የተፈናቀሉበት አካባቢ ያሉ ዕጩዎችን ለመምረጥ እንደተገደዱ የደብረ ብርሃን ተፈናቃዮች ገለጹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በአገር ውስጥ ተፈናቃዮች (IDPs) እና በሚሊተሪ ካምፖች ውስጥ በመጪው ሰኔ 2 ቀን 2018 ዓ.ም. ልዩ የምርጫ ድምፅ አሰጣጥ እንደሚካሄድ በገለጸ ማግስት፣ በደብረ ብርሃን መጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ ተፈናቃዮች በሂደቱ ላይ ያላቸውን ጠንካራ ተቃውሞና ምሬት ለ “ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል።

ከኦሮሚያ ክልል ተፈናቅለው በደብረ ብርሃን ከተማ በሚገኙ መጠለያዎች ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች፣ “እዚህ ተመዝግበን ሳለ ‘የተፈናቀላችሁበት ቦታ የሚገኘውን ዕጩ ነው የምትመርጡት’ መባላችን እጅግ አሳዝኖናል” ያሉ ሲሆን፣ ውሳኔው በኅብረተሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ቁጣና ጥርጣሬን ፈጥሯል።

ተፈናቃዮቹ የምርጫ ካርድ መውሰዳቸውን ቢያረጋግጡም፣ እስከ አሁን በመጠለያ ካምፖቹ ውስጥ ምንም ዓይነት የምርጫ እንቅስቃሴ፣ የዕጩዎች ማስተዋወቂያ ወይም የፖለቲካ ፓርቲዎች የቅስቀሳ ሂደት አለመኖሩንም ተፈናቃዮቹ ጨምረው ገልጸዋል።

“ቻይና ካምፕ” በሚባለው መጠለያ ጣቢያ የሚገኙና ከኦሮሚያ ክልል የተፈናቀሉ አንድ ግለሰብ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” በሰጡት ቃል፣ “ኅብረተሰቡ ካርድ እንዲወስድ ተደርጓል፤ ነገር ግን ምንም ዓይነት የምርጫ ዝግጅት የለም። ሁሉ ነገር ከተጠናቀቀ በኋላ አስመራጮች ከተፈናቃዮች መካከል ተመርጠው ነው ምዝገባው የተካሄደው” ብለዋል።

ምርጫ ቦርድ ለሂደቱ ያደረገው ምንም ዓይነት እገዛ የለም ያሉት እኚሁ ተፈናቃይ፣ ሁሉንም ቅድመ ዝግጅቶች ያሰናዳው ተፈናቃዩ ማኅበረሰብ ራሱ መሆኑን ጠቁመው፣ ከተፈናቃይ ካምፕ ውስጥ እየወጡ ወደ ከተማ በመሄድ የምርጫ ካርድ የወሰዱና የተመዘገቡ መኖራቸውንም መታዘባቸውን አክለዋል።

እኚሁ የቻይና ካምፕ ተፈናቃይ ቦርዱ ያስተላለፈውን መመሪያ ፍጹም አግባብነት የሌለው መሆኑን ሲያብራሩም፣ “የምርጫ ሂደት ሀገረ መንግሥት ግንባታ እስከሆነ ድረስ፣ እዚሁ ባለንበት ቦታ ያለ ፓርቲ እና ዕጩ መመረጥ ይሻለናል። የመጣንበት ቦታ የማናውቀውን ዕጩ ከምንመርጥ እዚሁ የምናውቀውን ሰው ብንመርጥ ጥሩ ነበር፤ እዚህ ከመጣን እኮ አምስት ዓመት ሞላን” ብለዋል።

ግለሰቡ አክለውም፤ “ተፈናቅለን የመጣንበት አካባቢ ጊዜያዊ የምርጫ ውጤት ቀድሞውኑ ይፋ ተደርጓል። ድምፅ ተቆጥሮ ውጤት ከተለጠፈ በኋላ አሁን የእኛ መምረጥ ነጥቡ ምንድነው? እኛ አምስት ዓመት በቆየንበት በደብረ ብርሃን አካባቢ መርጠው ውጤት ይፋ እያደረጉ ባለበት ወቅት የእኛ መምረጥ ትርጉሙ አልገባንም” ሲሉ ውሳኔውን ተቃውመዋል።

የምርጫ ሕጉ 1162/2011 በአንቀፅ 17 በልዩ ሁኔታ ስለሚቋቋሙ የምርጫ ጣቢያዎች ሲደነግግ “… ድምፅ የሚሰጡበትን ቦታ፣ ድምጻቸው የሚቆጠርበትን የምርጫ ክልል እንዲሁም ተያያዥነት ያላቸውን ጉዳዮች ቦርዱ በሚያወጣው መመሪያ ይወስናል” ይላል። በዚሁ መሠረት የወጣው “በልዩ ሁኔታ የሚቋቋሙ የምርጫ ጣቢያዎች መመሪያ ቁጥር 13/2013”፣ በአንቀፅ 13/ሠ ልዩ የምርጫ ጣቢያው የተቋቋመለት ተቋም “በሚገኝበት የምርጫ ክልል መደበኛ ነዋሪ የሆነ መራጭ በመደበኛ የምርጫ ጣቢያ መመዝገብ ስለሚችል በልዩ ምርጫ ጣቢያ መመዝገብ የለበትም” ይላል። መመሪያው መደበኛ መኖሪያ ማለት “ተፈናቃዮች ከመፈናቀላቸው በፊት በቋሚነት ይኖሩበት የነበረበት ቦታ ነው” ይላል።

የሰሜን ሸዋ ዞን የምርጫ ቦርድ ተወካይ ይህንን “የመጣችሁበትን አካባቢ ዕጩዎች ምረጡ” የሚል መመሪያ እንዳስተላለፈላቸው የጠቀሱት ከላይ የጠቀስናቸው የቻይና ካምፑ ተፈናቃይ፣ “የምንመርጠው ሰው እኛ የተፈናቀልንበትን ችግር የሚፈታ ነው ወይስ አይደለም የሚለውን ለማወቅ እንኳን ቅስቀሳም ሆነ የመራጮች ትምህርት የሰጠን አካል የለም። ተቃዋሚ ይሁን የመንግሥት ፓርቲ፣ ወይም እዚያ የተፈናቀልንበት ቦታ ማን ዕጩ እንደሆነ የምናውቀው ነገር የለም” ሲሉ ሁኔታውን አስረድተዋል።

በተመሳሳይ ሁኔታ በ“ባቄሎ መጠለያ ካምፕ” ውስጥ የሚኖሩ ሌላ ተፈናቃይም በመጠለያው ውስጥ ምንም ዓይነት የምርጫ እንቅስቃሴ አለመኖሩንና ማንን እንደሚመርጡ የተሰጣቸው ማብራሪያ ባለመኖሩ የተነሳ በካምፑ የተመዘገበው የመራጭ ቁጥር እጅግ አነስተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

በ“ወይንሸት መጠለያ ጣቢያ” የሚገኙና የምርጫ ካርድ የወሰዱ ሌላ ተፈናቃይ በበኩላቸው፤ “ከተፈናቀልን ቢያንስ አምስት ዓመት አልፎናል፤ ታዲያ አንድም ጊዜ ‘የት ወደቃችሁ?’ ያላለንን አካባቢ ዕጩ ለምን እንድንመርጥ እንደታሰበ አልገባንም” ሲሉ በምሬት ተናግረዋል።

“ቢያንስ ምርጫ ከታሰበ እዚሁ ሲያገለግሉን ባሉት አመራሮች ብንተዳደር መልካም ነበር። እዚህ ያለውም ቢሆን የምናውቀውን በሚል እንጂ፣ አምስት ዓመት ተዘግቶብን ተቀምጠናል፤ ማንም ይሁን ማን ለኛ ችግር ለውጥ አያመጣም” ብለዋል።

በዚሁ መጠለያ የምትገኝ ሌላ ተፈናቃይ ደግሞ፣ “ማንን እንደምንመርጥ የተገለጸልን ነገር የለም። ካርድ ውሰዱ ተባለ፣ ኅብረተሰቡ ካርድ ወስዷል፤ አድርግ የተባለውን ብቻ ነው የሚያደርገው” ካሉ በኋላ፣ የመጣችሁበትን ቦታ ትመርጣላችሁ መባሉን በጽኑ አውግዘዋል። “እንዴት ቢታሰብ ነው ሕዝቡ እዚህ መርጦ እዛ የሚቆጠረው? የምንመርጠው ሰው ማን እንደሆነ ሳይታወቅ ያፈናቀለንም ሊሆን ይችላል” ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።

በወይንሸት መጠለያ ካምፕ የሚገኙ አስተባባሪ ለ“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” እንደገለጹት፣ “እዚሁ አካባቢ ያለውን አስተዳደር ምረጡ ብንባል ችግር አልነበረውም፤ ነገር ግን ‘እንዴት ገዳዮቻችንን ምረጡ እንባላለን?’ የሚል እጅግ የበረታ ቅሬታና ተቃውሞ በሕብረተሰቡ ዘንድ ሰፍኗል” ብለዋል።

አስተባባሪው አክለውም፣ “በአካባቢው ያለው የጸጥታ ሁኔታ መጋዘን ውስጥ ተጠቅጥቀው እንዲመዘገቡ ከማድረጉ ባለፈ በሰባት መጠለያ ካምፖች ውስጥ ከ700 የማይበልጥ ሰው ብቻ እንዲመዘገብ አድርጓል፤ ይህ በእያንዳንዱ ካምፕ 700 ሰው ይመዘገባል ተብሎ ከነበረው ዕቅድ እጅግ ያነሰ ነው” በማለት ተሳትፎውም ዝቅተኛ መሆኑን ጠቅሰዋል።

“በወይንሸት መጠለያ ካምፕ ውስጥ 11 ሺህ የሚሆኑ ተፈናቃዮች መኖራቸውን እና በምርጫው ምዝገባ ወቅት ግን በዚህ መጠለያ 112 ሰዎች ብቻ ናቸው የተመዘገቡት” ያሉት አስተባባሪው፣ ለምዝገባ የተሰጠው ጊዜ ማጠሩ እና የምርጫ ጣቢያዎች አለመቋቋማቸው ሂደቱ ትኩረት እንዳልተሰጠው ማሳያ ነው ብለዋል።

“ድንኳኖች ይዘን እንመጣለን የሚል መረጃ ሰጥተውን የነበረ ቢሆንም፣ አንድ ተወካይ ይመጣ ነበር እሱም እገዛ እያደረገልን አይደለም። ምርጫው መቼ እንደሚደረግም የተገለጸልን ነገር የለም፤ ከመደበኛው ምርጫ ጋር አንድ ላይ ይሆናል ብለን ጠብቀን ነበር ግን አልሆነም” ሲሉ አስተባባሪው የዘገባውን ማጠቃለያ ሰጥተዋል።

በጉዳዩ ላይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምላሽ ሲስጥ፣ ተከታትለን ለአንባቢዎቻችን እናቀርባለን። (ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)