራ ሂደት ላይ በርካታ የአሠራር ክፍተቶች፣ የምስጢራዊነት ጥሰቶች እንዲሁም የሕግ ግድፈቶች ማጋጠማቸውን አስታውቋል።
ኅብረቱ ይፋ ባደረገው በዚህ ዝርዝር መረጃ መሠረት፣ መራጮች ስማቸው በባህረ-መዝገብ ላይ ሳይገኝ ድምፅ እንዲሰጡ ከመፍቀድ ጀምሮ በምስጢር የመምረጥ መብት ጥሰት እና በአስፈጻሚዎች ጣልቃ ገብነት ዙሪያ የጎሉ ግኝቶች ተመዝግበዋል።
ኅብረቱ ባወጣው የምርጫ ትዝብት ጊዜያዊ ሪፖርት መሠረት፣ በ130 የምርጫ ጣቢያዎች ላይ የመራጮች መዝገብ ላይ ስማቸው ያልተገኘ እና የመራጭነት ካርድ ያልያዙ፣ በእያንዳንዱ ጣቢያ ከአንድ እስከ 10 የሚሆኑ መራጮች ሕገ-ወጥ በሆነ መንገድ ድምፅ እንዲሰጡ ተደርጓል።
በተመሳሳይ ሁኔታ በሌሎች 8 የድምፅ መስጫ ጣቢያዎች ደግሞ ከ10 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ስማቸው በመራጮች መዝገብ ላይ ሳይሰፍር እና የመራጭነት ካርድ ሳይዙ እንዲመርጡ መፈቀዱ ተረጋግጧል።
በአንጻሩ፣ ኅብረቱ ከታዘባቸው 2,506 የምርጫ ጣቢያዎች መካከል በ2,458ቱ ላይ ስማቸው በመራጮች መዝገብ ላይ ሰፍሮ ድምፅ መስጠት የተከለከለ ሰው እንዳልነበረ የጠቀሰ ቢሆንም፤ በ46 የድምፅ መስጫ ጣቢያዎች ግን ከ1 እስከ 10 የሚሆኑ ሕጋዊ መራጮች ስማቸው በመራጮች መዝገብ ላይ እያለ ድምፅ እንዳይሰጡ መከልከላቸውን ይፋ አድርጓል።
በሌሎች 2 የድምፅ መስጫ ጣቢያዎች ደግሞ ከ10 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ስማቸው በመራጮች መዝገብ ላይ ሰፍሮ እያለ ድምፅ መስጠት መከልከላቸውን የኅብረቱ ሪፖርት ያስረዳል።
የኅብረቱ ባለሙያዎች ከታዘቧቸው 2,506 የምርጫ ጣቢያዎች ውስጥ በ93 በመቶዎቹ ላይ የድምፅ አሰጣጥ ምስጢራዊነት ሳይጣስ የተጠበቀ ቢሆንም፣ በ161 የምርጫ ጣቢያዎች ግን እስከ 10 እና ከዚያ በላይ በሚሆኑ መራጮች ላይ የድምፅ አሰጣጥ ምስጢራዊነት መጣሱ ታውቋል።
ኅብረቱ በሪፖርቱ ላይ እንደገለጸው፤ የምስጢራዊነት ጥሰት ተብለው የተመዘገቡት ድርጊቶች መራጮችን ተከትሎ ወደ ምስጢራዊ ድምፅ መስጫ ክፍል መግባት ወይም መራጩ ምልክት ያደረገበትን ወረቀት ለማየት መጠየቅ እና የመሳሰሉትን ሕገ-ወጥ ድርጊቶች የሚያካትት ነው።
ከዚህ በተጨማሪም፣ በ19 የምርጫ ጣቢያዎች ላይ የምርጫ አስፈጻሚዎች ራሳቸው ለመራጮች መመሪያ በሚሰጡበት ወቅት ለአንድ የተወሰነ ፓርቲ ወይም ዕጩ ድምፅ እንዲሰጡ ቀጥተኛ “ምክር” ሲለግሱ ታዝበዋል። በአሠራር ረገድም በ87 የምርጫ ጣቢያዎች ከአንድ እስከ 10 መራጮች፣ እንዲሁም በ6 ጣቢያዎች ደግሞ ከ10 በላይ መራጮች ጣታቸው ላይ የማይለቅ ቀለም ሳይቀቡ ድምፅ እንዲሰጡ ተፈቅዶላቸዋል። በሌላ በኩል በ64 የምርጫ ጣቢያዎች ላይ እስከ 10 እና ከዚያ በላይ የሚሆኑ የድምፅ መስጫ ወረቀቶች በሕግ መሠረት ማኅተም ሳይደረግባቸው ለመራጮች መታደላቸውን ሪፖርቱ ያሳያል።
የድምፅ መስጫው ዕለት አካላዊ ድጋፍ ለሚፈልጉ ዜጎች ሁኔታዎችን ከመመቻቸት አንጻር፣ ኅብረቱ ከታዘባቸው ጣቢያዎች ውስጥ 91 በመቶዎቹ ለአረጋውያን፣ ለአካል ጉዳተኞች እንዲሁም ማንበብና መጻፍ ለማይችሉ መራጮች በራሳቸው ምርጫ በረዳት እንዲታገዙ ፈቅደዋል።
በተቃራኒው ግን 32 የምርጫ ጣቢያዎች ድጋፍ ለሚፈልጉ መራጮች በራሳቸው ምርጫ በረዳት እንዲታገዙ ፍቃድ ሳይሰጡ ቀርተዋል። አጠቃላይ የድምፅ መስጠት ሂደትን በተመለከተም ኅብረቱ ከታዘባቸው ጣቢያዎች መካከል በ40ዎቹ ላይ ሂደት ተቋርጦ እንደነበር ተመልክቷል።
የድምፅ መስጫ ጣቢያዎችን መዝጊያ ሰዓት በተመለከተ በነበረው አፈጻጸም፤ 313 የምርጫ ጣቢያዎች ከምሽቱ 12:00 ሰዓት በፊት ሲዘጉ፣ 1,848 የምርጫ ጣቢያዎች ደግሞ ከምሽቱ 12:00 እስከ ምሽቱ 1:00 ሰዓት ባለው ጊዜ ውስጥ ተዘግተዋል። በአንጻሩ እጅግ ረጅም ሰልፍ በመኖሩ ምክንያት 241 የምርጫ ጣቢያዎች ከምሽቱ 3:00 ሰዓት በኋላ ለመዘጋት ተገድደዋል።
በመዝጊያ ሰዓቱ ላይ በ780 የምርጫ ጣቢያዎች ላይ ምንም ዓይነት ሰልፍ ወይም ሰው እንዳልነበረ የተገለጸ ሲሆን፣ በ1,715 ድምፅ መስጫ ጣቢያዎች ላይ ደግሞ በሰልፍ ላይ የነበሩ ሰዎች በሙሉ ድምፅ መስጠት ችለዋል። ሆኖም ግን በ11 የምርጫ ጣቢያዎች ላይ በሰልፍ ላይ ከነበሩት መራጮች መካከል ጥቂቶቹ ወይም ሁሉም ድምፅ ሳይሰጡ ሂደቱ መዘጋቱ ተረጋግጧል።
በመጨረሻም፣ ኅብረቱ ከታዘባቸው የምርጫ ጣቢያዎች ውስጥ በ98 በመቶዎቹ ላይ ታዛቢዎች በተገኙበት የድምፅ ቆጠራው በጣቢያው ውስጥ የተከናወነ ቢሆንም፣ በ59 የምርጫ ጣቢያዎች ግን የድምፅ ቆጠራው በድምፅ መስጫው ዕለት ወይም ድምፅ በተሰጠበት ጣቢያ እንዳልተከናወነ ሪፖርቱ ያሳያል።
በድምፅ ቆጠራ ወቅት በ12 የምርጫ ጣቢያዎች ላይ ግልጽ የሆነ ማስፈራራት ወይም የውጭ አካላት ጣልቃ ገብነት የነበረ ሲሆን፣ በ26 ጣቢያዎች ደግሞ ቆጠራው ድምፅ በተሰጠበት ጣቢያ አለመከናወኑ ተገልጿል።
ከዚህ በተጨማሪም በ65 የምርጫ ጣቢያዎች የድምፅ መስጫ ወረቀቶች ላይ መራጮች ያደረጉት ምልክት በግልጽ ሳይታይ (ሳይታይና ሳይታደል) መቆጠሩን፣ በ77 የምርጫ ጣቢያዎች ደግሞ የምርጫ አስፈጻሚዎች ራሳቸው በድምፅ መስጫ ወረቀቶች ላይ ምልክት ማድረጋቸውን ኅብረቱ በጥፋትነት መዝግቧል። የቆጠራው ማጠቃለያ ተደራሽነትን በተመለከተም፣ 40 የምርጫ ጣቢያዎች የድምፅ መስጫ ጣቢያውን ይፋዊ የውጤት መግለጫ እና ማመሳከሪያ ቅጽ ቅጂ ለሕዝብ እይታ እንዲታይ በምርጫ ጣቢያው በር ላይ ሳይለጥፉ መቅረታቸውን ኅብረት ለምርጫ በጊዜያዊ ሪፖርቱ አጋልጧል። (ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)




