በልዩ ሁኔታ በተቋቋሙ የምርጫ ጣቢያዎች ድምፅ የመስጠት ሂደት እየተከናወነ ነው፤ በተፈናቃይ መጠለያዎች የመራጮች መረጃ እጥረት ማጋጠሙ ተነገረ

ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም. ከተከናወነው 7ኛው ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ ቀጥሎ፣ በልዩ ሁኔታ በወታደራዊ ካምፖች እና በተፈናቃይ መጠለያ ጣቢያዎች ለሚገኙ ዜጎች ዛሬ ሰኔ 2 ቀን እንዲካሄድ በተያዘው መርሃ-ግብር መሠረት ድምፅ የመስጠት ሂደት እየተከናወነ ይገኛል።

ይሁን እንጂ በዕለቱ ውሎ በተለይም በተፈናቃይ መጠለያዎች ውስጥ አስቀድሞ የመራጮች ግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት አለመኖሩ እና በመከላከያ ካምፖች ደግሞ የምርጫ አስፈጻሚዎች የመከላከያ ደንብ ልብስ ለብሰው መገኘታቸው በሂደቱ ላይ የታዘብናቸው ዋና ዋና ክስተቶች ናቸው።

የ“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢዎች በመከላከያ ሠራዊት ስፖርትና ኪነ-ጥበብ ግቢ (በሙዚቀኞች ካምፕ) ውስጥ በተቋቋመው ልዩ የምርጫ ጣቢያ ተገኝተው የድምፅ አሰጣጥ ሂደቱን ተከታትለዋል። ዘጋቢዎቻችን በስፍራው ባደረጉት የቅኝት ቆይታ እስከ ረፋዱ 5:06 ሰዓት ድረስ 150 የመከላከያ ሠራዊት አባላት ድምፃቸውን ሰጥተዋል።

የምርጫ ጣቢያው ኃላፊ ለሚዲያችን እንደገለጹት, በዚህ ልዩ ጣቢያ ውስጥ የስታፍ ኮሌጅ፣ የመከላከያ ስፖርት ቡድን እና የኪነ-ጥበብ ካምፕ አባላትን ጨምሮ በአጠቃላይ 300 የሚሆኑ መራጮች ተመዝግበዋል። ኃላፊው አክለውም በሕጉ መሠረት በልዩ የምርጫ ጣቢያዎች እስከ 700 መራጮች መመዝገብ እንደሚችሉ ጠቅሰው፣ በአሁኑ ወቅት ሂደቱ ያለምንም መጨናነቅ በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ መሆኑን አስረድተዋል።

ይሁን እንጂ በወታደራዊ ካምፑ ውስጥ በተካሄደው በዚህ ምርጫ ላይ የሲቪል ማኅበራት ታዛቢዎች በቦታው ያልነበሩ ሲሆን፣ የምርጫ ጣቢያ ኃላፊውን ጨምሮ መዝገብ ሹሙ እና አስፈጻሚዎቹ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ይፋዊ ደንብ ልብስ ለብሰው ሥራቸውን ሲያከናውኑ ተስተውለዋል።

በተጨማሪም ምርጫውን ሲያስፈጽሙ የነበሩት የሠራዊቱ አባላት የወይንጠጅ ቀለም ያለው የምርጫ ቦርድ አርማ ያለበትን አልባሳት ከመልበስ ውጭ፣ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የዕውቅና ባጅ አለማድረጋቸውን ታዝበናል። ከመራጮቹ መካከልም የተወሰኑት በስፖርት ትጥቅ፣ ቀሪዎቹ ደግሞ በሠራዊቱ ደንብ ልብስ ሆነው ድምፅ ሰጥተዋል።

ከጠዋቱ 12:00 ሰዓት ጀምሮ ክፍት በሆነው በዚህ ጣቢያ፣ የምርጫ ካርድ የጠፋባቸው አንዳንድ አባላት ለመምረጥ የመጡ ቢሆንም፣ በመዝገብ ላይ የማመሳከር ሥራ ተሠርቶላቸው ድምፅ እንዲሰጡ ተደርጓል። በአንጻሩ በሌላ አካባቢ ተመዝግበው ለመምረጥ የመጡ አራት መራጮች በሕጉ መሠረት ሳይስተናገዱ እንዲመለሱ መደረጋቸውን የጣቢያው ኃላፊ ገልጸዋል። በካምፑ ውስጥ የፎቶና ቪዲዮ ቀረጻ በጥብቅ የተከለከለ በመሆኑ ምስላዊ መረጃዎችን ማካተት አልተቻለም።

በዛሬው ዕለት ከወታደራዊ ካምፖች በተጨማሪ በተፈናቃይ መጠለያዎችም ልዩ ምርጫው እየተካሄደ ይገኛል። በደብረ ብርሃን ከተማ በሚገኘው የ“ቻይና ካምፕ” ተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያ ምርጫው እየተካሄደ መሆኑን የገለጹት የመጠለያው ኮሚቴ አስተባባሪ፣ በመጠለያው ውስጥ ስላለው የመረጃ ክፍተት ሲያስረዱ፣ “በዚህ ምርጫ ጣቢያ መራጩ ሕዝብ ዛሬ ምርጫ እንዳለ ያወቀው ጠዋት ላይ ‘ውጡና ምረጡ’ ተብሎ ቅስቀሳ ሲደረግ እንጂ፣ ከዚያ በፊት ምርጫ መኖሩን እንኳ የሚያውቅ ሰው አልነበረም” ብለዋል።

በጥዋቱ በተደረገው ቅስቀሳ መራጩ ወጥቶ እንዲመርጥ ቢያስተባብሩም በቂ ፍላጎት አለመታየቱን የጠቀሱት አስተባባሪው፣ ለዚህም ዋነኛው ምክንያት መራጮቹ ማንን እና ምን ምርጫ እንደሚመርጡ አስቀድመው ባለማወቃቸው እንደሆነ ገልጸዋል። በጣቢያው ጥቂት መራጮችና የጸጥታ አካላት ብቻ የሚታዩ ቢሆንም ሂደቱ መቀጠሉ ተገልጿል።

በተመሳሳይ ሁኔታ በደብረ ብርሃን “ወይንሸት” መጠለያ ካምፕ የተመደቡ የምርጫ አስፈጻሚ ለ“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” እንደገለጹት፣ ድምፅ አሰጣጡ በተያዘው ዕቅድ መሠረት እየሄደ ቢሆንም፣ ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በኩል ግን በቂ የምግብ እና የውኃ አቅርቦትን የመሰሉ መሠረታዊ ድጋፎች አልተደረጉላቸውም።

እኚህ አስፈጻሚ አክለውም፣ በመጠለያው ውስጥ ለነዋሪው ሕዝብ የተሰጠ ምንም ዓይነት የመራጮች ትምህርት ባለመኖሩ፣ ኅብረተሰቡ ስለ ዕጩዎቹም ሆነ ስለ ምርጫው ይዘት መረጃ እንደሌለው አረጋግጠዋል።

በዚሁ የ“ወይንሸት” መጠለያ ጣቢያ ሲያስተባብሩ የነበሩ ሌላ ተፈናቃይ በበኩላቸው፣ መራጩ ሕዝብ በጠዋቱ ወጥቶ ድምፅ የሰጠ በመሆኑ እስከ ረፋዱ 7፡42 ሰዓት ድረስ የመራጮች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሱን እና አልፎ አልፎ የሚመጡ ዜጎች ብቻ እየተስተናገዱ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህ ጣቢያ ከ400 እስከ 500 የሚደርስ መራጭ የሚጠበቅ ሲሆን፣ እስካሁን ያጋጠመ ከባድ ችግር የለም። ይሁን እንጂ በጣቢያዎቹ ውስጥ ሂደቱን ሙሉ በሙሉ ሲያስተባብሩ የቆዩት ከመጠለያ ጣቢያው ራሳቸው የተመረጡ ተፈናቃይ አስተባባሪዎች ብቻ መሆናቸውንና ከምርጫ ቦርድ በቀጥታ የመጣ አንድም የውጭ አስተባባሪ አለመኖሩን አስተባባሪዎቹ ለ“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስታውቀዋል። (ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)