የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) ትናንት ሰኔ 3 ቀን 2018 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ በቅርቡ የተከናወነው 7ኛው ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ “በማግለል፣ በማስገደድ እና መዋቅራዊ በሆነ የምርጫ ስርቆት የተበከለ” በመሆኑ ሂደቱን ሙሉ በሙሉ ትርጉም አልባ አድርጎታል ሲል በከረረ ቃላት ኮንኗል።
ፓርቲው ምርጫው አምባገነናዊነትን “ሕጋዊ ለማድረግ የተወጠነ የፖለቲካ ድራማ” ነው ሲል የወቀሰ ሲሆን፣ በሀገሪቱ ባለው አውዳሚ ጦርነት ምክንያት ሂደቱ ወታደራዊ ጥበቃ ባለባቸው ጥቂት ከተሞች ብቻ መደረጉንና ትግራይ ክልል ሙሉ በሙሉ አለመሳተፉን በጥቅስ አስገንዝቧል።
ኦፌኮ “በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች እየተካሄደ ያለው አውዳሚ ጦርነት በሰፊ የገጠር እና የከተማ ዳርቻዎች ተአማኒነት ያለው ምርጫ ማካሄድ ፈጽሞ የማይቻል እንዲሆን አድርጎታል” ያለ ሲሆን፣ ምርጫው በከፍተኛ ወታደራዊ ጥበቃ ሥር ባሉ ዋና ዋና ከተሞች ብቻ ተደርጓል ብሏል።
በምርጫው ዕለት የምርጫ አስፈጻሚዎች ግልጽ አድልዎ መፈጸማቸውን፣ በመራጮች ላይ ማስፈራራት መኖሩን እና የተቃዋሚ ታዛቢዎች በኃይል መባረራቸውን የገለጸው የፓርቲው መግለጫ፤ ሂደቱን የታዘቡትን የአፍሪካ ኅብረት እና የኢጋድ ልዑካን ሪፖርት “የምርጫ ዕለት ቱሪዝም እንጂ እውነተኛ የታዛቢነት ሚና አይደለም” ሲል ነቅፎታል።
ኦፌኮ የአፍሪካ ኅብረት እና የምሥራቅ አፍሪያ የልማት በይነመንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ) “እጅግ አነስተኛ 100 የማይሞሉ ታዛቢዎች በማሰማራት በሃገሪቱ ከሚገኙ 52,000 በላይ የምርጫ ጣቢያዎች ውስጥ ደኅንነታቸው በተጠበቁ ጥቂት ከተሞች ብቻ የተወሰኑ (Safe-zone bias) 208 (0.4%) በሚወክሉ ጣቢያዎች ብቻ በመገኘት፣ የቅድመ ምርጫ ችግሮችን እና አጠቃላይ የሃገሪቱን ሁኔታ ሳያገናዝቡ በዕለቱ ትዝብት ላይ ብቻ በመመስረት በመላው ኢትዮጲያ ነፃ እና ፍትሓዊ ምርጫ እንደተካሄደ በማስመሰል ያወጡት የ’ሰላማዊና ግልጽነት’ ሪፖርት የ’ምርጫ ዕለት ቱሪዝም’ እንጂ እውነተኛ የታዛቢነት ሚና አይደለም” በማለት ክፉኛ ተችቷቸዋል።
በተመሳሳይ፣ የአውሮፓ ኅብረት በመሬት ላይ ያለውን አፈና ችላ በማለት በርቀት የሰጠውን በጎ አስተያየት “የዲፕሎማሲ ማባበያ” (Diplomatic appeasement) ሲል አጣጥሎታል።
ኦፌኮ የሀገሪቱ ጥልቅ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ስብራት በዚህ ምርጫ ሊጠገን እንደማይችል ጠቅሶ፣ ሀገሪቱን ከመበታተን ለማዳን በአሁኑ ወቅት ከመንግሥት ጋር በጦርነት ላይ ያሉ ታጣቂ ኃይሎችን እና ሁሉንም የፖለቲካ ኃይሎች ያካተተ “በድርድር ላይ የተመሠረተ አዲስ የፖለቲካዊ ስምምነት ፍኖተ ካርታ” በአስቸኳይ እንዲቀረጽ ጠይቋል። በማጠቃለያውም፣ መንግሥት ወታደራዊ ኃይልና ማግለልን ትቶ ሁሉን አቀፍ ውይይት እንዲጀምር፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ለራስን በራስ ማስተዳደርና ለእውነተኛ ሕብረ-ብሔራዊ ፌዴራሊዝም በሰላማዊ ትግል እንዲጸኑ፣ እንዲሁም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በመንግሥት ላይ ትርጉም ያለው ጫና እንዲያሳድር ፓርቲው ሦስት መሠረታዊ አስቸኳይ ጥሪዎችን አስተላልፏል። (ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)




