ሰኞ ግንቦት 24 ቀን የተካሄደውን 7ኛውን ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ ተከትሎ፣ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ዛሬ አርብ ግንቦት 28 ቀን 2018 ዓ.ም. በሰጠው መግለጫ ምርጫው በሰላም መጠናቀቁ በበጎ የሚነሳ ቢሆንም፣ በገዢው ፓርቲ መዋቅራዊ ተፅዕኖዎች፣ በምርጫ ቦርድ ክፍተቶች እና በውጭ ሚዲያዎች ጣልቃ ገብነት ከፍተኛ ፈተናዎች እንደነበሩበት መገምገሙን አሳወቀ። ፓርቲው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋዊ ውጤቶችን ካወቀ በኋላ ዝርዝር ሪፖርት የሚያቀርብ መሆኑ ጠቅሶ፣ ለአሁኑ አጠቃላይ የምርጫውን መልክ የገመገመበትን ይፋዊ አቋም አስታውቋል።
ኢዜማ በምርጫው ሂደት የታዩ አዎንታዊ እርምጃዎችን በሪፖርቱ መጀመሪያ ላይ ያሰፈረ ሲሆን፣ በተለይም የመራጮች ምዝገባ ሂደት ላይ የታየውን ስኬት አድንቋል። ፓርቲው ምንም እንኳ ገዢው ፓርቲ ዜጎችን በኃይል አስገድዶ እንዲመዘገቡ ያደረገበት ሁኔታ ቢኖርም፣ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ መመዝገቡ “የመምረጥ ፍላጎትን ያሳየ ጠንካራ ጎን” ነው ብሏል።
በተለይም በኢትዮጵያ የምርጫ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የመራጮች እና የዕጩዎች ምዝገባ ሂደት በከፊል በዲጂታል መንገድ መከናወኑን የጠቀሰው ኢዜማ፣ “መራጮችና ዕጩዎች ለመጀመሪያ ጊዜ በአንላይን (በኢንተርኔት) አማካኝነት መመዝገብ መጀመራቸው ለዴሞክራሲ ሥርዓቱ መዘመን ታላቅ እርምጃ ነው” ሲል ዕውቅና ሰጥቷል። ከዚህ በተጨማሪም ለተፎካካሪ ፓርቲዎች ሰፊ የሚዲያ ዕድል፣ የጋራ ክርክሮች እና የአየር ሰዓት በአግባቡ መመቻቸቱ በሂደቱ የታዩ ስኬቶች መሆናቸውን ጠቅሷል።
ኢዜማ በሂደቱ ላይ የከረረ ትችት የሰነዘረው በገዢው ብልጽግና ፓርቲ ላይ ሲሆን፣ ፓርቲው የመንግሥት የልማት ፕሮግራሞችን እና የሕዝብ ሀብትን ለምርጫ ቅስቀሳ ሽፋንነት ተጠቅሞበታል ሲል ከሷል።
ኢዜማ እንደገለጸው፣ ብልፅግና ፓርቲ “እንደ ማኅበራዊ ጥበቃ፣ የትምህርት ቤት ምሳና መሠረታዊ አገልግሎቶችን ማቅረብን የመሰሉ የመንግሥት የልማት ፕሮግራሞችን ለምርጫ ቅስቀሳ ፖለቲካዊ መጠቀሚያ አድርጓቸዋል። ዜጎች ለገዢው ፓርቲ ድምፅ ካልሰጡ እነዚህ አገልግሎቶች እንደሚቋረጡባቸው ስጋት ውስጥ በመክተት፣ ድምፅ በነፃ ፍላጎት የመግዛት ስልት ተከትሏል። ይህንንም ትስስር ‘የብልጽግና ቤተሰብ’ በሚባል የዳቦ ስም በመሰየም የመራጮች ውሳኔ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ አሳድሯል።”
ፓርቲው አክሎም፣ በመራጮች ምዝገባ ወቅት የቀበሌና የሀገር ውስጥ የመንግሥት አስተዳደር ሠራተኞች የመራጭነት ካርድ ይዘው በሚወጡ ዜጎች ላይ “የስነ-ልቦና ጫና እና ማስፈራራት” መፍጠራቸውን፣ እንዲሁም የመንግሥት መገናኛ ብዙኃንን ገዢው ፓርቲ እንደ ግል ንብረቱ ሲጠቀምበት እንደነበር ኮንኗል። ወደ ምርጫ ጣቢያ በሚያመሩ መንገዶች ላይ “እንኳን ደህና መጣችሁ” የሚሉ ድብቅ የገዢው ፓርቲ መፈክሮች መታየታቸውንም አክሏል።
ኢዜማ የምርጫ ቦርድን አቅም በጠንካራ ሁኔታ የገመገመ ሲሆን፣ ቦርዱ አሁንም ቢሆን ጠንካራ ተቋም መሆን አለመቻሉን ገልጿል። በተለይም በምርጫው ዕለት አስፈጻሚዎች ሕጋዊ ኃላፊነታቸውን ወደ ጎን በመተው ከመንግሥት አካላት ጋር በጥቅም መተሳሰራቸውን ጠቅሷል።
“ከሁሉም በላይ አሳሳቢው ጉዳይ፤ በምርጫው ዕለት ሂደቱን እንዲያስፈጽሙ የተመደቡ የቦርዱ አስፈጻሚዎች ሕጋዊ ኃላፊነታቸውን በሌሎች የመንግሥት አስተዳደር አካላትና ግለሰቦች ሲነጠቁ፣ ድርጊቱን ከማስቆም ይልቅ ዝምታን መምረጣቸው ነው” ሲል ቅሬታውን ገልጿል። አክሎም፣ “ተቋሙ ካለፉት ምርጫዎች በቂ ትምህርት ወስዶ ገለልተኛ አስፈጻሚዎችን በጥንቃቄ መመልመል ሲገባው፣ በይድረስ ይድረስ መመልመሉ “ቁጥራቸው ቀላል የማይባል የቦርዱ አስፈጻሚዎች በተግባር የገዢው ፓርቲ ታማኝ ተላላኪዎች ሆነው ተገኝተዋል” ሲል ቦርዱን ከሷል።
በመንግሥት የጸጥታ መዋቅር በኩል የታዩ የሕግ ጥሰቶችን የዘረዘረው ኢዜማ፣ “የሰላም ሠራዊት” ተብለው የተደራጁ ኃይሎች፣ የወረዳ የሥራ አስፈጻሚዎችና የመንግሥት ሠራተኞች በሕግ ሥልጣን ባልተሰጣቸው የምርጫ ተግባራት ውስጥ ገብተው ግልጽ ጣልቃ ገብነት መፈጸማቸውን ገልጿል። በተለይም ከከተማ ርቀው በሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች ላይ የመንግሥት የጸጥታ አካላት የተፎካካሪ ፓርቲ ታዛቢዎችን ሲያስፈራሩ፣ ሲያሳድዱ እና በጉልበት ከጣቢያዎች ሲያስወጡ መታዘቡን ይፋ አድርጓል።
በሌላ በኩል፣ ኢዜማ የውጭ አገራትና ዓለም አቀፍ የዜና ማዕከላት በምርጫው ሂደት ላይ የነበራቸውን ሚና የኮነነ ሲሆን፣ እነዚህ አካላት የኢትዮጵያን ምርጫ ሂደትን ሙሉ በሙሉ ገለልተኝነት የሌለውና ተዓማኒነት የጎደለው ለማስመስል “ፖለቲካዊ እና ስትራቴጂካዊ ፍላጎትን ብቻ ያማከለ ጫና” ሲፈጥሩ ነበር ብሏል። ይህ ድርጊት አገርን መሪ አልባ የማድረግ እና ብሔራዊ ተቋማትን የማፍረስ ዓላማ ያለው መሆኑን ፓርቲው በጥብቅ ገልጿል።
ኢዜማ በሪፖርቱ ማጠቃለያ ላይ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችም የራሳቸው ድክመት እንደነበረባቸው አልሸሸገም። አንዳንድ ፓርቲዎች የዴሞክራሲ ምኅዳሩን ለማሻሻል ከመሥራት ይልቅ፣ “ሁለት ልብ” ሆነው የምርጫውን ሂደት ማጣጣልን ምርጫ ማድረጋቸውን፣ አማራጭ የፖሊሲ ሐሳቦችን ከማቅረብ ይልቅ የሕዝብን ስሜት በመቀስቀስ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት መሞከራቸውን እና በሁሉም የምርጫ ክልሎች ታዛቢዎችን ማሰማራት አለመቻላቸውን በጉድለትነት ጠቅሷል። ኢዜማ የመንግሥት ሥልጣን ሊያዝ የሚችለው በሰላማዊ መንገድና በምርጫ ሥርዓት ብቻ መሆኑን የጠቀሰ ሲሆን፣ ያጋጠሙት መዋቅራዊ ችግሮች ቢኖሩም በምርጫው የታዩትን ጠባብ የዴሞክራሲ ዕድሎች ተጠቅሞ የሰላማዊ ትግል አማራጩን አጠናክሮ እንደሚቀጥልና ከሕዝብ ጎን በጽናት እንደሚቆም አስታውቋል። (ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)




