የ7ኛው ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ የድምፅ አሰጣጥ መጠናቀቁን ተከትሎ፣ ከተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በኩል የሚሰነዘሩ ይፋዊ ወቀሳዎችና ክሶች ከመዋቅራዊ የምርጫ ማጭበርበር ባለፈ፣ ወደ ድኅረ ምርጫ እስራት፣ ድብደባና የታዛቢዎች ማደናቀፍ መሸጋገራቸውን ፓርቲዎቹ ለ“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገለጹ። ተቃዋሚዎቹ በምርጫው ዕለትና በማግስቱ ያጋጠሟቸውን እክሎች ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በይፋ እያሳወቁ ሲሆን፣ ቦርዱም የቀረቡለትን በርካታ አቤቱታዎች ለመመርመር የሕግ ባለሙያዎች ቡድን በማቋቋም የማጣራት ሥራ መጀመሩን አስታውቋል።
የዎላይታ ሕዝቦች ነፃነት ንቅናቄ (ዎህነን) በ60 የምርጫ ክልሎች በሚገኙ ጣቢያዎች ላይ እያንዳንዳቸው ሁለት ታዛቢዎችን መድቦ እንደነበር የጠቀሱት የፓርቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ወልደማርያም ልሳኑ፣ ግንቦት 24 ቀን የተካሄደው ምርጫ እስከ ምሽቱ 12:00 ሰዓት ድረስ ሰላማዊ ቢመስልም፣ በወላይታ ሶዶ ከተማ በስምንት የምርጫ ጣቢያዎች ላይ የፌደራል፣ የክልልና የዞን አመራሮች በሲቪል የለበሱ ፖሊሶች ታጅበው በመግባት ሁከት መፍጠራቸውን ገልጸዋል።
በሰልፍ ላይ የነበረውን ሕዝብ በመበተን ሂደቱ እንዲጓተት መደረጉንና ቅሬታ ለማስገባት የነበሩ የቅሬታ ቅጾችን ጭምር መከልከላቸውን የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፣ “አንድ ሰው አምስት እና ስድስት ካርድ ይዞ መመረጥ የለበትም በሚል ቅሬታ ብናሰማም ምንም መፍትሔ ማግኘት አልቻልንም” ሲሉ ሂደቱን ነቅፈዋል።
ከዚህም ባሻገር ከሌሊቱ ስድስት ሰዓት ቆጠራው ሳይጠናቀቅ ታዛቢዎቻቸው በደባና በማስገደድ እንዲወጡ መደረጋቸውን ጠቅሰው፣ በዳሞት ጋሌ 1 እና 2፣ ኢንዶ ኮይሻ 2፣ ቦሎሶሶሬ ከ1 እስከ 3፣ ቦሎኮምቦ እና ኮይሻ ባሉ ጣቢያዎች በመገፋታቸው “ምርጫውን ተነጥቀናል” ብለዋል።
ስምንት የሚሆኑ የተቃዋሚ ፓርቲ ታዛቢዎች ደግሞ ባጃቸውን ለገዢው ብልጽግና ፓርቲ አባላት በመሸጥ ጣቢያዎቹን ለቀው መውጣታቸውን የጠቆሙት ፕሬዚዳንቱ፣ ያጋጠማቸውን ችግር ለምርጫ ቦርድ በይፋ ለማስገባት በሂደት ላይ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
በተመሳሳይ ሁኔታ የጎጎት ለጉራጌ አንድነት እና ፍትሕ ፓርቲ ፕሬዚዳንት አቶ መሐመድ አብራር ለ“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” በሰጡት ማብራሪያ፣ ፓርቲያቸው አስቀድሞ የተወዳደረው አንጻራዊ ሰላም ባለባቸው አካባቢዎች በመሆኑ ከጸጥታ አንጻር የገጠመው ከባድ እክል ባይኖርም፣ በአብሽቄ ምርጫ ክልል እና በሶዶ ወረዳ የተወሰነ የጸጥታ መስተጓጎል በመፈጠሩ ድምፅ ቆጠራው ሳይጠናቀቅ ማደሩንና ሂደቱ ከቁጥጥር ውጭ ወጥቶ እንደነበር ጠቁመዋል።
ፕሬዚዳንቱ በጉራጌ ዞን እና በምሥራቅ ጉራጌ ዞን ምርጫ ክልሎች የተካሄደውን የምርጫ ሂደት ሲኮንኑ፣ “ምርጫው አንድም ታዛቢ እና ሚዲያ በሌለበት የተደረገ ከመሆኑ አኳያ በተለይ ወደ ገጠሩ የነበረው ምርጫ በአንድ ወገን ቁጥጥር ስር የነበረ ነው” ብለዋል። ጎጎት በገዢው ፓርቲ አመራሮች ደረሱብኝ ያላቸውን እነዚህን ጥሰቶች ለምርጫ ቦርድ በየእርከኑ እያቀረበ መሆኑን አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ግንቦት 28 ቀን 2018 ዓ.ም. ባወጣው የመጀመሪያ ዙር የምርጫ ግምገማ መግለጫ፣ ምርጫው በሰላም መጠናቀቁ በበጎ የሚነሳ ቢሆንም፣ በገዢው ፓርቲ መዋቅራዊ ተፅዕኖዎች፣ በምርጫ ቦርድ ክፍተቶች እና በውጭ ሚዲያዎች ጣልቃ ገብነት ከፍተኛ ፈተናዎች እንደነበሩበት አሳውቋል።
ፓርቲው ገዢው ብልጽግና ፓርቲ የመንግሥት የልማት ፕሮግራሞችን እና የሕዝብ ሀብትን ለምርጫ ቅስቀሳ ሽፋንነት ተጠቅሞበታል ሲል በጥብቅ ከሷል። በጉራጌ ዞን እዣ ምርጫ ክልል የኢዜማ ዕጩ ዶክተር አብርሃም በርታ ለ“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” እንደገለጹት፣ የወረዳው የምርጫ ቦርድ አስፈጻሚዎች የገዢው ፓርቲ አባል የነበሩና የብልፅግና ፓርቲ አርማ ይዘው የሚዞሩ በመሆናቸው የገለልተኝነት ጥያቄ ነበረባቸው።
ዶክተር አብርሃም በሚደርስባቸው ጫና ለቦርዱ ቢያመለክቱም ሂደቱ በማድበስበስ ማለፉን ጠቅሰው፣ ቦርዱ ገለልተኛ ያልነበረበት ምርጫ በመካሄዱ ገዢው ፓርቲ ማሸነፉንና እነሱ ውጤት ማጣታቸውን ገልጸዋል። “ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” በቅስቀሳ ወቅት ከኢዜማ እና ከጎጎት በደረሳት ጥቆማ መሠረት ጉዳዩን ቦርዱን ጠይቃ ያገኘችው ምላሽ፣ አስፈጻሚዎቹ የገዢው ፓርቲ አባላት መሆናቸውን በመጥቀስ የቀረበው ክስ የተሳሳተ መሆኑንና ግለሰቦቹ በምርጫ ጣቢያዎቹ አልተመደቡም የሚል ቢሆንም፣ የኢዜማ ዕጩ ግን ሂደቱን በተቃውሞ ነቅፈውታል።
በሌላ በኩል፣ ባለፈው 6ኛው አገራዊ ምርጫ የፓርላማ እና የክልል ምክር ቤት ወንበሮችን አሸንፎ የነበረው የቁጫ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቁሕዴፓ)፣ ዘንድሮ በአካባቢው ባለሥልጣናት የቅስቀሳ ዕንቅፋቶች ሲፈጠሩበት ከቆየ በኋላ ግንቦት 24 በተከናወነው ምርጫ ላይ ፍጹም የኮሮጆ ማጭበርበር ተፈጽሟል በሚል በቁጫ ምርጫ ክልል የተካሄደው ምርጫ “ተጭበርብሯል” ሲል ግንቦት 26 ቀን ባወጣው መግለጫ አጋልጧል።
በተመሳሳይ ዕለት መግለጫ ያወጣው ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት ቅንጅት በበኩሉ፣ 7ኛውን ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ “ዴሞክራሲን አያዋልድ፣ መፍትሔም አይፈይድ” ሲል በጽኑ ወቅሶታል። ጥምረቱ አጠቃላይ ሂደቱ ከኢሕአዴጋዊ የጥርነፋ ውርስ ባሕርይ እና የጥቅለላ አባዜ ያልተላቀቀ ነው ሲል የከሰሰ ሲሆን፣ ውጤቱ ምንም ይሁን ምን ማንኛውም ዕጩ በትብብሩ ስም ወደ ምክር ቤት ቢገባ ፍጹም ተቀባይነት እንደማይኖረው አስታውቋል።
ፓርቲዎቹ በምርጫው ዕለት ካጋጠሟቸው መዋቅራዊ ችግሮች በተጨማሪ፣ ከምርጫው መጠናቀቅ በኋላ የተጀመረውን የድኅረ ምርጫ ወከባና እስር ለ“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” በዝርዝር አስረድተዋል። የዎላይታ ሕዝቦች ነፃነት ንቅናቄ (ዎህነን) በማኅበራዊ ሚዲያው ድኅረ ምርጫ ወከባና እስር መጀመሩን የገለጸ ሲሆን፣ የፓርቲው ብሔራዊ ጽሕፈት ቤት ዋና ኃላፊ እና የዳሞት ወይዴ 2 ምርጫ ክልል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዕጩ ተወዳዳሪ መምህር ታድዮስ ጭናሾ መና ግንቦት 26 ቀን የግዜያዊ የምርጫ ውጤትን ለማየት ወደ ትውልድ ስፍራቸው ባቀኑበት በድጉና ፋንጎ ወረዳ በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋላቸውን አሳውቋል።
የፓርቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ወልደማርያም ልሳኑ እንደገለጹት፣ ዕጩው በጣቢያው ጊዜያዊ ውጤትን ፎቶ ለማንሳት ሲሞክር የቀበሌ አመራሮች የከለከሉት ሲሆን፣ በመቀጠልም ስምንት የሚሆኑ አመራሮች “ስትቀስቀስና ስትጨፍር ዝም ብለንሃል” በሚል ድብደባ ፈጽመውበታል።
ዕጩው በቀበሌ ጽሕፈት ቤት ታስሮ ከቆየ በኋላ እስከ ምሽት በፖሊስ ጣቢያ እንዲቆይ የተደረገ ሲሆን፣ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሰጠው አስቸኳይ ትዕዛዝና ጣልቃ ገብነት ምሽቱን ከእስር ሊፈታ ችሏል።
በተመሳሳይ ሁኔታ የጎጎት ፓርቲ ፕሬዚዳንት አቶ መሐመድ አብራር እንደገለጹት፣ በዕጩዎቻቸው ላይ በቀጥታ የደረሰ እስር ባይኖርም፣ ዕጩ ተወካይ ታዛቢዎቻቸው ላይ ከምርጫው ዕለት ጀምሮ እስከ ድኅረ ምርጫው ድረስ የበረታ ጫና እየተደረገባቸው ይገኛል።
ታዛቢዎቹ “ካለንበት አካባቢ ካልወጣን ለሕይወታችን እንሰጋለን፣ ልንታሰር እንችላለን” በሚል ፍርሃት ውስጥ መሆናቸውንና በመንግሥት ሥራ ላይ በነበሩ ታዛቢዎች ላይ ደግሞ ከወዲሁ የሥራ ዋስትና ማስፈራሪያዎች እየደረሷቸው መሆኑን አቶ መሐመድ አብራር የጉዳዩን አስቸጋሪነት ሲያስረዱ ገልጸዋል።
ምርጫ ቦርድም እንዲህ ያሉ አቤቱታዎች በተደጋጋሚ እየቀረቡለት መሆኑን ገልጿል። የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ ግንቦት 29 ቀን 2018 ዓ.ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ በልዩ ቅጽ ተሞልተው በሰው፣ በቪዲዮና በሰነድ ማስረጃዎች የተደገፉ 47 መደበኛ ቅሬታዎች ለቦርዱ መቅረባቸውንና ከእነዚህ ውስጥ 31ዱ በፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ቀሪዎቹ 16ቱ ደግሞ በግል እጩዎች የቀረቡ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
ሰብሳቢዋ የቅሬታዎቹ ይዘት ሰፊ መሆኑን ጠቅሰው፣ የፓርቲ ወኪሎች ወደ ምርጫ ጣቢያ እንዳይገቡ መከልከል፣ ዕጩዎች ከውድድር እንዲወጡ ማስፈራራት፣ የምርጫ አስፈጻሚዎች ግልጽ ወገንተኝነት ማሳየት እንዲሁም ቦርዱ የምርጫ ሰዓት እንዲራዘም ቢወስንም አንዳንድ ጣቢያዎች ቀድመው በ12:00 ሰዓት መዝጋታቸው ከቀረቡት ቅሬታዎች መካከል ዋነኞቹ መሆናቸውን ገልጸው፣ የተመሠረተው የሕግ ባለሙያዎች ቡድን አቤቱታዎቹን መመርመር መጀመሩን አስታውቀዋል። (ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)




