የምርጫው ይፋዊ ውጤት ከሚታወጅበት ሁለት ቀን አስቀድሞ ልዩ የምርጫ መርሐ-ግብር እንደሚኖር ቦርዱ አስታወቀ

ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ባለፈው ሰኞ ተካሄዶ መጠናቀቁ ቢገለጽም፤ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች እና የመከላከያ ሰራዊት አባላት ግን ድምጻቸውን የሚሰጡት ገና በሚቀጥለው ሳምንት እንደሆነ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ገልጿል። ቦርዱ የምርጫውን የመጨረሻ ይፋዊ ውጤት ይገልጻል ተብሎ ከሚጠበቅበት ከሰኔ 4 ቀን ሁለት ቀናት አስቀድሞ፣ ማለትም ሰኔ 2 ቀን 2018 ዓ.ም. ልዩ የምርጫ መርሐ-ግብር ማዘጋጀቱን የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ ትላንት፣ ግንቦት 26፣ 2018 ተናግረዋል።

ተፈናቃዮች እና የመከላከያ ሰራዊት አባላት የመራጮች ምዝገባ በተካሄደበት ወቅትም፤ ከመደበኛው የጊዜ ሰሌዳ በተለየ መልኩ እንዲመዘገቡ ነበር የተደረገው። ከየካቲት 28 ጀምሮ ለአንድ ወር ሲካሄድ የቆየው መደበኛው የመራጮች ምዝገባ እስከ ሚያዝያ 14 ተራዝሞ መጠናቀቁ የሚታወስ ነው።

በአንጻሩ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች፣ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች እና በወታደራዊ የጦር ሰፈር ውስጥ የሚገኙ የመከላከያ ሰራዊት አባላት መራጮች ምዝገባ የተካሄደው ከሚያዝያ 18 እስከ ሚያዝያ 24 ባለው አንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ነበር። “በልዩ ሁኔታ” በተካሄደው በዚህ ምዝገባ 28,632 ተፈናቃዮች እና 126,498 የመከላከያ ሰራዊት አባላት መመዝገባቸውን ምርጫ ቦርድ ማስታወቁ አይዘነጋም።

ቦርዱ እነዚህ መራጮች ድምጽ እንዲሰጡ ያቀደው ከአምስት ቀናት በኋላ በመጪው ማክሰኞ መሆኑን የተቋሙ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል። ተፈናቃዮች ባሉባቸው ቦታዎች እና በወታደራዊ ካምፕ የሚደረጉ ምርጫዎች “በፍጥነት ተጠቃልለው መቅረብ የሚችሉ ውጤቶች” መሆናቸውንም አመልክተዋል።

“በተቻለ መጠን ቦርዱ ያለበትን የተጨናነቀ እና የተጣበበ ጊዜ አይቶ ወደ ኋላ የሚቀሩ ውጤቶች ካሉ፣ ህጉም እንደሚፈቅደው ከአቅም በላይ የሆነ ነገር በሚገጥም ጊዜ፣ ድምጽን በይፋ የማሳወቅ ስራ እስከ 20 ቀን ሊራዘም ስለሚችል፣ በዚያ ዕድል ተጠቅሞ አብሮ አጠቃልሎ የሚያመጣው ይሆናል” ሲሉ ሜላትወርቅ የእነዚህ መራጮች ውጤት መቼ ሊታወቅ እንደሚችል አብራርተዋል። በምርጫ ቦርድ የምርጫ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት፤ ይፋዊ የምርጫ ውጤት በማዕከል ደረጃ የሚገለጸው ሰኔ 4፤ 2018 ነው።

በሌላ በኩል በምርጫ ክልል ደረጃ ባሉት አምስት ቀናት ውስጥ የምርጫ ውጤት ተደምሮ እንደሚለጠፍ የገለጸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፤ እንደ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ባሉ የተወሰኑ ክልሎች ላይ ግን በድምፅ ቆጠራ ወቅት የሰው ኃይል እጥረት እያጋጠመው መሆኑን አስታውቋል።

የቦርዱ ሰብሳቢ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በርካታ የምርጫ አስፈጻሚዎች የምርጫ ውጤት የማዳመር (የማጠቃለል) ሥራ እየሠሩ ቢሆንም፣ የሰው እጥረት በመኖሩ ምክንያት ተጨማሪ የሰው ኃይል በመመደብ ሂደቱን ለማፋጠን ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

የምርጫውን ይፋዊ ውጤት ማሳወቅ የሚችለው ሕጋዊ ሥልጣን ያለው ቦርዱ ብቻ መሆኑን ያረጋገጡት ዋና ሰብሳቢዋ፤ ከአንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች እየቀረቡ ስላሉት የምርጫ ማጭበርበር ጥያቄዎችና አቤቱታዎች ዙሪያም ምላሽ ሰጥተዋል።

በቁጫ ምርጫ ክልል የተካሄደው 7ኛው አገራዊ ምርጫ “ተጭበርብሯል” ሲል የቁጫ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቁሕዴፓ) ከትላንት በስቲያ ግንቦት 25 ቀን 2018 ዓ.ም. ለቦርዱ በጽሑፍ ያስገባውን እና ትላንት ግንቦት 26 ቀን ይፋ ያደረገውን የቅሬታ መግለጫ አስመልክቶ ለሰብሳቢዋ ከጋዜጠኞች ጥያቄ ቀርቦላቸዋል።

ቁሕዴፓ በመግለጫው፤ የምርጫ አስፈጻሚዎች፣ የቀበሌ አመራሮችና የጸጥታ አካላት መራጩን ሕዝብ በማስገደድ የድምፅ መስጫ ወረቀት እየነጠቁ ራሳቸው ለገዢው ብልጽግና ፓርቲ ድምፅ ሰጥተዋል ሲል መክሰሱ ይታወሳል።

ይህንን አስመልክቶ ሰብሳቢዋ ሜላትወርቅ ኃይሉ በሰጡት ምላሽ፤ “ቁሕዴፓ ምርጫው ተጭበርብሯል በሚል ያወጣውን መግለጫ ተመልክተናል፤ አቤቱታውም ለቦርዱ በጽሑፍ ደርሷል” ያሉ ሲሆን፣ የቦርዱ የሕግ ክፍል በአቤቱታው ላይ አስፈላጊውን ክትትል በማድረግ በጉዳዩ ላይ በጥብቅ እየሠራበት መሆኑን አስታውቀዋል።

በሌላ በኩል፣ ነፃነት እና እኩልነት ፓርቲ (ነእፓ) በአማራ ክልል በተወሰኑ አካባቢዎች “የምርጫ ማጭበርበር ተግባራት ተፈጽመዋል” በሚል በነዚህ ሥፍራዎች ላይ ምርጫው እንዲደገም ለሚዲያ ጥያቄ ማቅረቡ ይታወሳል። ፓርቲው ግንቦት 24 ቀን በተካሄደው 7ኛው ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ በደቡብ ወሎ (በለጋምቦ፣ ለገሂዳ፣ ከለላ እና ደብረሲና) እንዲሁም በደሴ እና በባሕር ዳር ከተሞች የምርጫ ድምፅ አሰጣጥ ሂደት ላይ በርካታ ሕገ-ወጥ ድርጊቶች መታዘባቸውን ገልጾ ነበር።

ይሁን እንጂ የቦርዱ ሰብሳቢ ይህንን የነእፓን ክስ ውድቅ ያደረጉት ሲሆን፤ “ነፃነት እና እኩልነት ፓርቲ ያቀረበውን የምርጫ ማጭበርበር እና የድጋሚ ምርጫ ጥያቄ በተመለከተ እስካሁን ወደ ቦርዱ በይፋ የቀረበም ሆነ የደረሰ የጽሑፍ አቤቱታ የለም” ሲሉ ገልጸዋል። (ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)