እስካሁን በታወጁት የምርጫ ውጤቶች ብልፅግና ፓርቲ የተወዳደረባቸውን ወንበሮች በሙሉ ማሸነፉ ታውቋል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የ7ኛውን ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ ከፊል ውጤት እወጃ ከትላንት በመቀጠል፣ ዛሬ ሰኔ 3 ቀን 2018 ዓ.ም. ምሽት በስካይ ላይት ሆቴል በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ የሌሎች 22 የምርጫ ክልሎችን ውጤት አፅድቆ ይፋ አድርጓል።

ቦርዱ ባወጣው በዚህ የሁለተኛ ዙር ከፊል ውጤት መሠረት፣ ከተገለጹት ጠቅላላ 48 የምክር ቤት መቀመጫዎች መካከል ከአንዱ በስተቀር የገዢው ብልፅግና ፓርቲ ዕጩዎች ያሸነፉ ሲሆን፣ የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር (ኦብነግ) ዕጩ ደግሞ በሶማሌ የክልል ምክር ቤት አንድ ወንበር ማሸነፉ ታውቋል።

ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በጠቅላላው የ10 የምርጫ ክልሎች/ወንበሮች ውጤት የተገለጸ ሲሆን (1 ከአማራ፣ 3 ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ እና 6 ከኦሮሚያ)፣ 10ሩንም መቀመጫዎች በሙሉ የብልፅግና ፓርቲ ዕጩዎች አሸንፈዋል። ውጤታቸው የተገለጹት የምርጫ ክልሎችም በአማራ ክልል ጎዛምን፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ቀዲዳ ጋሜላ 2፣ ጉመር 1 እና እዣ 2 ሲሆኑ፣ በኦሮሚያ ክልል ደግሞ ሀብሮ 1፣ ቅንበቢት፣ ጥቁር እንጭኒ፣ ጀልዱ፣ ወሊሶ 2 እና ወሊሶ 1 የምርጫ ክልሎች ናቸው።

በዛሬው ውጤት እወጃ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ወይም የግል ዕጩዎች ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት (ፓርላማ)  ምንም መቀመጫ አላሸነፉም።

ለክልል ምክር ቤቶች በጠቅላላው የ12 የክልል ምክር ቤት የምርጫ ክልሎች ውጤቶች ተነግረዋል። የክልል ምክር ቤት ምርጫዎች በየምርጫ ክልሉ ብዙ መቀመጫዎች ያሏቸው በመሆኑ፣ በድምሩ የ38 መቀመጫዎች ውጤት የታወጀ ሲሆን፣ ከነዚህም ውስጥ ብልፅግና ፓርቲ 37ቱን አሸንፏል።

በዛሬው ውጤት ብቸኛውን የተቃዋሚ ወንበር ያሸነፈው ኦብነግ ሲሆን፣ በሱማሌ ክልል በደገ ሀቡር የምርጫ ክልል ነው። በሶማሌ ክልል ስር ካሉት ሁለት የምርጫ ክልሎች (ብርቆት እና ደጋህቡር) ውስጥ ለክልል ምክር ቤት ከተመደቡት ስምንት ወንበሮች መካከል ሰባቱን ብልፅግና ሲያሸንፍ፣ በደገ ሀቡር አንዱን ወንበር የኦጋዴን ግንባር ዕጩ የነበሩት አቶ መሀሙድ ሀሰን ሁሴን አሸንፈዋል።

በደጋህቡር የምርጫ ክልል ብልፅግና ለክልሉ ምክር ቤት ሦስት ዕጩዎችን ብቻ ያቀረበ በመሆኑ፣ የኦጋዴን ዕጩ ያሸነፉት ወንበር ገዢው ፓርቲ አስቀድሞ ያልተወዳደረበት መሆኑ ታውቋል። በአንጻሩ በኦሮሚያ ክልል ስር የሚገኙት 10 የክልል ምርጫ ክልሎች (ጥቁር እንጭኒ፣ ወሊሶ 2፣ ቀርሳ 2፣ ጉቴ፣ ጮሌ፣ ጭሮ 1፣ ሳጉሬ፣ ኦሞናዳ 1፣ ጫንጮ እና አርቦዬ) እያንዳንዳቸው 3 ወንበሮች ያሏቸው ሲሆን፣ 30ውንም መቀመጫዎች ሙሉ በሙሉ ብልፅግና አሸንፏል።

ቦርዱ ትላንት ሰኔ 2 ቀን 2018 ዓ.ም. ባወጀው የመጀመሪያ ዙር የከፊል ውጤት መግለጫው፣ ለክልል ምክር ቤት ካጸደቃቸው የምርጫ ውጤቶች መካከል በ46ቱ ብልፅግና ፓርቲ ማሸነፉን፣ እንዲሁም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከተገለጹት 12 ወንበሮች መካከል በ11ዱ ብልፅግና ማሸነፉን መግለጹ የሚታወስ ነው።

በትላንትናው ዕለት ተቃዋሚ ፓርቲዎቹ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የፓርላማ ዕጩ እና የቤኒሻንጉል ህዝብ ነፃነት ንቅናቄ (ቤህነን) ለክልሉ ምክር ቤት ያሸነፏቸው ሁለቱም ወንበሮች በተመሳሳይ መልኩ ብልፅግና ፓርቲ ያልተወዳደረባቸው እንደነበሩ “ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” መዘገቧ ይታወሳል።

ትላንት እና ዛሬ በታወጁት የምርጫ ውጤቶች መሠረት ብልፅግና ፓርቲ ተወዳድሮ የተሸነፈበት የፓርላማም ይሁን የክልል የምርጫ ክልል የለም። እስካሁን በድምሩ 22 የፓርላማ እና 85 የክልል ምክር ቤት ወንበሮች ውጤቶች ይፋ ተደርገዋል። ለፓርላማ 21ዱን እንዲሁም ለክልል ምክር ቤቶች 83ቱን ብልፅግና ፓርቲ ማሸነፉ ተገልጿል።

በስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ፣ የምርጫ ክልል እዣ 2 የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ)ን ወክለው ተመርጠው የነበሩት የፓርላማ ተወካይ የነበሩት ባርጠማ ፍቃዱ ሲርጋ፣ በሰባተኛው ምርጫ ያልተወዳደሩ ሲሆን፣ ኢዜማም በምርጫ ክልሉ ሌላ ዕጩ አላቀረበም።

ከውጤቱ እወጃ በተጨማሪ፣ የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ በዛሬው ምሽት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደገለጹት፤ ከተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ከግል ዕጩዎች በጥቅሉ 120 የሚሆኑ አቤቱታዎች እና ቅሬታዎች ለቦርዱ ቀርበዋል።

ቦርዱ ቅሬታ ከቀረበባቸው አካባቢዎች መካከል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5 አቤቱታዎች፣ እንዲሁም ለክልል ምክር ቤት 24 መደበኛ አቤቱታዎች በይፋ እንደደረሱት ለይቶ አስታውቋል። ከዚህ ቀደም ቦርዱ 47 መደበኛ ቅሬታዎች (31 ከፓርቲዎች እና 16 ከግል ዕጩዎች) እንደደረሱት ገልጾ የነበረ መሆኑ ይታወቃል።

አሁን ቦርዱ የቀረቡትን አቤቱታዎች በሕግ ባለሙያ ጉባዔ አማካኝነት የማደራጀት እና የምስክር የመስማት ሥራ ላይ መሆኑን ሰብሳቢዋ አብራርተዋል። ሜላትወርቅ የቅሬታዎቹን ውጤት አስመልክተው ሲናገሩ፣ ፓርቲዎች ያቀረቡትን ቅሬታ ቦርዱ ተቀብሎ በትክክል ከገመገመ በኋላ፣ ጉዳዩ በኦዲት ተጣርቶ የምርጫ ውጤትን ፍጹም የሚያስቀይር ሆኖ ከተገኘ፣ ሂደቱ ተመርምሮ በየምርጫ ክልሎቹ ላይ ምርጫ በድጋሚ እንዲከናወን ይደረጋል ብለዋል።

እነዚህ ቅሬታ የቀረበባቸው የምርጫ ክልሎች ውጤታቸው ወደ ኋላ እንዲቆይ ተደርጎ የማጣራት ሥራ እየተሠራ ሲሆን፣ የምርመራ ሂደቱ ሲጠናቀቅ ቀሪዎቹ ውጤቶች ለሕዝብ ይፋ እንደሚሆኑ ተገልጿል።

በምርጫ ክልል ደረጃ የውጤት መለጠፍ ሂደትን በተመለከተ፣ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ከተካሄደባቸው 501 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና 638 የክልል ምክር ቤቶች (በአጠቃላይ 1,139 ምርጫ ክልሎች) መካከል በሁሉም ቦታዎች ላይ ውጤት በምርጫ ክልል ደረጃ ሙሉ በሙሉ መለጠፉን ዋና ሰብሳቢዋ ተናግረዋል።

ሆኖም፣ በትላንትናው ዕለት በሁለት ምርጫ ክልሎች ላይ የማዳመር ሥራ ባለመጠናቀቁ ውጤት አለመለጠፉን ገልጸው የነበረ መሆኑን ያስታወሱት ወ/ሮ ሜላትወርቅ፣ ዛሬ ላይ የሃላባ 1 ምርጫ ክልል የማዳመር ሥራ ሙሉ በሙሉ መጠናቀቁን፣ በአንጻሩ የቀብሪ በያህ ምርጫ ክልል የማዳመር ሥራ አሁንም ድረስ ሙሉ በሙሉ አለመጠናቀቁን ጠቁመዋል።

እስካሁን ባለው ሂደት መሠረት፣ በየምርጫ ክልሉ ከተለጠፉት ውጤቶች መካከል 1,008 የሚሆኑት በማዕከል ደረጃ ደርሰው የማዳመር እና የማረጋገጥ ሥራ እየተሠራባቸው እንደሚገኝ ሰብሳቢዋ ገልጸዋል። በተጨማሪም አጠቃላይ ሂደታቸው ተጠቃሎ ወደ ማዕከል ጉዞ የጀመሩ የሌሎች 31 የምርጫ ክልሎች ውጤቶች መኖራቸውን የቦርዱ ሰብሳቢ በመግለጫቸው አብራርተዋል።

ሰኔ 2 ቀን የተከናወነውን የልዩ ጣቢያዎች ምርጫ አስመልክቶም፣ በሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች መጠለያዎች እና በወታደራዊ ካምፖች የተሰጠው ድምፅ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ፣ በአሁኑ ወቅት ውጤቱን ወደ ማዕከል የማጓጓዝ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ቦርዱ አስታውቋል። (ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)