ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት የጥምረቱ የምርጫ ጉዳዮች ኃላፊ ሰጥተውታል የተባለውን መግለጫ “በተግባርም በአስተዋፅዖም የማናውቀው ግለሰብ” መግለጫ ነው ሲል አስተባበለ

ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት (ትብብር) የተሰኘው የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥምረት ዛሬ አርብ ግንቦት 28 ቀን 2018 ዓ.ም. በማኅበራዊ ድረገጹ ባወጣው መግለጫ, “በትብብሩ ስም የተሰጠ እና የድርጅቱን ይፋዊ አቋም የማይወክል፣ እንዲያውም ከተቋቋምንበት ዓላማ በተፃራሪ የቆመ መግለጫ በሚዲያ ተሰራጭቷል” ሲል አስታውቋል።

ጥምረቱ ይህንን ማብራሪያ የሰጠው፣ በትላንትናው ዕለት ግንቦት 27 ቀን 2018 ዓ.ም. ከትብብሩ መሥራች ፓርቲዎች አንዱ የሆነው የአማራ ጊዮናዊ ንቅናቄ ፕሬዚዳንት የሆኑት እና በትብብሩ ውስጥ “የምርጫ ጉዳዮች ኃላፊ” መሆናቸው የተጠቀሱት አቶ ምርጫው ስንሻው ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን የሰጡትን መግለጫ ተከትሎ ነው።

አቶ ምርጫው ከፋና ሚዲያ ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ “7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሕዝቡ ትልቅነቱን፣ ሰላም ወዳድነቱንና አሸናፊነቱን ያረጋገጠበት ነው” ማለታቸው የሚታወስ ሲሆን፣ ሰላማዊ ሽግግር እንዲኖር ትብብሩ ጥረት ማድረጉንና “በምርጫው በሰላም የምንታገል ኃይሎች መሆናችንን ለዓለም ማሳየት ችለናል” ሲሉ ምልከታቸውን ሰጥተው ነበር።

ይህንን አስተያየት በጥብቅ የተቃወመውና ዛሬ አጠር ያለ መግለጫ ያወጣው ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት፣ “ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ እንዲሉ፣ በትብብሩ ስም የትብብሩ አቋም ያልኾነ፣ እንዲያውም እየተከታተለ በተፃራሪው የቆመ በአቅሙ እንደዶሮዋ ጭሬ ላፍሰው ዓይነት መግለጫ ሲሰጥ ሰምተናል” ብሏል።

መግለጫው ድርጊቱን በጽኑ ያወገዘ ሲሆን፣ “ከሰሞኑ የትብብሩ አመራር በመምሰል የምርጫ ጉዳይ ኃላፊ ነኝ በሚል፣ በተግባርም በአስተዋጽዖም የማናውቀው ግለሰብ እንዲኽና እንዲያ አለ የሚል ውርውር ሲል ታዝበናል፤ እነዚህ የብፌ ፖለቲከኛና የሳይበሩ ሸኔ ትንኮሳ የዝኾን ጆሮ ላይ ያረፈ ዝንብ ናቸው” ሲል በስሙ የተላለፈውን መልዕክት አጣጥሏል።

በዚህም ድርጊት አባላቶቹ፣ ደጋፊዎቹ፣ ለእውነት የቆሙ የሚዲያ አካላትና ሕዝቡ ግራ መጋባቱን የጠቀሰው መግለጫው፤ “በይፋዊ ማኅበራዊ ገጾቻችን ላይ የማይገኝና ትብብሩ በይፋ ያልወከላቸው አካላት የሚሰጡት የጽሑፍም ሆነ የደጅ ጥናት ዓይነት የሚዲያ ልምምጦች የትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት አቋም እንዳልኾኑና ወደፊትም እንደማይኾኑ በአክብሮት እንገልፃለን” ሲል በጥብቅ አሳስቧል።

በትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት ቅንጅት ውስጥ “በምርጫው እንሳተፍ ወይስ አንሳተፍ?” በሚል ጥያቄ ዙሪያ በፓርቲዎቹ መካከል ከፍተኛ ክፍፍል ተፈጥሮ መቆየቱ በተደጋጋሚ ሲገለጽ ቆይቷል። ጥምረቱ “አስቻይ የፖለቲካ ሁኔታዎች እስካልተስተካከሉ ድረስ በምርጫው አንሳተፍም” የሚል ጠንካራ አቋም ይዞ የቆየ ቢሆንም፣ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ላይ ተሳትፎ አድርጓል። በዚህ መሐል የትብብሩ ዕጩዎች የሆኑት አቶ ይሳቅ ወልዳይ እና አቶ ኤፍሬም ካሳ ራሳቸውን ማግለላቸው ይታወሳል።

ይሁን እንጂ ትብብሩ ምርጫው ከተጠናቀቀ በኋላ ግንቦት 26 ቀን ጥምረቱ ባወጣው ይፋዊ መግለጫ አጠቃላይ ሂደቱን “የጨረባ ምርጫ” ሲል የኮነነ መሆኑና ዕጩዎቹ ቢመረጡም እንኳ በጥምረቱ ስም ወደ ምክር ቤት እንዳይገቡ ማሳሰቡ ይታወሳል።

መስከረም 2018 ዓ.ም. የተመሠረተው ይህ ጥምረት፤ አምስት የፖለቲካ ድርጅቶች በጋራ የመሠረቱት ቅንጅት ነበር። መስራቾቹም፦ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ)፤ እናት ፓርቲ፤ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ)፤ አንድ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ እና የአማራ ግዮናዊ ንቅናቄ (አግን) ነበሩ።

ይሁን እንጂ ምክንያቱ በይፋ ባልተገለጸ ሁኔታ ቅንጅቱ “አንድ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲን” ከመካከሉ በመቀነስ፣ ጥምረቱ በአራት ፓርቲዎች ብቻ ሆኖ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ተወዳዳሪ ሆኖ ቀርቧል። (ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)