ከሁለት ቀናት በፊት ግንቦት 24 ቀን የተከናወነውን 7ኛውን ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ አስመልክቶ፣ የአፍሪካ ኅብረት (AU) እና የምሥራቅ አፍሪካ በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) የታዛቢዎች ቡድን ዛሬ ግንቦት 26 ቀን 2018 ዓ.ም. የጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል። መግለጫውን በጋራ የሰጡት የአፍሪካ ኅብረት ታዛቢ ቡድን መሪ የቀድሞው የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ እና የኢጋድ ታዛቢ ቡድንን የሚመሩት የቀድሞዋ የኡጋንዳ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ስፔሺዮሳ ዋንዲራ ካዚብዌ ናቸው።
ሁለቱ ዓለም አቀፍ የታዛቢ ቡድኖች ክፍተቶች ቢኖሩም በአጠቃላይ ምርጫው የኢትዮጵያውያንን የዴሞክራሲ ቁርጠኝነት ያሳየ አዲስ ምዕራፍ እና ስኬታማና ሰላማዊ ሂደት እንደነበር የገለጹ ቢሆንም, የምርጫ ጣቢያዎች ጥበትን እና በጸጥታ ስጋት ምክንያት የተፈጠረውን የአካታችነት ጉድለት በዋናነት አንስተዋል።
የአፍሪካ ኅብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን ባወጣው መግለጫ፣ ምርጫው በጥሩ ሁኔታ መጀመሩን፣ ዜጎች ድምፅ እንዲሰጡ ማስቻሉን እንዲሁም የምርጫ ወረቀቶችና ሳጥኖች በተገቢው መንገድ መዘጋጀታቸውን በጥሩ ጎን አንስቷል። በዕለቱ የታዩትን ረጃጅም ሰልፎች ተከትሎ የድምፅ መስጫ ሰዓት መራዘሙ መራጮች ዕድል እንዲያገኙ ማድረጉን ያደነቀው ቡድኑ፤ ይሁን እንጂ በትግራይ ክልል ሙሉ በሙሉ እና በአማራ ክልል በከፊል ምርጫ አለመካሄዱ በሂደቱ አካታችነት ላይ ክፍተት መፍጠሩን ጠቁሟል።
ከዚህ በተጨማሪም ኅብረቱ በተለየ ሁኔታ ባነሳው ስጋት፣ ታዛቢ ቡድኑ በተገኘባቸው የተወሰኑ የምርጫ ጣቢያዎች ላይ ከፍተኛ የቦታ ጥበት መስተዋሉን ገልጿል። በዚህ የቦታ ጥበት ምክንያት መራጮች፣ አስመራጮች (የምርጫ አስፈጻሚዎች)፣ ታዛቢዎች እና የፖለቲካ ፓርቲ ወኪሎች እርስ በርስ ተጠጋግተው ለመቀመጥ መገደዳቸውንና ይህም ለሂደቱ ምቾት ክፍተት መፍጠሩን በጥናት መታዘቡን ይፋ አድርጓል።
በሌላ በኩል የኢጋድ ታዛቢ ቡድን መሪ ባቀረቡት ሪፖርት መሠረት፣ ተቋሙ 26 ታዛቢዎችን በማሰማራት በ7 ክልሎች እና በሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች ላይ የቅርብ ክትትል አድርጓል። የኢጋድ የምርጫ ታዛቢዎች ስምሪት በወሰዱባቸው በኦሮሚያ፣ አማራ፣ ሲዳማ እና ሶማሌ ክልሎች እንዲሁም በድሬዳዋ እና አዲስ አበባ ከተሞች በሚገኙ በየጣቢያዎቹ በቂ የምርጫ ማስፈጸሚያ ቁሳቁሶች ተሟልተው የነበረ ከመሆኑም በላይ የድምፅ አሰጣጥ ሂደቱ ፍጹም ግልጽ እንደነበር ተመልክቷል።
በዚህ ምርጫ ላይ ከ54 ሚሊዮን በላይ መራጮች የተመዘገቡ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ 46 በመቶ ሴቶች እና 54 በመቶ ወንዶች መሆናቸውን የጠቀሰው ቡድኑ፣ ከ10 ሺህ በላይ ዕጩዎች በተሳተፉበት በዚህ ሂደት የመራጮች ምዝገባ በዲጂታል መንገድ መከናወኑን፣ የመራጮች ትምህርት በጥሩ መልኩ መሰጠቱን እና ለፓርቲዎች የሚዲያ ተደራሽነት መኖሩን በበጎ ጎን ዘርዝሯል።
የኢጋድ ታዛቢ ቡድንም እንደ አፍሪካ ኅብረት ሁሉ ሂደቱ በሰዓቱ መጀመሩንና ሳጥኖች በትክክል መታሸጋቸውን ያረጋገጠ ቢሆንም፣ በአንጻሩ ረጃጅም ሰልፎች መታየታቸውንና በትግራይና በከፊል አማራ ክልል ምርጫ አለመካሄዱን እንደ ዋና ችግር አስፍሯል።
ሁለቱም የታዛቢ ቡድን መሪዎች በምርጫው ዕለት የጸጥታ ኃይሎች ያሳዩትን ብቃት ያደነቁ ሲሆን፤ የጸጥታ አካላት የተሰጣቸውን ሕዝባዊ አደራ በአግባቡ በመወጣት ለምርጫው ሂደት ሰላማዊነት ከፍተኛ እና በጎ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ገልጸዋል። በሂደቱ ላይ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የተጣለባቸውን ኃላፊነት መወጣታቸው፣ ኢትዮጵያውያን ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ያላቸውን ቁርጠኝነት በተግባር ያሳዩበት ስኬታማ እርምጃ መሆኑን አረጋግጠዋል።
በመጨረሻም ሁለቱ ዓለም አቀፍ የታዛቢዎች ቡድኖች ለቀጣይ የምርጫ ሂደቶች የሚሆኑ በርካታ የጋራ ምክረ ሐሳቦችን ሰንዝረዋል። እንደአብነትም፣ የዲጂታል ቴክኖሎጂ አጠቃቀም እና የዲጂታል መሠረተ ልማት ይበልጥ እንዲጠናከር፣ የሴት ዕጩዎች ቁጥር እንዲበራከት፣ የወጣቶች ተሳትፎ እንዲያድግ እና መንግሥት አካታች የፖለቲካ ምኅዳር በመፍጠር አገራዊ ምክክሩን እንዲያጠናክር መክረዋል።
በተጨማሪም፣ በቦታ ጥበት የተነሳ የታዩትን ክፍተቶች ለመቅረፍ የምርጫ ጣቢያዎች በስፋትና ምቹ በሆነ ሁኔታ እንዲዘጋጁ፣ የጸጥታ አካላት ገለልተኝነታቸውን እንዲያስቀጥሉ፣ ከምርጫ ጋር የተያያዙ ግጭቶች እንዳይከሰቱ አስቀድሞ መከላከል እንዲቻል፣ እንዲሁም ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ሂደቱን ለመቆጣጠር የራሳቸውን ታዛቢዎች በስፋት እንዲልኩ ጥሪ አቅርበዋል። (ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)




