ምርጫ ቦርድ የ24 ምርጫ ክልሎች ውጤቶችን አፀደቀ፤ ሁለት ብልፅግና ያልተፎካከራቸው የተቃዋሚ ፓርቲ ዕጩዎች መመረጣቸው ታውቋል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዛሬ፣ ሰኔ 2፣ 2018 የመጀመሪያ ዙር የ24 ምርጫ ክልሎችን ውጤት አፅድቆ ይፋ አድርጓል። ከተረጋገጡት ውጤቶች መካከል ከአንድ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት (ፓርላማ) እና ከአንድ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት ወንበሮች በቀር፣ በሁሉም ብልፅግና ፓርቲ ያሸነፈ ሲሆን፣ የተቃዋሚ ፓርቲ ዕጩዎች ያሸነፉባቸው ሁለት ወንበሮች ገዢው ፓርቲ ዕጩዎችን ያላቀረበባቸው መሆኑ ታውቋል።

ምርጫ ቦርድ ይህንን ከፊል ውጤት ይፋ ያደረገው የ7ኛውን ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ ውጤት የማጠቃለል ሂደት በማዕከል ደረጃ የደረሱትን ውጤቶች በማፅደቅ መጀመሩን ባስታወቀበት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው። ቦርዱ በመመሪያ ቁጥር 14/2013 አንቀጽ 54 መሠረት ውጤታቸው ተጣርቶ ያለቀላቸውን ምርጫ ክልሎች ውጤት በየደረጃው ይፋ ማድረግ እንደሚችል ገልጿል።

በዚሁ መግለጫ የምክር ቤቶች ወንበሮች ውጤቶች የ24 (12 የክልል ምክር ቤት እና 12 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት) መሆናቸው ታውቋል።

በዚህም መሠረት ለክልል ምክር ቤት ወንበሮች ማሸነፋቸው ይፋ ከተደረጉት 12 የምርጫ ክልሎች ተወዳዳሪዎች መካከል በኦሮሚያ ክልል ስር የሚገኙት ስምንት ምርጫ ክልሎች (ጭሮ 2፣ ቅንበቢት፣ ሚጨታ፣ ጎማ 1፣ ሂርና፣ ጀልዱ፣ ግራዋ እና በዴሳ) 24 ወንበሮችን እንዲሁም በአማራ ክልል የመቄት 1 እና የጎንደር ዙሪያ 4 ምርጫ ክልሎች አራት ወንበሮችን፣ በጋምቤላ ክልል የዲማ ምርጫ ክልል 10 ወንበሮችን በሙሉ፣ እንዲሁም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ኩርሙክ የምርጫ ክልል ካሉ 9 ወንበሮች መካከል ስምንቱን በአጠቃላይ 46 ወንበሮችን የብልፅግና ፓርቲ ዕጩዎች አሸንፈዋል።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ኩርሙክ ምርጫ ክልል ቀሪውን አንድ መቀመጫ የቤንሻንጉል ሕዝብ ነፃነት ንቅናቄ (ቢህነን) ዕጩ የሆኑት አቶ ሀሲል አርባብ ሀሚስ አሸንፈዋል። ይህ የምርጫ ክልል ገዢው ብልፅግና ፓርቲ በምርጫ ክልሉ ካሉት ዘጠኝ ወንበሮች መካከል በአንዱ ላይ ዕጩ ሳያቀርብ የቀረበት መሆኑን “ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ቦርዱ በሚያዝያ ወር ይፋ ካደረገው የዕጩዎች ዝርዝር ተረድታለች።

ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውጤታቸው ይፋ ከሆኑት 12 ምርጫ ክልሎች ውጤቶች መካከልም በተመሳሳይ ሁኔታ 11ዱን የኦሮሚያ ክልል ወንበሮች (ሀሮማያ 1፣ ግራዋ፣ ሳጉሬ፣ ጫንጮ፣ ጭሮ 2፣ ኦሞናዳ 1፣ ሚጨታ፣ በዴሳ፣ አርዶዬ፣ ጎማ 1 እና ወንጪ) የብልፅግና ፓርቲ አሸንፏል።

በአማራ ክልል የጎንደር ዙሪያ 4 ምርጫ ክልል መቀመጫን ግን ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የተወዳደሩት አቶ ጣሂር መሀመድ ጣሂር አሸንፈዋል። ይህ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ወንበርም ገዢው ብልፅግና ፓርቲ ዕጩ ያላቀረበበት የምርጫ ክልል እንደነበር በቦርዱ የዕጩዎች ዝርዝር ላይ ተመልክቷል።

ቦርዱ በመግለጫው እንደገለጸው፣ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ከተካሄደባቸው 501 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና 638 የክልል ምክር ቤቶች (በአጠቃላይ 1,139 ምርጫ ክልሎች) መካከል ከሁለቱ በስተቀር በሁሉም ቦታዎች የማዳመር ሥራ ተጠናቆ ውጤቱ በየምርጫ ክልሉ ተለጥፏል።

የማዳመር ሥራቸው ገና ያልተጠናቀቀው የሃላባ 1 እና የቀብሪ በያህ ምርጫ ክልሎች ብቻ ናቸው። የሃላባ 1 ምርጫ ክልል ውጤት ማዳመር የዘገየው ሥራው ወደ ሆሳእና ተልኮ መሠራት ስላለበት ሲሆን፣ የቀብሪ በያህ ምርጫ ክልል ደግሞ ከተለያዩ ወረዳዎች የሚመጡ ውጤቶችን ሰብስቦ ለማዳመር ጊዜ በመውሰዱ እንደሆነ ተብራርቷል።

የማዳመር ሥራቸው ከተጠናቀቁት የምርጫ ክልሎች መካከል እስካሁን ወደ ማዕከል የደረሱት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት (ፓርላማ) ከ501 መቀመጫዎች ውስጥ የ353 ምርጫ ክልሎች ሲሆን፣ የተቀሩት የ148 ምርጫ ክልሎች ውጤቶች በአሁኑ ወቅት በጉዞ ላይ ይገኛሉ ተብሏል።

በተመሳሳይ፣ ከ638 የክልል ምክር ቤቶች መቀመጫዎች ውስጥ የ463 ምርጫ ክልሎች ውጤት ማዕከል የደረሰ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ የቀሩት የ175 የክልል ምርጫ ክልሎች ውጤቶች በጉዞ ላይ ናቸው።

የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ የውጤት አሰጣጥ ሂደቱን አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ፤ በአዋጁ መሠረት አጠቃላይ የምርጫ ውጤትን ቦርዱ በአንድ ጊዜ ይፋ የሚያደርግበት ቀን የተቀመጠ ቢሆንም፣ ያንን ቀን ማሳካት ካልተቻለ ግን አዋጁ የመፍትሔ አቅጣጫ ማስቀመጡን ገልጸዋል።

በዚህም መሠረት ቦርዱ የተጠቃለለ የምርጫ ክልል ውጤት ሙሉ በሙሉ ባይደርሰውም እንኳ፣ የደረሱትን ጊዜያዊ ውጤቶች ከስር ከስር ይፋ ማድረግ እንደሚችል በተደነገገው መሠረት የተወሰኑትን ይፋ እያደረገ እንደሚሄድ አብራርተዋል።

ቅሬታ የቀረበባቸውን ምርጫ ክልሎች በተመለከተ፣ እነዚህ አካባቢዎች ወደ ኋላ እንዲቆዩ ተደርገው በቀጥታ ወደ ኦዲት ክፍል እንደሚላኩ ሰብሳቢዋ ተናግረዋል። የኦዲት ክፍሉ የማጣራት ሥራውን ከሠራ በኋላ ችግር የሌለባቸውን ወደ ቦርዱ ለውሳኔ የሚልክ ሲሆን፣ ችግር የተገኘባቸው ጣቢያዎች ላይ ደግሞ ተገቢው ውሳኔ ይሰጥባቸዋል።

በውጤት ቅጹ አወቃቀር ላይ የምርጫ ክልሉ ስም፣ የክልሉ ስም፣ የምርጫ ጣቢያ ብዛት፣ እንዲሁም ጥቅም ላይ ያልዋሉና የተበላሹ የድምፅ መስጫ ወረቀቶች ብዛት ተቆጥሮ በዝርዝር እንደሚቀመጥ ዋና ሰብሳቢዋ ገልጸዋል።

ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከአንድ ምርጫ ክልል አንድ ሰው ብቻ የሚመረጥ በመሆኑ ከተወዳዳሪዎች መካከል ከፍተኛውን ነጥብ ያገኘው ዕጩ በደረጃው እንደሚመዘገብ ጠቅሰው፣ በክልል ምክር ቤት በኩል ደግሞ የምክር ቤቱ መቀመጫ ቁጥር ከክልል ክልል ስለሚለያይ መቀመጫዎቹ በዝርዝር ተለይተው እንደሚቀመጡ አብራርተዋል።

በሌላ በኩል፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በመደበኛው የምርጫ ዕለት ድምፅ መስጠት ላልቻሉ ልዩ ወገኖች ሰኔ 2 ቀን 2018 ዓ.ም. ስላከናወነው ልዩ ምርጫም ሰብሳቢዋ ማብራሪያ ሰጥተዋል። በዚህም መሠረት ከመደበኛ መኖሪያቸው ለተፈናቀሉ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች እና በየካምፑ ለሚኖሩ የጦር ሠራዊት አባላት ልዩ የምርጫ ጣቢያዎች ተዘጋጅተው የድምፅ መስጠት ሂደት ሲከናወን መዋሉን ገልጸዋል።

ይህ ልዩ የድምፅ መስጠት ሂደት በ442 የወታደር ካምፖች እና በ82 የተፈናቃይ መጠለያ ካምፖች ውስጥ መካሄዱ የተገለጸ ሲሆን፣ በወታደር ካምፖች 126,498 መራጮች፣ በሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ካምፕ ደግሞ 28,632 መራጮች ተመዝግበው ነበር። መግለጫው እስከተሰጠበት ሰዓት ድረስ በሀገር ውስጥ ተፈናቃይ ካምፖች ሙሉ በሙሉ፣ በወታደር ካምፖች ደግሞ ከአንድ ጣቢያ በስተቀር በሁሉም ቦታዎች የድምፅ መስጠት ሂደቱ ያለምንም ከባድ የጸጥታ እክል በሰላም መጠናቀቁን ቦርዱ አስታውቋል። (ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)